Friday, March 28, 2014

ኃይሌና ጌጤ በሽልማት ገቢ የኢትዮጵያን አትሌቶች ይመራሉ

       
 
የዓለም አትሌቶች በጎዳና ላይ ሩጫዎችና በተለያዩ የአትሌቲክስ ውድድሮች ባገኙት የሽልማት ገቢ  ከ1 እስከ 50  በወጣው ደረጃ ኢትዮጵያ  በሁለቱም ፆታዎች  በ23 አትሌቶች እንደተወከለች ለማወቅ ተቻለ፡፡ ከኢትዮጵያ አትሌቶች በሽልማት ገቢያቸው ኃይሌ ገብረስላሴ እና ጌጤ ዋሚ ይመራሉ፡፡ ባለፉት 15 ዓመታት  በዓለም ዙርያ በተካሄዱ የጎዳና ላይ ሩጫዎች እና ሌሎች የአትሌቲክስ ውድድሮች አትሌቶች ያገኙአቸውን በግልፅ የሚታወቁ  የገንዘብ ሽልማቶች በመደመር ደረጃውን ከሳምንት በፊት  በድረገፁ ይፋ ያደረገው የጎዳና ላይ ሩጫዎች የስታትስቲክስ ባለሙያዎች ዓለም አቀፍ ማህበር (ARRS/ Associations of Road racing statisticians )  ነው፡፡ ይህን ዓለም አቀፍ ደረጃ  በወንዶች ምድብ  የሚመራው በ52 የተለያዩ ጊዜያት 3 ሚሊዬን 548 ሺህ 398 ዶላር ያፈሰው ኃይሌ ገብረስላሴ ሲሆን በሴቶች ምድብ ደግሞ በ56 የተለያዩ ጊዜያት 2 ሚሊዬን 236 ሺህ 415 ዶላር ያገኘችው የእንግሊዟ ፓውላ ራድክሊፍ ናት፡፡  በወንዶች ምድብ በደረጃው ሰንጠረዥ መግባት ከቻሉት  50 አትሌቶች 10 ኢትዮጵያውያን ሲገኙበት በድምሩ 10 ሚሊዬን 345 ሺህ 423 ዶላር በሽልማት ገቢ አድርገዋል፡፡ በሴቶች ምድብ ደግሞ  ከ50ዎቹ አትሌቶች 13 ያህሉ ኢትዮጵያውያን ሲሆኑ ድምር የሽልማት ገቢያቸው 9 ሚሊዬን 575 ሺህ 957 ዶላር ነው፡፡

      የጎዳና ላይ ሩጫዎች የስታትስቲክስ ባለሙያዎች ማህበር www.arrs.net በተባለው ድረገፁ በዓለም አቀፍ የአትሌቲክስ  ከ3ሺ ሜትር አንስቶ ያሉትን የጎዳና ላይ ሩጫዎች እና ሌሎች ውድድሮች በትኩረት በመከታተል የአትሌቶችን የውጤታማነት ደረጃ፤ ሰዓትና ድምር ስኬት ከፋፍሎ በማስላት ወርሃዊ እና ዓመታዊ መረጃዎችን ይፋ ያደርጋል፡፡ በዚሁ ድረገፅ የዓለም አትሌቶች በጎዳና ላይ ሩጫዎች እና በሌሎች የአትሌቲክስ ውድድሮች በሰበሰቡት የሽልማት ገንዘብ ላይ ደረጃውን በማውጣት የሚያስታውቅበት አሰራርም አለው፡፡ ኤአርአርኤስ በሽልማት ገቢ  ለሚሰራው ደረጃ እና ሌሎች መረጃዎችን በድረገፁ ለማስፈር የሚጠቀምበትን ዳታቤዝ ለማዘጋጀት   በመላው ዓለም የሚደረጉን ከ160 ሺህ በላይ የጎዳና ላይ የሩጫ እና ሌሎች ውድድሮችን በመከታተል መረጃዎችን ከማሰባሰቡም በላይ በየውድድሩ  35 ሺህ አትሌቶች ያስመዘገቧቸውን 900 ሺህ በላይ ውጤቶች አገናዝቧል፡፡ እነዚህን መረጃዎች በማሰባሰብ እና በማቀናበር ከስታትስቲክስ ባለሙያዎች ማህበር ጋር በመላው ዓለም ያሉ ከ100 በላይ ባለሙያዎች የሚሰሩት ሲሆን  በሺዎች የሚቆጠሩ የአትሌቲክስ በጎ ፍቃደኞችም በተለያዩ ተግባራት ተሳታፊ ይሆኑበታል፡፡

      ኤአርአርኤስ የዓለም አትሌቶች በጎዳና ላይ ሩጫ እና ሌሎች የአትሌቲክስ ውድደሮች ያገኟቸውን የሽልማት ገቢዎች ያሰባሰበው በግል በሚመዘገብ ውጤት በግልፅ የሚወስዷቸውን የሽልማት ድርሻዎችና  በቡድን ውጤት የሚያገኙትን ገቢ በመደማመር ነው፡፡ በሽልማት ገቢው የተሰራው ደረጃ አትሌቶች በተለያዩ ዓለምአቀፍ ውድድሮች በግላቸው ተደራድረው የሚያገኟቸውን የተሳትፎ ክፍያዎች፤  ልዩ ልዩ ጥቅማጥቅሞች፤ የቦነስ ሽልማቶች፤ የስፖንሰር ገቢዎች፤ እንደመኪና አይነት የተለያዩ ስጦታዎችን ያካተተ አይደለም፡፡ ከዚህ በታች የቀረበው በኤአርአርኤስ ድረገፅ በዓለም አትሌቶች የሽልማት ገቢ ደረጃ ላይ በሁለቱም ፆታዎች ከ50ዎቹ ተርታ የገቡት የኢትዮጵያ አትሌቶች ባገኟቸው የሽልማት ገቢዎች በአገር እና በዓለምአቀፍ የሚኖራቸው ደረጃ ነው፡፡
=======================
በወንዶች
$3,548,398  (52)  ኃይሌ ገ/ስላሴ
                                                 - ከዓለም 1ኛ
1,559,828   (47) ቀነኒሳ በቀለ - 2ኛ
1,544,520   (18) ፀጋዬ ከበደ - 4ኛ
648,500   (10) አዲስ አበበ   - 15ኛ
$573,445   (24) ሌሊሳ ዴሲሳ  - 21ኛ
568,947   (38)  ገብሬ ገ/ማርያም - 22ኛ
533,700   (32) ድሪባ መርጋ - 26ኛ
475,850   (31) ታደሰ ቶላ- 35ኛ
475,465   (26) ጥላሁን ረጋሣ  -36ኛ
416,770   (11) ደሬሳ ኤዴ - 47ኛ

በሴቶች
$1,438,280   (44) ጌጤ ዋሚ   - ከዓለም 6ኛ
1,254,395   (67) ብርሃኔ አደሬ  - 9ኛ
970,893   (56)  መሠረት ደፋር  - 16ኛ
904,836   (43) ጥሩነሽ ዲባባ   - 17ኛ
835,605   (45)  ማሚቱ ደሳካ  - 19ኛ
772,189   (19) አሰለፈች መርጊያ  -  22ኛ
647,873   (46) ደራርቱ ቱሉ  - 28ኛ
622,053   (36) ድሬ ቱኔ አሪሲ  - 29ኛ
621,508   (25)  ብዙነሽ በቀለ  - 30ኛ
517,380   (40)  መሰለች መልካሙ   - 36ኛ
517,220   (18)  ትርፌ በየነ  - 37ኛ
515,185   (27) አፀደ ባይሳ  - 40ኛ
475,920  (29)  ሙሉ ሰቦቃ -  45ኛ
ማስታወሻ - በቅንፍ የተቀመጠው አኃዝ የተሸለሙበት ብዛት ነው፡፡
አንድ ዶላር በወቅታዊ የምንዛሬ ዋጋ 19.80 ብር ነው፡፡
                                                         ምንጭ ፡- አዲስ አድማስ ጋዜጣ

የምኒልክ መስኮት


     ይህ ቦታ ከደ/ብርሃን ከተማ ወደ ሰሜን አቅጣጫ በሚወስደው የአስፖልት መንገድ 4ዐ ኪ.ሜትር ያክል እነደተጓዙ አንዲት ጥድና ጅብ ዋሻ የሚባሉ አካባቢዎች እንደደረሱ ወደ ቀኝ በመታጠፍ ወደ ከፍታ ተራራ በመውጣት የሚያገኙት ተፈጥሮአዊ ክስተት ነው፡፡ የአካባቢው ነዋሪዎች ይህንን ቦታ "የምኒልክ መስኮት" አንዴም "ገማሳ ገደል" በማለት ይጠሩታል፡፡ ይህ ቦታ በጣም ከፍተኛ ተራራ ላይ የሚገኝ በመሆኑ ከአመት አመት ልምላሜ የማያጣውና በአረንጓዴ ሸማ እንደተሸፈነ ጌጥ ተፈጥሮ ውበት ያለበሰችው አስደናቂ ሥፍራ ነው፡፡

       ከተፈጥሮአዊ ውበቱ ጋር ተዳምሮ በአካባቢው ያለው እንደ ጭስ ጧት ከማታ የሚግተለተለው ጉምና ነፋሻማ አየር ሁልጊዜ የማይሰለችና አስደሣች ስፍራ ያደገርዋል፡፡ በዚህ ስፍራ ነው እንግዲህ ሆን ተብሎ የታቀደና በተዋጣለት መሀንዲስ ተከርክመው የተሰሩ የሚመስሉት ግራና ቀኝ እንደምስል ቀጥ ብለው የሚገኙትን ተራሮች ከነ ግርማ ሞገሣቸው የሚያገኙት፡፡

  በዚህ ቀዳዳ ወደ ምስራቅ ቁልቁል አሻግረው ሲመለከቱ ያላሰቡትንና ያልጠበቁትን ክስተት ይመለከታሉ፡፡ የይፋት ቆላማ መንደሮች፣ ኢትዮጵያን ለሁለት ከፍሎ የሚያልፈው ትልቁ ስምጥ ሸለቆ ፣ የአፋር ክልል በርሃማ ቦታዎችና የአዋሽ ወንዝ በሰልፍ ተኝተው በአግራሞት ለመመልከት ያስችልዎታል፡፡ይህ የሚሆነው ታዲያ ከገደሉ በር እንደ እጣን ጭስ እየተጥመለመለ የሚወጣው ነጭ ጉም እና የአካባቢውን ቀዝቃዛ አየር እየሳቡ ነው ፡፡

  አፄ ምኒልክ በንግስና ዘመናቸው ወደ አያታቸው ንጉስ ሣህለ
 ስላሴ የትውልድ ቦታ ወደ ሆነችው ሰላድንጋይ ከተማ ለተለያዩ ጉዳዩች ሲሄዱና ሲመለሱ በዚህ ስፍራ በመገኘት ትልቁ የስምጥ ሸለቆ የሚያልፍባቸውን አካባቢዎችና የአዋሽን ወንዝ በተመለከቱ ጊዜ እጅግ ከመደነቃቸው የተነሣ በተደጋጋሚ በቦታው እየተገኙ ይመለከቱ ነበር፡፡ በዚህ የተነሳ የአካባቢው ነዋሪዎችም የዚህን ስፍራ መጠሪያ ስም የምኒልክ መስኮት የሚል ስያሜ ሰጥተውት እስከ አሁን ድረስ በዚሁ ስያሜ እየተጠራ ይገኛል፡፡



        ሥፍራው የወፍ ዋሻን ደን ከፊል ገጽታ ከስሩ የያዘ ሁልጊዜ ለምለም የማይለየው በመሆኑ በርካታ ዝንጀሮዎች፣ ሺኮኮዎችና ገደሉን እንደመጠለያ አድርገው የሚኖሩ በርካታ የአእዋፍ ዝርያዎች የሚገኙበት መሆኑ ደግሞ የቱሪስት መስህብነቱን ይበልጥ ማራኪና አስደናቂ ያደርገዋል፡፡

Thursday, March 27, 2014

ከልቼ ቤተመንግሥት እስከ ታዕካ ነገሥት ኢየሱስ - በመ/ር ሳሙኤል ተስፋዬ


  በአብዛኛው ኢትዮጵያውን ዘንድ የሚወደዱትናእምዬበሚል ቅጽል የሚጠሩት ዐፄ ምኒልክ ለሀገሪቱም ሆነ ለቤተ ክርስቲያን ባለውለታ ነበሩ፡፡እምዬየሚለውን ቅጽል ሕዝቡ የሰጣቸው፤ የተራበውን ሕዝብ ግብር የሚያበሉ፤ ያለ ፍርድ ሰው የማይቀጡና ደግ ስለሆኑ ነው፡፡

  ዳግማዊ ዐፄ ምኒልክ ከአባታችው ከሸዋው ንጉሥ ኃይለ መለኮት ሣህለ ሥላሴና ከእናታቸው ወይዘሮ እጅጋየሁ ለማ አድያም ነሐሴ ፲፪ ቀን ፲፰፻፴፮ .. ደብረ ብርሃን አካባቢ አንጎለላ ከሚባል ሥፍራ ተወልደው፤ በአንጎለላ መቅደላ ኪዳነ ምሕረት ቤተ ክርስቲያን ክርስትና ተነሡ። አያታቸው ንጉሥ ሣህለ ሥላሴ የምኒልክን መወለድ ሲሰሙምን ይልህ ሸዋበሉት ብለው ስም አወጡ። እሳቸው “…ምኒልክ በሚል ስም የሚነግሥ ንጉሥ ኢትዮጵያን ታላቅ ያደርጋታልየሚል ትንቢት ስለነበርምኒልክየኔ ስም ነው ብለው ነበር። ሆኖም፣ በህልማቸው ከልጁ ጋር አብረው ቆመው ከሳቸው ጥላ የልጁ ጥላ በልጦ፤ በእግር የረገጡትን መሬት ሲያለካኩ እሳቸው ከረገጡት ልጁ የረገጠው ረዝሞ አዩ። ከዚህ በኋላምኒልክ የኔ ስም አይደለም። የሱ ነው። ስሙን ምኒልክ በሉትብለው አዘዙ። ጳውሎስ ኞኞአጤ ምኒልክበተባለው መጽሐፍ
 
    ምኒልክ እስከ ሰባት ዓመታቸው ድረስ መንዝ ውስጥ ጠምቄ በሚባል አምባ ከእናታቸው ዘንድ አደጉ።አያታቸው ንጉሥ ሣህለ ሥላሴ ሲሞቱ የሸዋውን አልጋ የምኒልክ አባት ንጉስ ኃይለ መለኮት ወረሱ።ዓጼ ቴዎድሮስ በጥቅምት ወር ፲፰፻፵፰ / ትግራይንና ወሎን አስገብረው፣ ምኒልክ ገና የአሥራ ሁለት ዓመት ልጅ ሳሉ፤ የድፍን አማራንና የወሎን ጦር አስከትተው የሸዋውን ንጉሥ ኃይለ መለኮትን ለማስገበር ሸዋ ገቡ። ሁለቱ መሪዎች ጦርነት ለመግጠም ተዘጋጅተው ሲጠባበቁ ንጉሥ ኃይለ መለኮት ባደረባቸው ሕመም ጥቅምት ቀን ፲፰፵፰ አረፉ። በዚህ ጊዜ የሸዋ መኳንንት ሕፃኑን ምኒልክን ከጠላት እጅ እንዳይወድቅባቸው ይዘው ሸሹ፤ ዳሩ ግን ዐጼ ቴዎድሮስ እንደሚከታተሏቸው ስላወቁ ኅዳር ቀን ፲፰፵፰ / የልጅ ምኒልክ ሠራዊትና የዐፄ ቴዎድሮስ ሠራዊት በረከት በተባለው ቦታ ላይ ገጥሞ የምኒልክ ሹማምንት አቶ በዛብህ፣ አቶ አንዳርጋቸው ሁሉ ተያዙ። ልጅ ምኒልክም ለቴዎድሮስ ገቡ። ምኒልክ መቅደላ ገብተው በቁም እሥር ይቀመጡ እንጂ ከቴዎድሮስ ልጅ ከመሸሻ ጋር አብረው አደጉ። ወዲያውም የደጃዝማችነት ማዕረግ ተሹመው በጥር ወር ፲፰፻፶፮ . የዓፄቴዎድሮስን ልጅ ወይዘሮ አልጣሽን አገቡ። በዚህ ሁኔታ ፳፪ ዓመታቸው ድረስ ለአሥር ዓመታት ዐፄ ቴዎድሮስ ግቢ ኖሩ።

    ዐፄ ቴዎድሮስ ምኒልክን እንደልጃቸው ያዩዋቸውና በታላቅ ጥንቃቄም ያስተምሯቸው ነበር። ምኒልክም ቴዎድሮስን እንደአባት ይወዷቸው እንደነበር ይገለጻል። ምኒልክ ከመቅደላ ሰኔ ፳፬ ቀን ፲፰፻፶፯ አምልጠው አንኮበር ገቡ። በአንኮበር ጥቂት ወራት ከተቀመጡ በኋላ ወደ ደብረ ብርሃን ወርደው አዲሱን ከተማቸውን ልቼን እያሠሩ ተቀመጡ። ዐፄ ምኒልክ የመጀመሪያ ቤተመንግሥታቸው ልቼ እንደነበረ የታሪክ ድርሳናትና የልቼ ቤተ መንግሥት ፍርስራሽ ያስረዳል፡፡ በተለይም ዐፄ ምኒልክ ከየካቲት ፲፰፻፷ . እስከ ታኅሣሥ ፲፰፻፸፰ . በልቼ ቤተመንግሥት እንደነበሩ በተጻጻፉት ደብዳቤ አማካኝነት ታውቋል ፡፡ ምኒልክ ከልቼ ቤተመንግሥት ሳሉ ከሀገር ውጭም ሆነ ከሀገር ውስጥ መልእክቶችን ተለዋውጠዋል። ከየካቲት ቀን ፲፰፻፸፰ . እስከ የካቲት ቀን፲፰፻፸፰ . ከዐፄ ዮሐንስ ጋር ልቼ ላይ ውጊያ አደርገዋል፡፡ በኋላም የካቲት ፲፪ ቀን ፲፰፻፸፰ . ውጊያ ለማቆም ፣የልቼ ሥልጣን ማካፈልንና በሌሎች ጉዳዮችም ለመረዳዳት ስምምነት አድርገዋል፡፡ ይህም የልቼ ስምምነት ተብሎ ተመዝግቦ ይገኛል፡፡

   ኤስ ሩቬንደንና ሪቻርድ ፓንክረሥት እንደዘገቡት ዳግመኛ በመጋቢት ፲፰፻፸፰ ዐፄ ዮሐንስና ዐፄ ሚኒሊክ ልቼ ላይ የማዕረግ አጠቃቀምን በተመለከተ ስምምነት ላይ ደረሱ፡፡ ጸሐፌ ትእዛዝ ገብረ ሥላሴ ታሪከ ነገስት ዘዳግማዊ ምኒልክ በተሰኘው መጽሐፋቸው የዐጼ ምኒልክን ንግሥናና የልቼ ቤተ መንግሥትን ሥነ ሥርዓት እንዲህ ይገልጹታል “….(ምኒልክ) መስቀልን ውለው ልቼ ከተማቸው ወጡ፡፡ ከዚያም በሥርዓተ መንግሥት ዘውድ የሚደፉበት፣ አዳራሽ የሚገኙበት ጊዜ ነውና ልቼ ከተማ ከዕድሞው ግቢ ሰፊ ዳስ ተሠርቶ ግብር ለማብላት ልክ መጠን የሌለው ሁኖ ተዘጋጅቶ ነበረ፡፡ ደግሞም ከዳሱ አፋፍ ከሰገነቱ ዝቅ ያለ ሥራው ልዩ ልዩ የሆነ መንበር ተሠርቶ ነበር፡፡ በዚህም ጊዜ የዳሱ ጌጥ ሥራው የቆመበትም ሁሉ በልዩ ልዩ ዓይነት ግምጃ የተሸፈነ ነበር፡፡  ከዚህም አስቀድመው ባዋጅበምገዛው አገር የሚኖር ካህን ከየደብሩ መስቀልና ጥና ከአልባሳቱ ጋር እየያዘ በጥቅምት ሁለት ቀን ይግባብለው አዘውት ጠቅሎ ገባ፡፡ በዚህም ጊዜ በእስክንድርያ ሃይማኖት ሳይገዘት ሰንብቶ የነበረው ሲገዘት ሰነበተ፡፡


     ከዚህም በኋላ በጥምቅት በ፫ ቀን ቅዳሜ ማታ ንጉሥ ከነሠራዊታቸው ከልቼ ተነሥተው ደብረ ብርሃን ወርደው አደሩ፡፡ ሲነጋ ንጉሡ ከመቅደስ ልብሰ መንግሥት ለብሰው መምህር ገብረ ሥላሴ፣ መምህር ግርማ ሥላሴ ንጉሡን በወርቅ አልጋ አስቀመጧቸው፤ ዘውዱንም ደፉላቸው፡፡ በዚያን ጊዜ የመምህራኑ ጸሎት ይህ ነው፡፡ እግዚኦ በኃይልከ ይትፌሣሕ ንጉሥ ምኒልክ ወብዙኅ ይትሐሠይ በአድኅኖትከ፤ ፍትወተ ነፍሱ ወሀብኮ፤ ወስእለተ ከናፍሪሁ ኢከላእካ፤ እስመ በጻሕካ በበረከት ሠናይ፤ ወአነበርከ አክሊለ ዲበ ርእሱ ዘእምዕንቍ ክቡር፤ ሐይወ ሰአለከ ወሀብኮ፤ ለነዋኅ መዋዕል ለዓለመ ዓለም እያሉ ምስጋና እየጨመሩ በየመሥመሩ ሁሉ ንሴብሕ ወንዜምር ለፅንዕከ ብለው ይህንን መዝሙር እያደረሱ የወርቅ ሰይፍ አስታጠቋቸው፡፡ ቅንት ሰይፈከ ኃያል ውስተ ሐቌከ በሥንከ ወበላሕይከ አርትዕ ተሠራሕ ወንገሥ እያሉ ይህንን መዝሙር በእንተዝ ይገንዩ ለከ አሕዛብ እግዚኦ ለዓለም ወለዓለመ ዓለም እስከሚለው ድረስ ሲጨርሱ ካህናቱም ከቅድስት ቁመው በአንድ ቃል ተቀጸል ጽጌ ምኒልክ ሐፄጌ ተቀጸል ጽጌ አሉ፡፡ ሊቀ መኳስ አጥናፍ ሰገድ ካባ ላንቃ ለብሶ፡፡ ራስ ዳርጌ ራስ በና ራስ ወርቅ አሥረው ወጡ፡፡ ባለወርቅ መጣምር በቅሎዎቻቸው ቀረቡ፡፡ ንጉሡ ከበቅሎ ሲሆኑ ግራ ቀኝ ሰይፍ ተመዞ ነበር፡፡ በዚህ ጊዜ ለጊዜው ተሸልመው የነበሩ ቁጥር የሌላቸው ሊቃውንት ከቤተ ክርስቲያን በወጡ ጊዜ ዑደት ሲሆን እንደ ፊተኛው ተቀጸል ጽጌ ምኒልክ ሐፄጌ ተቀጸል ጽጌ እያሉ ዞሩ ስፍራው ጠቦ በሩቅ ካህናት ንሴብሖ ይሉ ነበር፡፡
     
  ከዚህም በኋላ ጕዞ ተጀመረ፡፡ ሲጓዝም መኳንንቱም በየማዕርጋቸው ሠራዊቱም አጊጦ ጭፍራውም በየአለቀው አምሮ ተሰልፎ ይሄድ ነበር፡፡ እንዲህም ባማረ ጕዞ ተጕዘው ልቼ ከተማቸው ገቡ፡፡ ካዳራሽ ገብተው ከዙፋን ሲቀመጡ ከአደባባዩ የነበሩ መድፎች ፳፪ ጊዜ ተተኰሱ፡፡ ከዚህ ቀጥሎ ከቡሎ ወርቄ ጀምሮ እስከ ሣሪያ ተሰልፎ የነበረው ከቅጥሩም ውስጥ የተሰለፈው ነፍጥ በተተኰሰ ጊዜ ከብዛቱ የተነሣ የክረምት ነጐድጓድ መሰለ፡፡ በንጉሡም ዙፋን አጠገብ በተዋረድ በልዩ ልዩ ዓይነት ሥጋጃው ወላንሣው እየተነጠፈ ተዘጋጅቶ ነበር፡፡ ራሶችም መኳንንቱም በየማዕርጋቸው ተቀምጠው ግርማ መንግሥት ሆኖ አዳራሽ ተገኝተው ዋሉ፡፡ …. ይህም ነገር በተደረገ ጊዜ ያየውም የሰማውም እጅግ አደነቀ፡፡ ይህም የሆነ  ፲፰፻፸፩ ዓመተ ምሕረት በዘመነ ሉቃስ በጥቅምት በአራት ቀን ነው፡፡ በዚህም ጊዜ ዘውዳቸውን በደስታ በፍቅር ለእግዚአብሔርም ለሰውም አስመርቀው ለሠራዊትዎ ብዙ ቀን አዳራሽ (ልቼ) ተገኙ፡፡ሲል፦ አክታ ኢትዮጲካ የተሰኘው መጽሐፍ እንደገለጸው ደግሞ ፲፰፻፸፪ . ፋዘር ማሲያ የተባለው ጣልያናዊ በዐፄ ሚኒልክ ልቼ ተጠርቶ ነበር፡፡ ይህም የሆነው የጣሊያን ጆኦግራፊ ማኅበር ወደኢትዮጵያ መግባት ስለፈለገ ፋዘር ማሲያ ማብራሪያ እንዲሰጥ ታስቦ ነው፡፡ ካርዲናል ማሲና እንደዘገበውም ፲፰፻፸፪ዓ. ልቼ በተደረገው የሶስት ቀን ድግስ ንጉሥ ምኒልክ ተገኝተው ነበር፡፡ ለዚህም ድግስ አዲስ የመመገቢያ አዳራሽ ተሰርቶ ነበር፡፡

   በ፲፰፻፸፮ . የ፷፭ ዓመት አዛውንቱ ማርኬዝ ኦራሊዬ አንቲኖሪ ከጂዮቫኒ፤ ቻሪኒና ሎሬንዝ ላንዳኒ እንዲሁም ከጣሊያን ወታደሮቻቸው ጋር በመሆን በአንኮበር በኩል በጥቅምት ቀን ልቼ ደርሰው ነበር፡፡ በዚያም ከዐፄ ሚኒልክ ጋር ተገናኝተው ወደ አዳራሽ አስገቧቸው ግብዣም ተደረገላቸው ፡፡ በ፲፰፻፸፯ ዐፄ ሚኒልክ ኢትዮጵያውያን ወጣቶች በአውሮፓውያን ወታደራዊ ዘዴ እንዲሰለጥኑ በማሰብ አልጀሪያ የነበረ የፈረንሳይ ጦር አባል ሎያዥ ፓይተር የተባለን ሰው ልቼ መጥቶ እንዲያሰለጥን አድርገዋል፡፡ በ፲፰፻፸፯ መጨረሻ አንቲኖሪና ቻሪኒ በሴባስቲያኖ ማርቲና አንቶኒዬ ቺቺ አማካኝነት ቺሪና ቺቺ ኢትዮጵያን ለማሰሰ መጥተው ግንቦት ፲፬ ቀን ፲፰፻፸፯ ከልቼ ተነሡ ፡፡

    የልቼ ታዕካ ነገሥት ኢየሱስ ክርስቶስ ቤተ ክርስቲያን

     
  የልቼ ታዕካ ነገሥት ኢየሱስ ክርስቶስ ቤተ ክርስቲያን ቀድሞ የዐፄ ምኒልክ ልቼ ቤተ መንግሥት ይባል ነበር፡፡ በአሁኑ ዘመን ደግሞ የታዕካ ነገሥት ኢየሱስ ክርስቶስ ቤተ ክርስቲያን ተበሎ ተሰይሞ በቤተ ክርስቲያን ስም ነው የሚታወቀው፡፡ ስያሜውን የሰጡት የሰሜን ሸዋ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ኤፍሬም ናቸው፡፡ ቀድሞ በደብረ ብርሃን ከተማ ዙሪያ በእግዚአብሔር ፈቃድ የተመሠረቱ በርካታ አብያተ ክርስቲያናት ነበሩ:: ኋላ በግራኝ አህመድ ከፈረሱት ከአብያተ ክርስቲያናት መካከል የኢየሱስ ቤተ ክርስቲያን ይገኝ ነበር:: ይህንንም ስለሚያውቁ ይሆናል አቡነ ኤፍሬም በደብረ ብርሃን (ልቼ) ቤተ ክርስቲያኑ እንዲሠራ የመሠረት ድንጋይ ያኖሩት::
  በድርሳነ ዑራኤል ዘሐምሌ ሁለተኛ ምእራፍ ላይ ተመዝግቦ የሚገኘው አሳብ እንዲህ ይላል “…ከዚህ በኋላ ሃይማኖቱ የቀና ዘርዐ ያዕቆብ ነገሠ እሱም መጀመሪያ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ደብረ ብርሃን ላይ ታላቅ ቤተ ክርስቲያን ሠራ ሁለተኛም ቅድስት በሆነች በእናቱ በድንግል ማርያም ስም ሦስተኛም የመላእክት አለቃ በሆነ በቅዱስ ዑራኤል ስም …” በዚህ አካባቢ የሚኖረው ሕዝብ በአቅራቢያው ቤተ ክርስቲያን ባለመኖሩ ለቀብርም ሆነ፤ ለአገልግሎት ርቆ ለመሄድ ተገዶ ነበር:: በዚህም የተነሣ ይህ ቤተ ክርስቲያን እንዲተከል ግድ ስላስፈለገ ብፁዕ አቡነ ኤፍሬም መጥተው፤ ቦታውን ባርከው፣ ስሙንም የታዕካ ነገሥት ኢየሱስ ክርስቶስ ቤተ ክርስቲያን ብለው መሰየማቸውን መሪጌታ ክፍለ ክርስቶስ ያስረዳሉ::

   ዐፄ ምኒልክ ቤተ መንግሥታቸው እንደነበረ ከመጻሕፍትና ከሀገር ሽማግሌዎች እንዲሁም መጽሐፍ ያገኘነው:: እዚህ ቦታ ላይ የምናያቸው ተጨባጭ ነገሮች  በወቅቱ ዐፄ ምኒልክ ለችሎት በሚያስቀርቡ ጊዜ ሕዝቡ ለፍርድ ሲመጣ ድንጋዮችን ይዞ በመምጣት በመከማቸታቸው ኋላም ለአጥር አገልግሎት ውሏል፡፡ ይህም ዙሪያውን በሦስት ረድፍ የድንጋይ ካብ (እንደ አጥር ሆኖ ስፋቱ ሁለት ሜትር ቁመቱ ሶስት ሜትር) የተከበበ ነው:: ይህ የካብ ድንጋይ አረጀ እንጂ ድሮ እንደተሠራ ነው:: ቢፈርስም እንኳን ታሪኩ እንዳይጠፋ እንደዚሁ ነው የተካበው:: ዐፄ ምኒልክ እዚህ ቦታ ላይ በንግሥናቸውና ለኢትዮጵያ ቅን ተጠሪ ሆነው በነበሩበት ሰዓት የማይጠፋ አትክልት፣ የማይጠፋ ሀብት ለኢትዮጵያ ሕዝብ አስቀምጠውለት ከሄዱት አንዱ  ባሕር ዛፍ ነው:: ቦታው ረግረጋማ ስለነበር ከአውስትራሊያ የባሕር ዛፍ አምጥተው ስለነበር ዛሬ ብዙ አገልግሎት በመስጠት ላይ ነው:: ልጆች በነበርንበት ሰዓት /ቤት ስንሄድ ቦታውን እንዲሁ እናየዋለን እንጂ ገባ ብለን በአካባቢው መጥተን የምናየው ነገር አልነበረም::

   እግዚአብሔር ፈቃዱ ሲሆን ግን ተሰብስበን ይህንን ለመሥራት ወይም ደግሞ የሚሠሩትን አካል እንደ እናንተ ያሉትን የእግዚአብሔር ቤተሰቦች የሆኑትን ለመጥራት ተነሣሥተናል:: በወቅቱ ግን እሳቸው የሠሩትም ያደረጉትም በችሎት የተቀመጡበትም እኛን ሊያነሳሳ እና የእግዚአብሔር ፈቃድ ሆኖ ቅዱስ ሥጋው እና ክቡር ደሙ እንዲፈተትበት ለቤተ ክርስቲያን አገልግሎት እንዲውል እግዚአብሔር ፈቃዱ ሆነ፡፡ ይህን ያስቻለው የንጉሡ ቅንነት ነው ብዬ ነው እኔ  የማስበው:: ይህ ታሪክ ደግሞ የዚህ አካባቢ ብቻ ሳይሆን የመላው ኢትዮጵያ ታሪክ ነው፡፡
   

     ክምር ድንጋይ የሚመስለው በሙሉ ቤት ነው ፡፡ ሁሉም የድንጋይ ቤት ነው:: ቤተ መንግሥት ሰለሆነ በብዙ ዓይነት ነው ቤቱ፡፡  ቤቶቹ ባሉበት ፈርሰው ክምር ድንጋይ ቢሆኑም አጥሩ እንደ ኢያሪኮ ግንብ ሶስት ዙር ባለበት ቢገኝም ድንጋዩም ሆነ መሬቱ የሀገር ሀብትና ንብረት ስለሆነ ማንም ግለሰብ መውሰድና ማጥፋት ሳይችል ታሪኩ እንዳይረሳ እግዚአብሔር እስከፈቀደ ድረስ መቀመጥ አለበት:: ቤተመንግሥት ሰለሆነ ብዙ ዓይነት ነው፡፡ ዋናው ቤተ መንግሥታቸውና የችሎት አዳራሽ አለ፡፡ የንጉሣዊያን ቤተሰብ  መኖሪያ ነው ተብሎ የሚገመት አለ፡፡  የግብር አዳራሽ አለ፡፡ የወታደር ሰፈር አለ፡፡ የግብር ቤት አለ፡፡ ሠራተኞች ሰፈር አለ፡፡ የእንግዶች ማረፊያ አለ፡፡ የመኳንንቱ ቤት ወዘተ. ፍራሹና ግንቡ ይታያል፡፡  የችሎት ቦታቸው የነበረው ቦታ ለቤተ ክርስቲያኑ እንደ መቃኞ እያገለገለ ይገኛል፡፡ በተጨማሪም ፈረስ መፈተኛቸው የነበረው ሜዳ አሁንም ማንም ሳያርሰው ይገኛል፡፡

    የውኃ ምንጫቸው ክረምት ከበጋ አትደርቅም አለች፡፡ የገበያ ቦታቸው የተንጣለለው ሜዳ አሁንም አለ፡፡ በማለት መሪጌታ ገልጸውልን፤ ማሳሰቢያቸውን እንዲህ በማለት አስከተሉታሪኩ እንዳይረሳ እግዚአብሔር ፋቃዱ ሆኗል፡፡ ድንጋዩን ማንም ሳይጠብቀው አግኝተነዋል፡፡ አሁን ደግሞ ቤተ ክርስቲያን እየተሠራ ነው፡፡ እንግዲህ ተባብረን ታሪኩን እንጠብቅ ቤተ ክርሰቲያኑን እንሥራ፡፡

   ቀድሞ የንጉሥ ምኒሊክ ቤተ መንግሥት የነበረው ቦታ ዛሬ የክርስቶስ መመስገኛ ሥፍራ ሆኗል፡፡ ታሪካዊነቱ እንዳለ ሆኖ ቤተ ክርስቲያን በመሠራት ላይ ይገኛል፡፡ ወደፊት ተመራማሪዎች፣ ጎብኚዎች፣ የሃይማኖቱ ተከተዮች ልቼ ታዕካ ነገሥት ኢየሱስ ይመጣሉ፡፡ ሁሉንም እንደፍላጎቱ ማስተናገድ እንዲቻል፡የሁላችንም ትኩረት ተሰጥቶት ቦታውን ማቃናት፣መጠበቅ፣ መገንባት ወዘተ. ይኖርብናል፡፡