Thursday, January 23, 2014

ለነባር የ20/80 ቤቶች ፕሮግራም ተመዘጋቢዎች ተገንብተው የተጠናቀቁ 50 ሺ ቤቶች ሊተላለፉ ነው


   የ10/90 ቤት ፈላጊ ተመዝጋቢዎች ሙሉ በሙሉ በዚህ ዓመት መጨረሻ ቤታቸውን ይረከባሉ፡፡ በአዲስ አበባ ያለውን የመኖሪያ ቤት ፍላጎት ሙሉ በሙሉ ለማሟላት የከተማ አስተዳደሩ ነባርና አዳዲስ የቤት ፕሮግራሞችን ይፋ አድርጎ በድጋሜ ምዝገባ ካካሄደ ስድስት ወራት አልፏል፡፡ ቁጠባን መሰረት ባደረጉ በሁሉም የቤቶች ፕሮግራም 9 መቶ ሺ የሚደርስ የከተማዋ ኑዋሪ ተመዝግቧል፡፡

   ኑዋሪዎቹ በኢትዮጵያ ንግድ ባንክም የሚጠበቅባቸውን ቁጠባ እያካሄዱ ነው፡፡ ከቁጠባው ጎን ለጎንም የከተማ አስተዳደሩ ቤቶችንም መገንባት ቀጥሏል፡፡ የአዲስ አበባ ከተማ ቤቶች ግንባታ ፕሮጀክት ጽ/ቤት ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ይድነቃቸው ዋለልኝ በአሁኑ ወቅት የ75ሺ ቤቶች ግንባታ በመጠናቀቅ ላይ ነው ብለዋል፡፡

   የተጠናቀቁ ቤቶችን ለማስተላለፍ የቅድመ ዝግጅት ስራዎች ተጠናቋልም ብለዋል ዋና ስራ አስኪያጁ፡፡ መካከለኛ ገቢ ያላቸውን የከተማዋን ነዋሪዎች፣ በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያንንና ትውልደ ኢትዮጵያውያንን የቤት ባለቤት በሚያደርገው 40/60 ፕሮግራም 160 በላይ ዜጎች ተመዝግበዋል፡፡ የእነዚህ ቤቶች ግንባታም በአምስት የግንባታ ቦታዎች እንደተጀመሩ የአዲስ አበባ የቁጠባ ቤቶች አነርፕራይዝ የህዝብ ግንኙነት ሀላፊ አቶ ዮሀንስ አበይነህ አስታውቀዋል፡፡

  ለ40/60 የቤቶች ፕሮግራም ቀጣይ 12 ሺ ቤቶች ለመገንባትም የመሬት መረጣና ሌሎች አስፈላጊ ስራዎች ተጠናቀው ወደ ግንባታ ለመግባት ዝግጅት መጠናቀቁን የህዝብ ግንኙነት ኃላፊው ተናግረዋል፡፡

No comments:

Post a Comment