Tuesday, May 26, 2015

አርቲስት ሻምበል መኮንን መርሻ ከዚህ አለም በሞት ተለዩ



   አንጋፋው የፖሊስ ኦርኬስትራ ሙዚቀኛ የነበሩት ሻምበል መኮንን መርሻ ትላንት ከዚህ አለም በሞት ተለይተዋል።አርቲስቱ በ1950ዎቹ መባቻ የፖሊስ ኦርኬስትራን ተቀላቅለው በሙዚቃው ከግማሽ ምዕተ አመት በላይ አሳልፈዋል፡፡ አርቲስቱ የታዋቂ ድምፃውያንን ሙዚቃ በመድረክ በማጀብ እና በካሴት በማቀነባበር ለሀገራችን የሙዚቃ እድገት የበኩላቸውን ድርሻ ተወጥተዋል፡፡


    ጥላሁን ገሰሰ ፣ አለማየሁ እሸቴ ፣ ሂሩት በቀለ ፣ ዘሪቱ ጌታሁን እና ታደለ በቀለን የመሳሰሉ አንጋፋ ድምፃውያንን በትራንፔት በማጀብ ተወዳጅነትን አትርፈዋል፡፡ ሻምበል መኮንን መርሻ በመድረክ ላይ ከሚያሳዩት ድንቅ የትራንፔት አጨዋወት ባለፈ ኦሮምኛ ሙዚቃን በመጫወትም በ1950ዎቹ ስመ ገናና ድምፃዊ ነበሩ፡፡

   
   አንጋፋው የፖሊስ ኦርኬስትራ ሙዚቀኛ ሻምበል መኮንን መርሻ የቀብር ስነ ስርዓት ዛሬ በቂርቆስ ቤተክርስቲያን ቤተሰቦቻቸው ፣ ወዳጅ ዘመዶቻቸው እና አድናቂዎቻቸው በተገኙበት ተፈፅሟል፡፡      

Saturday, May 23, 2015

የአበጋር የግጭት አፈታት ስነ ስርዓት...


  አበጋር ማለት ባህላዊ የግጭት መፍቻ ስርአቱ ተቋም መጠሪያ ስያሜ እና የዳኛነት ስርአቱን የሚከውኑ ግለሰቦች የማዕረግ ስም ነው፡፡ አበጋር በሚኖሩበት አካባቢ ማህበረሰብ ውስጥ የሚከሰቱ የተለያዩ ግጭቶችን የመፍታትና የማስታረቅ ስልጣንና ይሁንታ ያገኙ ሰዎችን የያዘ ተቋም ነው፡፡ ተቋሙ ከአነስተኛ ግጭት እስከ ከፍተኛው የግድያ ወንጀል ድረስ ያሉ ግጭቶችን በየደረጃው የመፍታት ስልጣን አለው፡፡ ይህ ተቋም ወንዶች ብቻ የሚሳተፉበት ነው፡፡
  
  አበጋርነት ማዕረግ በሁለት መንገድ ይገኛል፡፡ የመጀመሪያው ከዘር የሚወረስ ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ በመመረጥ ይገኛል፡፡ በዘር የሚገኘው አበጋርነት ከጥንት ጀምሮ ከአባት ወደ ወንድ ልጅ በቅብብሎሽ የሚወረስ ነው፡፡ ወንድ ልጅ የሌለው አበጋር ለሴት ልጁ ማውረስ አይችልም፡፡ ነገር ግን አበጋሩ ለመረጠው የወንድሙ ወይም ለእህቱ ወንድ ልጅ ማውረስ ይችላል፡፡  አበጋሩ የሚተካውን አካል የመምረጥ እና የማብቃት እንዲሁም እድሜው መድረሱን ያረጋግጣል፤ ተተኪው አበጋር የማመዛዘን ብስለቱ እንዲያድግ እና ትክክለኛ ፍርድ እንዲሰጥ እድሜው 30 እና ከዚያ በላይ መሆን ይኖርበታል፡፡

  ሁለተኛው የአበጋርነት ማዕረግ ደግሞ በመመረጥ የሚገኝ ነው፡፡ ከአካባቢው ማህበረሰብ መካከል ተደማጭነት ፣ ተቀባይነት ፣ የሚከበር እና ተግባቢነት ያለውን ግለሰብ ማህበረሰቡ በመምረጥ እና በመሰየም የሚሰጠው ማዕረግ ነው፡፡ የተመረጠው አበጋር በተለያዩ ሁኔታዎች የተሰጠውን ኃላፊነት በአግባቡ መወጣት ካልቻለ ሌላ የመምረጥመ ሆነ የመተካት ስልጣን ያለው የአካባቢው ማህበረሰብ ነው፡፡ በዘር እንደሚገኘው የአበጋርነት ማዕረግ ለወንድ ልጁ ወይም ለሌላ አካል ስልጣኑን ማውረስ ወይም ማስተላለፍ አይችልም፡፡

  አበጋር የሰላም አባቶች ናቸው፡፡ ደም የተቃባን ያስታርቃሉ ፣ ደም ያደርቃሉ፡፡ አብዛኛው የወሎ ህዝብም የሀይማኖት ልዩነት ሳይገድበው በአበጋር ይዳኛል፡፡ አበጋሮች /ሽማግሌዎች/ የሟች እና የገዳይን ቤተሰብ ያቀራርባሉ፡፡ የአበጋርን የሰላም ፣ የእርቅ ጥሪ አልቀበልም የሚል አይኖርም ፤ ቢኖርም ከህብረተሰቡ ይገለላል፡፡ የአበጋር የእርቅ ስነ ስርዓት በሁሉም ህብረተሰብ ይከበራል፡፡ በአጠቃላይ አበጋር የዘመመ ጎጆን ፣ የፈረሰ ትዳርን ያቃናል፡፡


  አበጋርም ሆነ ሌሎች  ባህላዊ ዳኝነቶች እና የእርቅ ስነ ስርዓቶች ሊጎለብቱ እና ሊያድጉ ይገባል፤ ምክንያቱም ዘመናዊውን የፍትህ ስርዓት ያግዛሉና፡፡

   ምንጭ ፡-  በባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር የቋንቋና የባህል እሴቶች ልማት ዳይሬክቶሬት

Wednesday, May 20, 2015

የዘፈን ግጥም ደራሲ ይልማ ገብረአብ ስራዎች እና የህይወት ተሞክሮ……

  ብልህ ስንኝ ቋጣሪ ፣ ትጉህ ቃላት ቀማሪ በመሆን በኢትዮጵያ የሙዚቃ ኢንዱስትሪ ውስጥ በሙዚቃ ግጥም ድርሰቱ በኩል የድርሻውን እየተወጣ የሚገኝ ታላቅ የጥበብ ሰው ነው፡፡ በሙዚቃ ውስጥ የዚህን ሰው ግጥም ያላቀነቀነ ድምፃዊ ፣ በሙዚቃ መሳሪያ ያላጀበ ሙዚቀኛ ፣ የእሱን የሙዚቃ ግጥም ከዜማ ጋር ያላዋሀደ አቀናባሪ ፣ የእሱን ግጥም በዜማ ያልቀመመ የዜማ ደራሲ ፣ የእሱን ስራ የያዘ በካሴት ክርም ሆነ በሲዲ ያላሳተሙ ሙዚቃ ቤቶች ቢኖሩ እንኳን በጣት የሚቆጠሩ ናቸው፡፡ አርቲስት ይልማ ገብረአብ፡፡

     የዘፈን ግጥም ደራሲ ይልማ ገብረአብ የጥበብ ጀማሬው በቀበሌ ኪነት ውስጥ ይሁን እንጂ የፅሁፍ ዝንባሌው የመጣው ብርሃን ኢትዮጵያ አንደኛ ደረጃ ት/ቤት በሚማርበት ወቅት ነው፡፡ ለጓደኞቹ እና ለራሱ የፍቅር ደብዳቤ በመፃፍ፡፡ በልጅነቱ የቄስ ትምህርት የተማረው አርቲስት ይልማ ገብረአብ አንደኛ ደረጃ ትምህርቱን በብርሃን ኢትዮጵያ ፣ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን ደግሞ በዳግማዊ ምኒሊክ ት/ቤት አጠናቋል፡፡ ቀደም ባለው ጊዜ ቤተሰቦቹ በከፈቱት “ዋዜማ” የተሰኘ ምሽት ቤት /ናይት ክለብ/ እነ ክቡር ዶክተር አሊ ቢራ ፣ ተሾመ ደምሴ እና አያሌው መስፍንን በማየት እሱም ክራር እና ጊታር የመሳሰሉትን የሙዚቃ መሳሪያዎች በመጫወት ወደ ሙዚቃው አለም ገባ፡፡
   በ1974ዓ.ም “ይረገም” የተሰኘውን የመጀመሪያ የግጥም ስራ ድርሰቱን ለአንጋፋው ድምፃዊ ሙሉቀን መለሰ ሰጥቷል፡፡ ይህ ዘፈን ከራሱ ህይወት ጋር የተገናኘ ሲሆን በጊዜው የፍቅር ጓደኛው የነበረችውን አይናለምን “ያይኔ ነገርማ……” በማለት በቅኔ ያወሳበት ስራው ነው፡፡ ለዚህ ስራው 250 ብር ተከፍሎታል፡፡ ክፍያው ተቀጥሮ ከሚያገኘው ደሞዝ 80 ብር ማለት ነው በእጅጉ የላቀ እና የመጀመሪያው  በመሆኑም አርቲስቱ በጣም ነበር የተገረመው፡፡  ከዚያ በኋላም ድምፃዊ ኤፍሬም ታምሩ “ተሰናብታኝ” የተሰኘውን ካሴቱን ሲያወጣ (ተሰናብታኝ ፣ ሸግዬ ፣ እና አንድ ሌላ ስራም ሰርቶለታል) ለዚህም 90 ብር ነበርና የተከፈለው ፤ ከሙሉቀን ክፍያ ጋር አነፃፅሮ ግር ተሰኝቶ ነበር፡፡
    
    ድምፃዊት አስቴር አወቀ የተጫወተችው “ጣፋጭ ብርቱካኔ ነህ የኔ ወለላ…..”  የይልማ ገብረአብ ግጥም ሲሆን ዜማው ደግሞ የራሷ የአስቴር አወቀ ነው፡፡ በዚህ ስራዋም በአህጉር አቀፍ ደረጃ ተሸላሚ ሆናበታለች፡፡ ከዚህ በኋላም እስካሁን ድረስ ለ105 ድምፃውያን ወደ1800 የሚደርሱ የዘፈን ግጥሞችን ደርሷል፡፡ ዜማ ድርስት ብዙ አይደለሁም የሚለው አርቲስት ይልማ ገብረአብ በራሱ ጥቂትም ቢሆኑ ግጥም እና ዜማ የሰራቸው ዘፈኖች አሉት፡፡ ለአብነት ለአረጋኸኝ ወራሽ - ተነስ በል ልቤ ፣ ለምስራቅ ታዬ ፣ እንዲሁም ለመስፍን አበበ - ርግቤ እና ሌሎችንም ሰርቷል፡፡ በተለይ ርግቤ የተሰኘው ስራ ከመጀመሪያ የፍቅር ጓደኛው ከአይናለም ለተወለደችው ልጁ የተሰራ ነው፡፡


   ተወዳጁ አርቲስት ቴዎድሮስ ካሳሁን /ቴዲ አፍሮ/ ለአርቲስት ይልማ ገብረአብ “የወርቅ ብዕር” 40 ሺ ያህል ታዳሚ በተገኘበት ሸልሞታል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም በቅርቡ ድሬ ቲዩብ ባዘጋጀው የኪነ ጥበብ ባለሙያዎች ሽልማት ላይም “የምንጊዜም የዘፈን ግጥም ደራሲ” ተብሎ ተሸልሟል፡፡ ሽልማቶቹ በቀጣይም በሙዚቃው ዘርፍ የተሸለ ስራ እንዲሰራ የሚያበረታቱ ናቸው፡፡ በነገራችን ላይ “ፀባየ- ሰናይ” የሚለው የቴዲ አፍሮ ዘፈን ግጥሙ የይልማ ገብረአብ ነው፡፡


  አርቲስቱ የተለያዩ ርዕሰ ጉዳዮችን በግጥሞቹ የዳሰሰ ሲሆን ኢትዮጵያዊነትን የሚገልፁ ፣ ባህልን የሚያንፀባርቁ ተወዳጅ የባህል ስራዎችንም ደርሷል፡፡ ለአብነትም ፡- ለአስናቀች ወርቁ ፣ ተሾመ አሰግድ ፣ ራሄል ዮሀንስ እና ባህሩ ቀኜ የደረሳቸውን ሙዚቃዎች መጥቀስ ይቻላል፡፡ አርቲስት ይልማ ገብረአብ ለኤፍሬም ታምሩ 71 ለአረጋኸኝ ወራሽ ደግሞ 90 ያህል ስራዎችን ደርሷል፡፡ ቀሪዎቹ ስራዎቹም በአንጋፋ እና ወጣት ድምፃውያን ተቀንቅነዋል፡፡ ከዚሁ ጋር ተያይዞም ከአዲስ አበባ እና ጅማ ዩኒቨርስቲዎች የተለያዩ ምሁራን ጥናቶች አድርገውባቸዋል፡፡ የመመረቂያ ፅሁፍም ተፅፎባቸዋል፡፡

አርቲስት ይልማ ገብረአብ ለእነማን ምን ሰጠ የሚለውን በጥቂቱ እንመልከት፡-

1.  ለክቡር ዶ/ር ጥላሁን ገሰሰ - አንቺ ልጅ ጎፈሬ ፣ እንቆቅልሽ ፣ በይ እንጓዝ (ከብዙነሽ በቀለ ጋር)
2.  ለትዝታው ንጉስ ለመሀሙድ አህመድ - በርከት ያሉ የትዝታ ስራዎች ፣ ያገር ቤቷ ፣ ልኑርበት ፣ ስንቱን አስታወስኩት ፣ ሙዚቃ ደግነሽ ፣ አደራ (ከጎሳዬ ተስፋዬ ጋር)
3.  ለኤፍሬም ታምሩ - ልመደው ፣ ካጓጓዘኝ ፣ ጎዳናዬ ፣ ጀመረኝ ፣ ቢልልኝ ፣ እንደ ገብሱ ዛላ ፣ ሰው መሰረቱ ፣ ሞሽሩት በዝና እና ሌሎችም …..
4.  ለአስቴር አወቀ  ሁለት ሙሉ አልበም ሰርቶላታል፡፡ - ነህ የኔ ወለላ ጣፋጭ ብርቱካኔ ፣ እኔን እንጂ ገላ ፣ አመሰግናለሁ ፣ ሙዚቃ ፣ ብርዱ አልተስማማኝም….
5.  ለቴዎድሮስ ታደሰ - እየቆረቆረኝ ፣ በመላ በሰበብ ፣ ከተስማማሽ ፣ በመዋደዳችን ፣ ልደሰት በወዜ ፣ እምዬ ኢትዮጵያ……
6.  ለፀጋዬ እሸቱ  -  ያንተ ያለህ ፣ ዘምናኒት ፣ አባጃልዬ ፣ ተጓዥ ባይኔ ላይ ….. ከእነዚህም በተጨማሪ ለሀመልማል አባተ ፣ ለነዋይ ደበበ ፣ ለአሰፉ ደባልቄ ፣ ለኬኔዲ መንገሻ ፣ ለተፈራ ነጋሽ ፣ ለብዙነሽ እና ሂሩት በቀለ ፣ ለአስናቀች ወርቁ ፣ ባህሩ ቀኜ ፣ ለተሾመ አሰግድ ፣ ለራሄል ዮሀንስ ፣ ለማሪቱ ለገሰ ፣ ለጋሻው አዳል (እሪኩም) ፣ ለኩኩ ሰብስቤ -  9 ያህል የትዝታዎች ስራዎችን ሰርቷል፡፡ በቅርብ ከወጡት ደግሞ ለማዲንጎ አፍወርቅ ፣ ለዮሴፍ ገብሬ (ጆሲ) ፣ ለጃኖ ባንድ - “አይራቅ” ን ሲሰራ ወደፊት የሚወጡም እሱ የሰራቸው በርካታ የግጥም ድርሰቶች አሉት፡፡  መላ በሉ(ለኤች አይ ቪ) እና አሽከርክር ረጋ ብለህ (ለትራፊክ አደጋ) እንዲሁም ሌሎች በቡድን /በጋራ/ የተሰሩ የሙዚቃ ግጥሞችንም ለአድናቂዎቹ አበርክቷል፡፡ የዚህ አንጋፋ የጥበብ ሰው ስራዎች በአንድ ጀንበር የሚያልቁ አይድለምና እኔ በዚሁ ላብቃ ፡፡ የቀረውን እናንተ ጨምሩበት…… እድሜ ከጤና ጋር ተመኝቻለሁ፡፡