Sunday, January 26, 2014

አየር መንገዱ በየአመቱ 15 እስከ 20 በመቶ የሽያጭ እድገት በማስመዝገብ ላይ ነው


  የኢትዮጵያ አየር መንገድ በያዝነው በጀት ዓመት የሚያጓጉዛቸውን መንገደኞች ብዛት ሰባት ሚሊዮን ለማድረስ ማቀዱን ገለጸ። የአየር መንገዱ ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ተወልደ ገብረ ማርያም ትናንት ከፍተኛ ሽያጭ ላስመዘገቡ የጉዞ ወኪሎች ሽልማት በሰጡበት ወቅት እንዳስታወቁት አየር መንገዱ ዓመታዊ ዕድገቱን በማስቀጠል ተጓዦቹን በከፍተኛ መጠን ለማሳደግ እየሰራ ነው።
 
 አየር መንገዱ ያስገባቸው ዘመናዊ አውሮፕላኖች ደንበኞቹ ባሳዩት ከፍተኛ ተመራጭነትና የጉዞ ወኪሎቹ ባደረጉት ርብርብ የትኬት ሽያጫቸውን በከፍተኛ መጠን አሳድገውታል። አየር መንገዱ የሚሰጠውን ሁሉን አቀፍ አገልግሎት በማሻሻልና ለችግሮች አፋጣኝ መፍትሄ በመስጠት የደንበኞችን የአገልግሎት እርካታ 87 በመቶ መድረሱንም ገልጸዋል። ተጨማሪ 16 ዘመናዊ አውሮፕላኖችን ለማስገባት በዝግጅት ላይ መሆናቸውንም ዋና ሥራ አስፈጻሚው አስታውቀዋል።

   የአየር መንገዱ የአዲስ አበባ የሽያጭ ዳይሬክተር ወይዘሮ ሰብለ ደገፉ እንደገለጹት ወደ 70 በመቶ የሚጠጋውን  በአዲስ አበባ የትኬት ሽያጭ በጉዞ ወኪሎች የሚሸፈን ሲሆን የቀረውን አየር መንገዱ ያከናውናል። አየር መንገዱ  በየአመቱ 15 እስከ 20 በመቶ የሽያጭ እድገት በማስመዝገብ ከፍተኛ ለውጥ ላይ መሆኑም ጠቁመዋል።

    በዕለቱ ከፍተኛ ሽያጭ በማስመዝገብ የተሸለሙት 31 የጉዞ ሽያጭ ወኪሎች ናቸው። የኢትዮጵያ አየር መንገድ እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር በ2025 በያዘው ራዕይ ዓመታዊ ገቢውን 10ቢሊዮን ዶላር ለማድረስ እየሰራ መሆኑም ተገልጧል ።
                                                ምንጭ ፡-  ኢ.ዜ.አ

No comments:

Post a Comment