Tuesday, November 15, 2016

አንጋፋው የሙዚቃ አቀናባሪ እና ዜማ ደራሲ ሙሉጌታ አባተ ከዚህ አለም በሞት ተለየ፡፡

 
    በሙዚቃው አለም ሶስት አስር አመታትን አስቆጥሯል፡፡ በቀድሞው ሀረርጌ ክፍለ ሀገር ጎሀ ምስራቅ ባንድ ውስጥ የዘመናዊ ሙዚቃ ክፍል ኃላፊ ነበር ፡፡ በዚያ ቆይታው የተለያዩ የኦሮምኛ ኦሮምኛ ዘፈኖችን ከእነ ከድር ሰኢድ፣ አደም ሀሮን እና ሌሎች ድምፃውያን ጋር ሠርቷል፡፡  

   ወዲህ ወደ አዲስ አበባም መጥቶ በስቱዲዮ ውስጥ እጅግ በርካታ የሙዚቃ አልበሞችን አቀናብሯል፡፡ የዘፈን ግጥም ድርሰት ይሞክራል ፣ ፒያኖ እና ቤዝ ጊታርም ይጫወታል፡፡ የሙዚቃ አቀናባሪ እና ዜማ ደራሲ ሙሉጌታ አባተ ከአንጋፋዎቹ ማህሙድ አህመድ ፣ ታምራት ሞላ ፣ መልካሙ ተበጀ እስከ ዘመነኞቹ ጐሳዬ ተስፋዬ ፣ ማዲንጐ አፈወርቅ ፣ ፍቅረ አዲስ ነቃጥበብ የበርካታ ድምፃውያንን ስራዎች አቀናብሯል፡፡ አዲስ አበባ ከመጣ በኋላ በስቱዲዮ ያቀናበረው የመጀመሪያ ስራው የሠርጉአለም ተገኝ  ሸኙኝ የተሠኘ አልበም ሲሆን አበበ ተካ ፣ አረጋኸኝ ወራሽ ፣ ታደሠ አለሙ ፣ ገነት ማስረሻ ፣ ፀጋዬ እሸቱ ፣ ራሄል ዮሀንስ ፣ ኃይለየሱስ ግርማ ፣ ኃይልዬ ታደሠ እና ሌሎች ድምፃውያን ስራዎችንም ቀምሯል፡፡


  ወደ ባህል ሙዚቃዎች የሚያደላው ሙሉጌታ አባተ የአማርኛ ፣ ትግሪኛ ፣ ኦሮምኛ ፣ ጉራጌኛ እና ሌሎች የብሄረሰብ ሙዚቃዎችንም አቀናብሯልዜማም ደርሷል፡፡ ብዙ የበዓላት ስራዎችን እና ማህበራዊ ጉዳዮች ላይ (እንደ ኤች .አይ.ቪ/ኤድስ) የመሳሰሉ ስናዎችንም ዜማ በመድረስ አቀናብሮ ለህዝብ አድርሷል፡፡ ከአማርኛ ሙዚቃዎች በተጨማሪ ለኦሮምኛ, ትግርኛና ጉራጊኛ ዚቃ ያበረከተው አስተዋጽኦም ቀላል አይደለም፡፡ ዚቃ አቀናባሪ፣ የግጥምና ዜማ ደራሲ ሙሉጌታ አባተ ባደረበት ሕመም በኮሪያ ሆስፒታል ሕክምና ሲከታተል ቆይቶ ከዚህ አለም በሞት ተለይቷል፡፡ የቀብር ስነ - ስርዓቱም ወዳጅ ዘመዶቹ ፣ የጥበብ ቤተሰቦች እና አድናቂዎቹ በተገኙበት በሰሚት ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን ተፈፅሟል፡፡


 የ52 ዓመቱ የሙዚቃ አቀናባሪ እና ዜማ ደራሲ ሙሉጌታ አባተ ባለትዳር እና የስድስት ልጆች አባት ነበር፡፡ ፈጣሪ ነፍስህን ይማረው እያልኩ ፤ ለቤተሰቦቹ ፣ ወዳጅ ዘመዶቹ እና አድናቂዎቹ መፅናናትን እመኛለሁ፡፡

Sunday, October 16, 2016

ለአሜሪካው ፕሬዚዳንት ቡሽ ደብዳቤ የፃፈች ኢትዮጵያዊት ….. አርቲስት አሰለፈች አሽኔ

   
  በውበቷና ቁመናዋ ዓይነ ግቡ የሆነችው ይህች ጉብል፤ በሀገር ፍቅር ቴአትር ቤት መድረክ በአካልም በሙያም አድጋ ታላቅ የጥበብ ሰው ለመሆን በቅታለች፡፡ አርቲስቷ ሁለገብ የጥበብ ሰው ስትሆን እጅግ በርካታ አጫጭርና ረጃጅም ቴአትሮችን በመድረክ ተጫውታለች። በግሏ እና ከሌሎች ጋር በማዜም በሸክላ ያስቀረፀቻቸው የሀገር እና የፍቅር እንዲሁም የትዝታ ዜማዎቿ ዘመን ተሻጋሪነታቸውን ያስመሰከሩ ናቸው። ዛሬም ቀልብ ይስባሉ፣ ልብ ያሸፍታሉ። የሀገር ፍቅሯ ንግስት አርቲስት አሰለፈች አሽኔ፡፡
   
  አሰለፈች በአገር ፍቅርና በብሔራዊ ቴአትር እንዲሁም በሲኒማ ራስ (ራስ ቴአትር) 80 በላይ ትያትሮች ላይ ተወናለች፡፡ ለአብነትም ኪሊዮ ፓትራ፣ ሮሚዮ እና ጁሌት ፣ ህይወት፣ አቦዘነች እኔ ላነቺ ክፉ፣ የቬኑሱ ነጋዴ ፣ ቀዩ ማጭድ፣ የልጃገረድ ሳሎን፣ የቆጡን አወርድ ብላ የብብቷን ጣለች፣ እብዷ ጎረቤቴ ፣ የህይወት መራራ ፣ ስራ ለሰሪው እሾህ ላጣሪው ፣ ዞሮ ዞሮ ሁሉም ዜሮ ፣ የሰው ሆዱ የወፍ ወንዱ ፣ ታጋይ ሲፋለም ፣ ቃልኪዳን አፍራሹ ውለታ ደምሳሹ ፣ ቆራጥ ፣ ያላቻ ጋብቻ ፣ የልጃገረድ ሳሎን እና ባሻዳምጤ ጥቂቶቹ ናቸው። በአብዛኞቹ ላይ መሪ ተዋናይ ሆና ነው የሰራችው፡፡ ሁለገቧ አርቲስት አሰለፈች አሽኔ በሲኒማ ራስ (ራስ ቴአትር) ከትወና ባሻገር በምክትል ስራ አስኪያጅነትም አገልግላለች ረጅሙን የስራ ዘመኗን በአገር ፍቅር ቴአትር ቤት ያሳለፈችው አርቲስቷ "አገር ፍቅር ለኔ አሳዳጊ ወላጄ ነው" ትላለች።


  አሰለፈች ከጓደኛዋ ጌጤነሽ ክብረት ጋር በ1968ዓ.ም አካባቢ “ሸገኔዎች” የተሰኘ የሙዚቃ ሸክላ አሳትማም ነበር ፡፡ “እየው ድማሙ  መቼ ነው  ዛሬ ነው  ፍቅር እንደገና  ሠላም ለምወድህ  እንዲህም እንዲህም  የንብ አውራ መሳይ  ሳብዬየሚሉ ዜማዎቿ ለአብነት ይጠቀሳሉ። “ማንጠግቦሽ” ተሰኘ ሙዚቃዊ ድራማም አላት፡፡ ከጥላሁን ገሠሠ፣ ከፍሬው ኃይሉ ከአሰፋ አባተ ፣ ከተማ መኮንን ፣ አሰፋ ሀይሌ ፣ ታጠቅ ገብረወልድ እና ከሌሎችም ታዋቂ ዘፋኞች ጋር በህብረት የዘፈነቻቸው በርካታ ስራዎች አሏት። በውዝዋዜ ረገድም ከነ ሙናዬ መንበሩ፣ ዘነበች ታደሰ እና ሌሎችም ጋር የሀገር ፍቅር ቴአትር ቤት መድረክን አድምቃለች። ታዳሚውን አስደስታለች። በሙያዋ ከሌሎች አርቲስቶች ጋር የተለያዩ አገራት በመሄድ ሙዚቃዎችን፣ ትርኢቶችንና ባህላዊ ውዝዋዜዎችን አሳይታለች። ለአፍሪካ አንድነት ድርጅት(አፍሪካ ህብረትም) ቀደም ሲል ከጓደኞቿ ጋር ህብረ ዝማሬ ሰርታለች፡፡ አሰለፈች ድምፃዊ ፣ ተወዛዋዥ እና ተዋናይ ከመሆኗም ባሻገር ግጥም እና ዜማ ትደርሳለች፡፡


  
  በሀገር ፍቅር ቆይታዋ በርካታ ስራዎችን የሰራችው አርቲስት አሰለፈች ለንጉሱ ፣ ለግርማዊት እቴጌ መነን እና ለውጪ መሪዎች በልዩ ልዩ በዓላት ወቅት አበባ እና ሌሎች ስጦታዎችን ታቀርብም ነበር፡፡ ንጉሱም በተለያዩ ጊዜያት ልዩ ልዩ ሽልማቶችን አበርክተውላታል፡፡ በ1937ዓ.ም ጅሩ ተወልዳ አዲስ አበባ ያደገችው አሰለፈች አሽኔ በተለያዩ የአለም ሀገራትም ስራዎቿን አቅርባለች፡፡ በአንድ ወቅትም በአሜሪካ ቆይታዋ ለፕሬዚዳንት ጆርጅ ቡሽ ደብዳቤ ፅፋ ከፕሬዚዳንቱም ለፃፈቻ ደብዳቤ ምላሽ ተሰጥቷታል፡፡ ከስፖርት እግር ኳስ እና ሩጫን ትወዳለች፡፡ ቀደም ባለው ጊዜም የቅድስ ጊዮርጊስ ክለብ ደጋፊ ነበረች፡፡ በሩጫው አለም እነ አበበ ቢቂላ ፣ ሀይሌ ገ/ስላሴ ፣ ደራርቱ ቱሉ ፣ ጥሩነሽ እና ገንዘቤ ዲባባን እንደምታደንቅም ገልፃለች፡፡


  በ1947 , በሀገር ፍቅር ቴአትር ስራን አሀዱ ያለችው አርቲስት አሰለፈች አሽኔ፤ በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ ብሄራዊ የኪነጥበብ ማዕከል ጥላ ስር ሆና ደጋፊ አጥተዉ የሚገኙትን አንጋፋሞያ ባልደረቦችዋን በመርዳት ላይ ትገኛለች፡፡  ረጅም እድሜ እና ጤና በመመኘት መረጃዬ በዚሁ አበቃሁ ቀሪውን እናንተ ጨምሩበት ….

Monday, September 26, 2016

መስቀል በጉራጌ.... !!!

  
                 የመስቀል በዓል በጉራጌ ብሔረሰብ ያለው ማህበራዊ ፋይዳ

  የመስቀል በዓል አጀማመር መሰረት የሆነው የእየሱስ ክርስቶስ መስቀል መገኘት ጋር የተያይዘ ሲሆን ከአራተኛው መቶ ክፍለ ዘመን ማለትም ከንግስት እሌኒ አገዛዝ ዘመን ጀምሮ እንደሚከበር የታሪክ ድርሳናት ያስረዳሉ፡፡ እየሱስ ክርስቶስ የተሰቀለበትን መስቀል በጠፋበት ወቅት የነበረችው ንግስት እሌኒ መስቀሉን ለመፈለግ በተነሳችበት ወቅት አንድ ባህታዊ ‹‹በራዕይ ተገልፆልኛል የእየሱስ ክርስቶስ መስቀል ለማግኘት ደመራ አስደምረሽ /እንጨት አስከምረሽ/ በእሳት ሲቀጣጠል ጭሱ መስቀሉ ወዳለበት ቦታ ይመራሻል ከዚያም በኃላ አስቆፍረሽ ታወጪዋለሽ» አላት፡፡ በተባለው መሠረት ንግስት እሌኒ መስቀሉን ፍለጋ ቁፋሮ መስከረም 17 ጀምራ ከ6-7 ወራት ፈጅቶ መጋቢት 10 መስቀሉ ተገኘ፡፡

    በዚህ መሰረት መስቀሉ ከተገኘበት ጊዜ ጀምሮ በየዓመቱ መስከረም 17 ቀን የደመራ ስነ ስርዓት በማካሄድ ይዘከራል፡፡  ይህ ታላቅ በዓል በሁሉም የኢትዩጵያ ብሔር ብሄረሰቦችና ህዝቦች ባህል፣ አኗኗርና ወግ በተላበሰ መልኩ የሚከበር ቢሆንም የበዓሉ አከባበር ደረጃና የሚሰጠው ትኩረት ከቦታ ቦታ ይለያያል፡፡ በጉራጌ ብሔረሰብ ዘንድ በድምቀት ከሚያከብራቸው በዓላት መካከል ትልቁና ዋንኛው የመስቀል በዓል ነው፡፡
     

ዓመቱን ሙሉ ተለያይተው የኖሩ ቤተሠቦችና ዘመዳሞች የሚገናኙበት፣ የሚጠያየቁበት፣ ማህበራዊ ችግሮቻቸው የሚፈቱበት፣ ወጣቶች የሚተጫጩበት፣ በጋብቻ የተሳሰሩ ቤተሠቦች የሚጠያየቁበት፣ በጥል የተለያዩ ባልና ሚስቶች የተጣሉ ሠዎች የሚታረቁበት፣ እዳ የሚሠረዝበትና በዳይና ተበዳይ ይቅር የሚባባሉበት በዓል ነው፡፡ ወጣቶችና አዛውንት ደመራ ለማብራት በወጡበት በእድር ደንቦች በአካባቢ ልማት፣ በግብርናና ንግድ ስራዎች ላይ የሚመክሩበት፣ ወጣቶች በአባቶች የሚመረቁት፣ ጎልማሶች ከአባቶች ኃላፊነት የሚረከቡት፣የወላድ ማህፀን የሚባረከው፣ ሟርተኞች የሚረገሙት በዚሁ በዓል ነው፡፡ ወላጆች ለበዓሉ የተዘጋጀን ሰንጋ ከፊታቸው አቁመው ሻኛውን በመዳሰስ ትውልዱን ይመርቃሉ /ይባርካሉ/፤ ለአገር ሰላምና ብልፅግና ፈጣሪያቸውን በፀሎት ይለምናሉ፡፡ በጐረቤት እና በአካባቢ ያለን ችግረኛ የሚያስቡበት፣ ለወለደች አራስ የሸሉዳ ስጋ፣ ለተገረዙ ልጆች ጭቅና ስጋ የሚሰጡበት በመስቀል በዓል ነው፡፡

      ከመስከረም 16 ጀምሮ እስከ ጥቅምት 5 ድረስ ባህለዊ የአዳብና ጨዋታ በተለያዩ የገበያ ስፍራዎችና የጋራ መሠብሠቢያ ቦታዎች በሚኖረው የዘፈንና ጭፈራ ትዕይንቶች በመሳተፍ ወጣት ወንዶችና ሴቶች ሎሚና ብርቱካን የሸንኮራ አገዳ በመለዋወጥ ጓደኛ የሚመርጡበትና መጻሂ ህይወታቸውን መሰረት የሚጥሉበትና የሚወስኑበት በዓል ነው፡፡ በአዲሱ ዓመት የሚሠሩ ስራዎች ተለይተው እንዴት መሠራት እንዳለባቸው የሚመከርበትና የሚታቀድበት በመሆኑ ማህበራዊ ፋይዳው እጅግ የላቀ ነው፡፡

      መስቀል በጉራጌ ብሔረሠብ ዘንድ ትልቅ በዓል እንደመሆኑ መጠን ዝግጅቱም እንዲሁ ከበድ ያለ ነው፡፡ የመስቀል በዓል ዝግጅት የሚጀምረው መስቀል በተከበረበት ዓመት /መስቀል እንዳለቀ ለሚቀጥለው በዓል አከባበር ማሠብ ይጀመራል፡፡በዚህም መሠረት ከትውልድ ቀዬያቸው ርቀው የሚኖሩ የብሔረሰቡ ተወላጆች ከትንሽ እስከ ትልቅ ገቢ ያላቸውንም ጨምሮ ለመስቀል በዓል ማሰብ የሚጀምሩትና ገንዘብ የሚያጠራቅሙት ከጥቅምት ወር ጀምሮ ነው፡፡ በአገር ቤት የሚኖሩ ሴቶች የመስቀልን በዓል ለማክበር ቅቤ ማጠራቀም የሚጀምሩበት ወዲያው መስቀል እንደወጣ ነው፡፡ መስቀል ሶስትና አራት ወራት ገደማ ሲቀሩት ዝግጅቱ እየተጧጧፈ ይሄዳል፡፡

      በዚህ ወቅት የሥራ ክፍፍሉ በዕድሜና በፆታ እንደየ አቅሙና ችሎታው ይሠጣል፡፡ የልጆችና የወጣቶች ወንዶች የስራ ድርሻ ለመስቀል በዓል ዝግጅት የሚሆን ፍልጥ እንጨት ማዘጋጀት፤ አባወራዎች ለዕርድ የሚቀርቡ ሰንጋዎች ማድለብና ማዘጋጀት እና በመስቀል በዓል ወቅት ከብቶች የሚበሉትን የሳር ድርቆሽ የማዘጋጀትና ክልክል የሳር ቦታዎች መከለል እንዲሁም የተለያዩ ደረጃ ያላቸወ ቢላዋዎች ማዘጋጀት ናቸው፡፡ የወጣት ሴቶች የሰራ ድረሻ ደግሞ ቤት ማሳመር /የተለያዩ ቀለም ባላቸው አፈሮች ቤት መቀባት ሲሆን እማወራዎች በቅድሚያ እንሰት ፍቀው ያዘጋጃሉ፣ ጅባ ይሰራሉ /ይገዛሉ/ ለክትፎ ግብዓት የሆኑት እንደ ቂቤ፣ ሚጥሚጣ ያዘጋጃሉ፡፡ ከነሐሴ 12 /ከቡሄ/ ጀመሮ ዝግጅቱ እንደገና በአዱስ መልክ ተጠናክሮ ይከናወናል፡፡ ምክንያቱም መስቀል ደርሷልና ነው፡፡

      ለምሳሌ የመስቀል ደመራ ይደመራል፣ ወጣት ወንዶች የመስቀል እንጨት ጫካ ሄደው መፍለጥና ማዘጋጀት የማጀምሩት ከቡሄ ጀምሮ እንደሆነና ሌሎች ማንኛውም ነገሮች ሁሉ በትጋትና ንቃት ይከናወናሉ፡፡ መስቀል በጉራጌ አስቀድሞ ሰፊ ቅድመ ዝግጅት ከተደረገበት በኃላ በዓሉ ከመስከረም 12 እስከ ጥቅምት 5 ድረስ ለበዓሉ ተብሎ የተዘጋጀ ባህላዊ ምግቦችና መጠጦች እየተጠቀሙ በታላቅ ደስታና ጭፈራ እንዲሁም ልዩ ልዩ ክንዋኔዎችን በማካሄድ የሚከበረ ሲሆን የቀናቶቹ ስያሜና የሚካሄዱ ትባራት እንደሚከተለው ይሆናል፡፡

መስከረም 13 ወሬት የኸና

     በመስቀል በዓል ለምግብ ማቅረቢያነት የሚውሉ ቁሳቁሶች ከየግድግዳው የሚወርዱበት ቀን ነው፡፡ የቤት መገልገያ ቁሳቁሶች በጥንቃቄ ፀድተው እስከ ጥቅምት 5 ድረስ በምግብ ማቅረቢያነት ያገለግላሉ፡፡በተጨማሪያም ሁሉም ቤቱን አፅድቶ አዳዲስ ጅባዎች አነጣጥፎ መስቀልን ለማክበር ዝግጅት የሚጠናቀቅበት ዕለት ነው፡፡

መስከረም 14 ደንጌሳት /የዴጚያ እሳት(ይፍት)

     ለሁሉም የቤተሰብ አባል በተዘጋጀለት የሸክላ ጣባት የጐመን ክትፎ የሚበላበት ቀን ነው፡፡ የዚህ ቀን ሙሉ ወጪ የሚሸፍኑት ሴቶች ናቸው፡፡ በዚህ ዕለት ማታ በየደጃፉ በልጆች የተደመሩ ዳመራዎች የሚቃጠሉበት ቀን ሲሆን በብሔረሰቡ አጠራር የዴጚያ ኧሳት (የባዮች ኧሳት ቀነ) ይባላል፡፡ ስለሆነም ዳመራው ሲቃጠል ጎረ ጎረ ፣ ጎረ ጎረ... እያሉ ፈጣሪን ለዚህ እለት ላደረስከን ብለው ሲያመሰግኑ ሴቶች ደግሞ በእልልታ ያደምቁታል፡፡

መስከረም 15 ወኸመያ /ጨርቆስ/ የእርድ ማይ/

    በጉራጌ ብሔረሰብ ዘንድ ዋናው የመስቀል በዓል የሚከበርበት በእዚህ ዕለት ነው፡፡ በዕለቱም የአባወራዎች ተግባር ጐልቶ የሚታይበት ሆኖ እያንዳንዱ የቤተሰብ አባል ሁለትና ከዚያ በላይ በመሆን የደለበ ሰንጋ የሚያርድበት ዕለት ነው፡፡ በዚህ ዕለት ስጋውን ወንድየው እንዳስገባ ጥሬ ስጋ በቅቤ በመንከር (ጨፉየ) ቀጥሎም ተወዳጁ የጉራጌ ክትፎ ይበላል፡፡


መስከረም 16 ያባንዳ እሳት/ የጉርዝ እሳት

    ዋናው መስቀልና ትልቁ /የአባቶች/ ዳመራ የሚበራበት ዕለት ሲሆን በአብዛኛው ሀይማኖታዊ ይዘት ይላበሳል፡፡ ወጣት ወንዶችና ሴቶች ቤተክርስቲያን ሄደው ባህላዊ ጭፈራ "አዳብና" የሚጨፍሩበትና ሀይማኖታዊ ሥርዓት የተከተለ ዳመራ የሚቃጠልበት ቀን ነው፡፡ ወጣቶቹ ከጭፈራ ቦታቸው ወደ ቤት ከተመለሱ በኃላ ወደ ማታ አካባቢ ዋናው ዳመራ በየአካባቢው ይቃጠላል፡፡ በዳመራው ስርም ባህላዊ ጭፈራ ይደምቃል፣ ይጠጣል፡፡ ከዚህ ሁነት በኃላ ሁሉም ወደ ቤቱ ገብቶ በተዘጋጀለት ጣባ ክትፎ ይበላል፡፡

መስከረም 17 ንቅ ባር/ የከሠል ማይ

ከለሊቱ 12 ሰዓት ጀምሮ በአንድ አጥቢያ የሚተዳደሩ ዕድርተኞች ዳመራ ወደ ተቃጠለበት ቦታ በመሰብሰብ ቃለ መሀላ በማስገባት አዲስ የአካባቢ ዳኛ የሚሾምበትና ያለፈው ርክክብ የሚያደርግበት፣ አዲስ የአባልነት ጥያቄ የሚቀርብበትና ምዘግባ የሚካሔድበት ዕለት ነው፡፡


መስከረም 18 የፊቃቆማይ

ሴት ልጃገረዶች የተለያዩ የሥፌት ጌጣ ጌጦች /ዕቃዎች/ ለማዘጋጀት የሚረዳ ሰንደዶ ለቀማ የሚጀመርበት ዕለት ሲሆን በየመንደሩ ልጃገረዶች ባህላዊ ዜማ እያዜሙ ሰንደዶ ለቀማ ያደርጋሉ፡፡

ከመስከረም 17 እስከ መስከረም 23 "የጀወጀ/ የጀወቸ"

አማትና አማች የመጠየቂያ ጊዜ ነው፡፡ ሴት ልጆች ለእናቶቻቸው የፀጉር ቅቤ ለአባቶቻቸው ባርኔጣና ጭራ ሲይዙ ባሎቻቸው ደግሞ ሙክት በመያዝ ይሄዳሉ፡፡ ራሳቸው የአብራካቸው ክፋይ የሆኑትም ልጆቻቸው በወላጆቻቸው የሚመረቁ ሲሆን በጠቅላላ አማቾቻቸው ዘንድ ትልቅ ክብርና ሞገስ ያጐናፅፏቸዋል፡፡

ባህለዊ የመስቀለ በዓል ጨዋታአዳብና

   አዳብና ከመስቀል በዓል ጋር ተያይዞ ከመስከረም 16 እስከ ጥቅምት 5 ባሉት ቀናት ውስጥ በተለያዩ የገበያ ቦታዎችና አቢያተ-ክርስቲያናት የሚከወን የወጣቶች ባህላዊ ጭፈራ ስነ- ስርዓት ነው፡፡ በዚህ ሰነ- ስርዓት ላይ በተለያዩ ምክንያቶች ከየትውልድ ቀዬያቸው ርቀው የቆዩ ዘመድ አዝማዶች፣ አብሮ አደጐች ተገናኝተው ናፍቆታቸው ይወጣሉ፡፡


  ከዚህ በተጨማሪ ክብ እየሰሩ የሚዘፍኑ ወጣት ወንዶችና ሴቶች ዜማና ዳንኪራ በሚደምቀው በዚሁ የአዳብና ጭፈራ ወቅት የትዳር ጓደኛ የመምረጥ ስራ ይከናወናል፡፡ወንዱ ልጅ ለጭፈራ ከወጡት ኮረዳዎች መሀከል ቀልቡ ካረፈባት ልጅ የሎሚ ስጦታ በመስጠት /ወርውሮ/ በመምታት ለትዳር የምትሆነውን ልጅ በባህሉ መሠረት ያጫል፡፡ በአዳብና ከሚከወናወት የተለያዩ ባህለዊ ጨዋታዎች መካከል በወንዶች ብቻ የሚከወን የዝላይ ትዕይንትም አለ፡፡ሌላው የሙየቶች ክዋኔ ጥበብ አንዱ ነው፡፡ ሙየቶች ለአዳብና ጭፈራ ከሚወጣው የክዋኔው ታዳሚ ለየት ያለ ቋንቋ፣ ዜማና ዳንኪራ ያለው ክዋኔ ጥበብ የሚያቀርቡ ማህበረሠብ ሲሆኑ ወደ አናታቸው በአደይ አበባ የተሽቆጠቆጡ ልምጭ ይዘው መሪያቸውን እየተከተሉ ሲያዜሙና ሲጨፍሩ ይስተዋላሉ፡፡

     በአጠቃላይ በመስቀል ወቅት የሚከናወኑ ባህላዊ መስተጋብሮችና ትዕይንት ለዞኑ ቱሪዝም እድገት ትልቅ ሀብት ነው፡፡ በዞኑ በአለም ቅርስነት ከተመዘገበው ጢያ ትክለ ድንጋይ ጀምሮ የጊቤ ሸለቆ ብሔራዊ ፖርክ፣ ጥንታዊና ታሪካዊ ገዳማትና መስጅዶች እንደሁም ውብና ማራኪ የሆኑ መልክአ ምድሮችን የያዘውን ጉራጌ ዞን የመጐብኘት አድል ይፈጥራል፡፡