Tuesday, November 15, 2016

አንጋፋው የሙዚቃ አቀናባሪ እና ዜማ ደራሲ ሙሉጌታ አባተ ከዚህ አለም በሞት ተለየ፡፡

 
    በሙዚቃው አለም ሶስት አስር አመታትን አስቆጥሯል፡፡ በቀድሞው ሀረርጌ ክፍለ ሀገር ጎሀ ምስራቅ ባንድ ውስጥ የዘመናዊ ሙዚቃ ክፍል ኃላፊ ነበር ፡፡ በዚያ ቆይታው የተለያዩ የኦሮምኛ ኦሮምኛ ዘፈኖችን ከእነ ከድር ሰኢድ፣ አደም ሀሮን እና ሌሎች ድምፃውያን ጋር ሠርቷል፡፡  

   ወዲህ ወደ አዲስ አበባም መጥቶ በስቱዲዮ ውስጥ እጅግ በርካታ የሙዚቃ አልበሞችን አቀናብሯል፡፡ የዘፈን ግጥም ድርሰት ይሞክራል ፣ ፒያኖ እና ቤዝ ጊታርም ይጫወታል፡፡ የሙዚቃ አቀናባሪ እና ዜማ ደራሲ ሙሉጌታ አባተ ከአንጋፋዎቹ ማህሙድ አህመድ ፣ ታምራት ሞላ ፣ መልካሙ ተበጀ እስከ ዘመነኞቹ ጐሳዬ ተስፋዬ ፣ ማዲንጐ አፈወርቅ ፣ ፍቅረ አዲስ ነቃጥበብ የበርካታ ድምፃውያንን ስራዎች አቀናብሯል፡፡ አዲስ አበባ ከመጣ በኋላ በስቱዲዮ ያቀናበረው የመጀመሪያ ስራው የሠርጉአለም ተገኝ  ሸኙኝ የተሠኘ አልበም ሲሆን አበበ ተካ ፣ አረጋኸኝ ወራሽ ፣ ታደሠ አለሙ ፣ ገነት ማስረሻ ፣ ፀጋዬ እሸቱ ፣ ራሄል ዮሀንስ ፣ ኃይለየሱስ ግርማ ፣ ኃይልዬ ታደሠ እና ሌሎች ድምፃውያን ስራዎችንም ቀምሯል፡፡


  ወደ ባህል ሙዚቃዎች የሚያደላው ሙሉጌታ አባተ የአማርኛ ፣ ትግሪኛ ፣ ኦሮምኛ ፣ ጉራጌኛ እና ሌሎች የብሄረሰብ ሙዚቃዎችንም አቀናብሯልዜማም ደርሷል፡፡ ብዙ የበዓላት ስራዎችን እና ማህበራዊ ጉዳዮች ላይ (እንደ ኤች .አይ.ቪ/ኤድስ) የመሳሰሉ ስናዎችንም ዜማ በመድረስ አቀናብሮ ለህዝብ አድርሷል፡፡ ከአማርኛ ሙዚቃዎች በተጨማሪ ለኦሮምኛ, ትግርኛና ጉራጊኛ ዚቃ ያበረከተው አስተዋጽኦም ቀላል አይደለም፡፡ ዚቃ አቀናባሪ፣ የግጥምና ዜማ ደራሲ ሙሉጌታ አባተ ባደረበት ሕመም በኮሪያ ሆስፒታል ሕክምና ሲከታተል ቆይቶ ከዚህ አለም በሞት ተለይቷል፡፡ የቀብር ስነ - ስርዓቱም ወዳጅ ዘመዶቹ ፣ የጥበብ ቤተሰቦች እና አድናቂዎቹ በተገኙበት በሰሚት ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን ተፈፅሟል፡፡


 የ52 ዓመቱ የሙዚቃ አቀናባሪ እና ዜማ ደራሲ ሙሉጌታ አባተ ባለትዳር እና የስድስት ልጆች አባት ነበር፡፡ ፈጣሪ ነፍስህን ይማረው እያልኩ ፤ ለቤተሰቦቹ ፣ ወዳጅ ዘመዶቹ እና አድናቂዎቹ መፅናናትን እመኛለሁ፡፡