Monday, January 27, 2014

ኢትዮጵያ በአልጀሪያ ኤምባሲ ልትከፍት ነው


 ኢትዮጵያ በአልጀሪያ ኤምባሲ የመክፈት እቅድ እንዳላት የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡ የኢትዮ -አልጀሪያ 3ኛው የጋራ የሚኒስትሮች ጉባኤ ጥር 18/2006 . ዕለት በሸራተን አዲስ የተለያዩ ስምምነቶችን በመፈራረም ተጠናቋል፡፡ የኢፌዴሪ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ዶክተር ቴዎድሮስ አድሃኖም የአልጀሪያ መንግስት ኢትዮጵያ  በአልጀሪያ ለመክፈት ላቀደችው የኤምባሲ /ቤት መስሪያ ቦታ መስጠታቸውን አድንቀዋል፡፡

   ዶ/ር ቴድሮስ የኢትዮ- አልጀሪያ ግንኙነት ከጊዜ ጊዜ እያደገ መምጣቱንና የአልጀሪያ ባለብሃቶችም  ኢትዮጵያ ውስጥ በመምጣት ኢንቨስት ለማድረግ ፍላጎት እንዳላቸው ጠቁመው  ኢትዮጵያም  የሞቀ አቀባባል  እንደምታደርግላቸው ገልፀዋል፡፡ የአልጀሪያ የውጭ ጉዳይ  ሚኒስትር ራምታሌ ላማምራ በበኩላቸው የኢትዮ አልጀሪያ የሚኒስትሮች የጋራ ጉባኤ የሁለቱን ሃጋራት ግንኙነት ወደ ላቀ ደረጃ ከማሸጋጋር አንጻር የማይተካ ሚና ይኖረዋል ብለዋል፡፡

   ላማምራ ኢትዮጵያ በደቡብ ሱዳን የተፈጠረውን የፖለቲካ ቀውስ ለማረጋጋት በሁለቱ ተቀናቃኝ ወገኖች የተኩስ አቁም ስምምነት እንዲኖር የተጫወተችውን ሚናና ለአፍሪካ ህብረት አጀንዳዎች መሳካት  የምታደርገውን ብርቱ እንቅስቃሴ አድንቀዋል፡፡ የኢትዮ- አልጀሪያ የሚኒስትሮች ስብሰባ በቱሪዝም፣ በባህል፣ በሳይንስና ቴክኖሎጂ፣ በማዕድንና ፔትሮሊየም፣ በወጣቶች ዘርፍ እንዲሁም በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት አጀንሲና በአልጀሪያ ፕሬስ አገልግሎት መካከል የመግባቢያ ሰነዶች ተፈራርመዋል፡፡
 
   ከኢትዮ- አልጀሪያ የሚኒስትሮች የጋራ ጉባኤ በፊት የባለሞያዎች ስብሰባ የተካሄደ ሲሆን ባለሞያዎቹ በማህበራዊ፣ፖለቲካዊና ምጣኔ ሃብታዊ ጉዳይ ላይ በዝርዝር መክርዋል፡፡ ባለሞያዎቹ በውይይታቸው ወቅት በንግድ፣ በኢንዱስትሪ፣ በገጠር ልማት፣ በግብርና፣ በኢንቨስትመንትና በወጣቶች ጉዳይ ላይ  ሁለቱ ሃገራት በትብብር ለመስራት የሚያስችላቸውን  የአቅጣጫ ጠቋሚ ንድፍ አስቀምጠዋል፡፡ የአትዮ- አልጅሪያ የጋራ የሚኒስትሮች ጉባኤ ሩብ ክፍለ ዘመን ያስቆጠረና የሁለቱን  ሀገራት  ግንኙነት  ለማጠናከር የተመሰረተ ነው፡፡

No comments:

Post a Comment