Sunday, July 19, 2015

ቀራፂ፣ አዝማሪ፣ ባለቅኔ ፣ ነጋዴ፣ የመኪና ጠጋኝና ሹፌር …. ነጋድራስ ተሰማ እሸቴ



   የመጀመሪያው ሙዚቃን በሸክላ ያስቀረፁ እና ህጋዊ መንጃ ፍቃድ በመያዝ (ከጀርመን ሀገር) የመጀመሪያው ኢትዮጵያዊ መኪና አሽከርካሪ /ሹፌር/ ናቸው፡፡ በኢትዮጵያ የሙዚቃ ታሪክ (Recording History) ሸክላ የተቀረፀ የመጀመሪያው ዜማ የነጋድራስ ተሰማ እሸቴ ስራዋች ሲሆኑ ዘመኑም በአጤ ምኒልክ ዘመነ መንግስረት ነበር( እ.ኤ.አ 1910) ፡፡



  በ1900ዓ.ም ሙሴ ሆልስ የተባሉ ጀርመናዊ በኢትዮጵያ ለብዙ ጊዜ ከቆዩ በኋላ ወደ ሀገራቸው ሲመለሱ አፄ ምኒልክን በተሰናበቱበት ጊዜ ጀርመን ሀገር ወስደው የሚያስተምሯቸው ሶስት ወጣቶች እንዲሰጧቸው ስለ ጠየቋቸው እና ነጋድራስ ተሰማ እሸቴም በጥሩ ሰዓሊነታቸው በቤተ መንግስቱ ስለ ታወቁ “ያ ተሰማ እሸቴ እጁ ብልህ ነውና መኪና መንዳት እና መጠገን እንዲማር እሱ ይኺድ” ብለው አፄ ምኒልክ ስለ ወሰኑ ወደ ጀርመን አገር ሄደው ለሁለት አመት ተኩል ያህል የአውቶሞቢልን አሰራር ለመማር ችለዋል፡፡



  ነጋድራስ ተሰማ እሸቴ መስንቆ መምታት እና ዜማ ካባታቸው ተምረው ስለነበር ወደ ጀርመን ሄደው በቆዩበት ጊዜ የተላኩበትን የሹፌርነት እና የመካኒክነት ትምህርት አጠናቀው አጥጋቢ ውጤት ከማምጣታቸውም በላይ የመጀመሪያውን የአማርኛ ዜማ በሸክላ ለማስቀረፅ በቅተዋል፡፡ በጀርመን ቆይታቸው ወቅት “ሂዝ ማስተርስ ቮይስ” የተባለው የጀርመን የሙዚቃ ድርጅት ጠይቋቸው የኢትዮጵያ መዲና እና ዘለሰኛ ዜማዎችን በ17 አይነት ስልት እየተጫወቱ ተቀርፀዋል፡፡ ኩባንያው የተሰማ እሸቴን ዜማዎች በ17 ሸክላዎች የቀረፀ ሲሆን ለዜማው ባለቤት የድካም ዋጋ እንዲሆን በወቅቱ 17ሺህ የጀርመን ማርክ ከፍሏቸዋል፡፡

   በዘመኑ ብቻ ሳይሆን በሀገራችን አሁንም እነዚህ የነጋድራስ ተሰማ እሸቴ ብርቅዬ ሸክላዎች በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ በኢትዮጵያ ጥናትና ምርምር ተቋም ውስጥ ተሰብስበው ይገኛሉ፡፡ እነዚህ በተቋሙ እጅ ያሉት 16 ያህል ሸክላዎች እያንዳንዳቸው ሁለት ሁለት ዜማዎችን የያዙ ሲሆን በአጠቃላይ 32 ዜማዎች ተቀርፀውባቸዋል፡፡ እያንዳንዱ የሸክላው ገፅ ላይ A ወይም B ተብሎ ተሰይሟል፡፡የዜማው ስምም ተፅፎበታል፡፡ የዜማው ባለቤት ተሰማ እሸቴ ስም አለ ፤ ሸክላው ጀርመን ሀገር መሰራቱ እንዲሁም የሸክላው ቁጥር ተጠቅሷል፡፡

  ሌሎች የአማርኛ ዲስኮች የተቀረፁት ጠላት ኢትዮጵያ ሊገባ ሁለት አመት ያህል ሲቀር ነው፤ የእነ ፈረደ ጎላ ፣ ንጋቷ ከልካይ እና ተሻለ መንግስቱ የዜማ ሸክላዎች ብቅ ያሉት፡፡ እስከዚያ ጊዜ ድረስ ግን የነጋድራስ ተሰማ እሸቴ ሸክላች ከ20 አመት በላይ አቅም ባላቸው ቤተሰቦች ዘንድ በብቸኝነት በግራማፎን ሲደመጡ ቆይተዋል፡፡ ነጋድራስ ተሰማ በዘፈኖቻቸው የአገርና የባንዲራ ፍቅርን ፣ የተቃራኒ ፆታን ፍቅር ፣ ስልጣንን ፣ ጀግንነትን አውድሰውበታል፡፡ ነጋድራስ ተሰማ፣ የመኪና ሹፍርናና የመካኒክነት ሙያን እንዲሰለጥኑ በአፄ ምኒልክ ተመርጠው ወደ ጀርመን አገር በተላኩ ጊዜ ከተላኩበት ሙያ ውጪ በስዕል ፣ በቅርፃ ቅርፅና በሙዚቃ ሙያ በርካታ ስራዎችን ሲሰሩ ቆይተው ወደ አገራቸው ተመልሰዋል፡፡
  ነጋድራስ ተሰማ እሸቴ ከአባታቸው ከአቶ እሸቴ ጉቤ እና ከእናታቸው ከእማሆይ ወለተየስ ሀብቱ ሀምሌ 20 ቀን 1869. ምንጃር ቀርሾ አጥር በተባለው ስፍራ ነው የተወለዱት ፡፡ አባታቸው አቶ እሸቴ የራስ መኮንን ጭፍራ ስለ ነበሩና መስንቆም ስለሚጫወቱ ራስ መኮንንን ተከትለው ወደ ሐረር ሲሄዱ ነጋድራስንም በህፃንነታቸው ይዘዋቸው በመሄዳቸው ያደጉት እና አማርኛ ትምህርታቸውን ያጠናቀቁት በሐረር ነው፡፡ አባታቸው አቶ እሸቴ ሐረር እንዳሉ በመሞታቸው ነጋድራስ ተሰማ በወጣትነት ዕድሜያቸው  ዳግማዊ አፄ ምንሊክን ተከትለው ወደ አዲስ አበባ መጡ፡፡ እኚህ ሰው የኢትዮጵያ ስፖርት ፈርጥ የሆኑት የአቶ ይድነቃቸው አባት ናቸው፡፡


     የመጀመሪያው ኢትዮጵያዊ ቀራፂ፣ ፎቶግራፈር፣ አዝማሪ፣ ባለቅኔ ፣ ሰዓሊ ፣ የፖለቲካ ሰው ፣ ነጋዴና የመኪና ጠጋኝና ሹፌር የሆኑት ነጋድራስ ተሰማ ፣ በዘመናቸው በርካታ አዳዲስ ነገሮችን ለመጀመር ከፍተኛ ፍላጎትና ጉጉት የነበራቸው ሰው ነበሩ፡፡ ከዘፈን ችሎታቸው በተጨማሪ የተለያዩ ስዕሎችንና ቅርፃቅርፆችን በመስራት ለአዳዲስ ሙያዎች ፈር ቀዳጅ እንደሆኑም ይነገራል፡፡ ሃሳባቸውን በነፃነት ለመግለፅና ፊት ለፊት ለመጋፈጥ ደፋር ነበሩ የሚባሉት ነጋድራስ ተሰማ ፣ የቅርፃ ቅርፅ ስራዎች ፣ ስዕሎችና ዘፈን ሀጢያትና ክፉ ስራ እንደሆነ ይታመን በነበረበት በዚያ ዘመን ፣ የፍቅረኛቸውን ምስል በቅርፅ ሠርተውና የተለያዩ የፍቅር ዜማዎችን በማዜም ዘመናቸውን የቀደሙና ሃሳባቸውን በነፃነት ለመግለፅ የደፈሩ ሰው ናቸው፡፡

Wednesday, July 1, 2015

ድምፃዊ ፀዳለ ገብረማሪያም ማን ናት ... ?


    ድምፃዊት ፀዳለ ከድምፃዊነቷ ባሻገር ጥሩ ተወዛዋዥ ናት፡፡ ቫልስ እና ታንጎ የመሳሰሉትን ስትጫወት ደግሞ ከአይን ያውጣሽ ታስብላለች ይላሉ በቅርብ የሚያውቋት፡፡ የሁለት ወንድ ልጆችም እናት ናት፡፡

  ከሀረር ወደ አዲስ አበባ መጥታ አክስቷ ጋር ያደገችው ፀዳለ በአክስቷ አማካኝነት ወ/ሮ አሰገደች አላመራው ሆቴል(ፓትሪስ ሉሙምባ ምሽት ክበብ) ገባች፡፡ በዚሁ ምሽት ክበብ ውዝዋዜ ትሰራ የነበረችው ፀዳለ የተለያዩ ድምፃውያን ስራቸውን ሲያቀርቡ በመስማት እሷም ለራሷ  ታንጎራጉር ጀመር፡፡ ከዚያም በጓደኞቿ አነሳሽነት ወደ ሙዚቃው አለም ገባች፡፡ በወቅቱም የብዙነሽ በቀለን “የሚያስለቅስ ፍቅር” በመጫወት ነው የተቀጠረችው፡፡

  በፓትሪስ ሉሙምባ ቆይታዋ በዳንስ ፣ ውዝዋዜ እና ድምፃዊነት እየሰራች 100ብርም ይከፈላት ነበር፡፡ በፓትሪስ ሉሙምባ ምሽት ክበብ ስትጫወት በተመለከቷት ሻምበል ወንድሙ ዘውዴ እና ድምፃዊ ታምራት ሞላ አማካኝነት ምድር ጦር ኦርኬስትራ በ1958ዓ.ም በሲቪል የዘመናዊ ሙዚቃ ድምፃዊነት ተቀጠረች፡፡ በምድር ጦርም የራሷን የመጀመሪያ ስራ “ካለህበት መጣሁ” የተሰኘ ሙዚቃን ተጫውታለች፡፡ ቀስ በቀስም በርከት ያሉ የአማርኛ እና የሀረር ኦሮምኛ/ቆቱኛ/ ሙዚቃዎችን በግል እና በጋራ አቀንቅናለች፡፡
 
  በግሏ ፡- ካለህበት መጣሁ ፣ ቀለበቴን እንካ ፣ ፍቅር ነው፣ መች ቀረሁ፣ ጨክኜ ፣ የሴቶች ህሊና ፣ አጀቢቱ ፣ ልጆቼን አደራ እና ሌሎችንም ሰርታለች፡፡ በተለይ “ልጆቼን አደራ” የተሰኘው ስራዋ ከራሷ ህይወት ጋር የተገናኘ ሲሆን የግጥሙ ደራሲ ደግሞ ሲራክ ታደሰ ነው፡፡ ከባሏ ጋር በተለያየችበት ወቅት የተጫወተችው ይህ ስራ በግጥሙ ውስጥ የእሷን ህይወት ስለሚያሳይ የተወሰኑትን የዘፈኑን ግጥሞች በጥቂቱ እነሆ፡-
             “መሰረት የሌለው ፍቅርና ቤት
             አይቀርም መፍረሱ ዛሬ አየሁት
             ትቀበለኝ እንደሆን ሀሳቤን
             አደራ እልሃለሁ ልጆቼን፡፡
             ሳምንህ የከዳኸኝ አንተ የጊዜ ሰው
             ትዳራችን ጠፋ ቤታችን ዘጋህው
             እኛም እንለያይ ይበተን ሀብታችን
             እስኪ ለማን ይቅሩ ህፃን ልጆቻችን……”
በጋራ(ከሃብታሙ ሽፈራው) ጋር ፡- ውይይት ፣ ሰመለሌ እና ሌሎች ኦሮሚኛ ዘፈኖችን ተጫውታለች፡፡

    በምድር ጦር ቆይታዋ ከእነ ታምራት ሞላ ፣ አባይ በለጠ ፣ ሀብታሙ ሽፈራው ፣ ጌታቸው አስፋው ፣ ጥላዬ ጨዋቃ እና ሌሎችም ጋር አብራ ሰርታለች፡፡ ከምድር ጦር ኦርኬስትራ ጋርም በተለያዩ የሀገራችን አካባቢዎች በመዘዋወርም ሙዚቃዎቿን አቅርባለች፡፡ ምድር ጦር 270 ብር ይከፈላት ነበር፡፡ በኋላም ዕድገት አግኝታ በ400 ብር ወደ ማዕከላዊ ዕዝ ተዛውራለች፡፡ በዚያ ቆይታዋም ከእነ ብዙነሽ በቀለ ፣ መንበረ ፣  ዘመነ መለሰ እና ሌሎችም ጋር ተጫውታለች፡፡

   ድምፃዊ ፀዳለ ገብረማሪያም ከ1958 - 81 ዓ.ም በምድር ጦር ፣ ከ1981 - 85 ዓ.ም በማዕከላዊ ዕዝ ፣ከ1985 - 2000 ደግሞ በራስ ትያትር በዘመናዊ ሙዚቃ ድምፃዊነት ሰርታለች፡፡ በዚሁ አመትም ጡረታ ወጥታለች፡፡ብዙ ስራዎቿን ግጥም እና ዜማ ይሰሩላት የነበሩት ምድር ጦር በነበረችበት ጊዜ - (ኮለኔል ለማ ደምሰው ፣ ተሾመ ሲሳይ እና ወንድሙ ዘውዴ) ሲሆኑ ማዕከላዊ ዕዝ - (አየለ ማሞ) ራስ ትያትር ደግሞ ሱራፌል አበበ ናቸው፡፡

  ነሀሴ 5,1938 ዓ.ም ሀረር የተወለደችው ድምፃዊት ፀዳለ ገብረማሪያም አሁን በህመም ምክንያት ቤት ውላለች፡፡ ሰርጋችንን ያሞቅንባቸው ፣ ብሶታችንን የረሳንባቸው ፣ ወደ ኋላ በምልሰት ትዝታዎቻችንን ያስታወስንባቸው ፣ አርቲስቶቻችን የህዝብ ሀብት በመሆናቸው ክብር ልንሰጣቸው ይገባል፡፡በችግራቸው ጊዜም ልናስታውሳቸው እና ልንደርስላቸው ያስፈልጋል፡፡