Saturday, December 27, 2014

ለእይታ ያልታደሉ ቅርሶች ...



  የታዕካ ነገስት በዓታ ለማርያም ህንፃ ቤተ ክርሲቲያንን ለመስራት 10 ዓመታትን ፈጅቷል፡፡ ከ1910 እስከ 1920 ዓ.ም ድረስ፡፡ ህንፃ ቤተ ክርስቲያኑን  ያሰሩት የዳግማዊ አፄ ምኒልክ 3ኛ ልጅ የነበሩት ግርማዊት ንግስተ ነገስት ዘውዲቱ ምኒሊክ ናቸው፡፡ ንግስት ዘውዲቱ ይህን ህንፃ ቤተ ክርስቲያን እና በውስጡ ያለውን ሙዚየም ለአባታቸው መልካም ስራ መታሰቢያ እና ለአፅማቸው ማረፊያ በማለት እንዳሰሩት ይነገራል፡፡


  በቤተ ክርስቲያኑ የውስጥ ክፍል አራቱም አቅጣጫ የሀገሪቱን ታሪክ የሚያወሱ ስዕሎችን ተመልክተው  ወደ ምድር ቤት ሲወርዱ አነስ ያለችውን የበዓታ ሙዚየም ያገኛሉ፡፡ በዚች አነስተኛ ሙዚየም ውስጥ ለአይን የሚያስገርሙ ተጎብኝተው የማይጠገቡ ቅርሶችን ያያሉ፡፡ እነሱም የትላንት የጥበብ እድገታችን እና የስልጣኔ ጉዞአችን የት ድረስ እንደነበር ያመላክታሉ፡፡

  በቅድሚያ 1924 ከግሪክ ቤተ ክርስቲያን ለግርማዊት ንግስተ ነገስት ዘውዲቱ ምኒልክ የተበረከተላቸውን የእየሱስ ክርስቶስ የግንዘት ምስል ከመስተዋት በተሰራ ሳጥን ያገኛሉ፡፡ ከዚህ እይታ ባሻገር አይንዎትን ሲያማትሩ ሶስት መካነ መቃብሮችን በመደዳ ተሰድረው ይመለከታሉ፡፡ / የዳግማዊ አፄ ምኒልክ የግርማዊት እቴጌ ጣይቱ ብጡል የንግስተ ነገስት ዘውዲቱ ምኒልክን/፡፡ ከዚህ ፈንጠር ብለው ደግሞ የግብፁን ሊቀ ጳጳስ የአቡነ ማቴዎስ እና የልዕልት ፀሀይ ኃይለስላሴን መካነ መቃብሮች ያገኛሉ፡፡ 

   እነዚህ ብቻ አይደሉም በሙዚየሙ ውስጥ 100 አመት በላይ እድሜ ያላቸው ወንበሮችን አይተው ይደነቃሉ፡፡ እነዚህ ወንበሮች አንዱ የዳግማዊ አፄ ምኒልክ ተንቀሳቃሽ ወንበር ሲሆን በአደዋ ጦርነት ጊዜም አብሯቸው ሄዶ ሲያስቀድሱ ይጠቀሙበት እንደነበር ይነገራል፡፡ ሌላው ወንበር ደግሞ የግርማዊት ንግስተ ነገስት ዘውዲቱ ሲሆን እሱም ንግስቲቱ ዳዊት ሲደግሙ ይጠቀሙበት እንደነበር የሙዚየሙ አስጎብኚ ይገልፃሉ፡፡ አይንዎትን ዘወር አድርገው ቀና ሲያደርጉ ደግሞ 115 አመት በላይ እድሜ ያላቸው እና ከትልቅ ግንድ በሰው ቁመት ልክ ተፈልፍለው የተሰሩ ሁለት ወርቃማ ቅብ ያላቸው ዙፋኖችን ያያሉ፡፡ 


  አፄ ምኒልክ እና እቴጌ ጣይቱ ይጠቀሙባቸው የነበሩ የወርቅ ጥላዎች ፣ የአፄ ኃይለስላሴ እና የእቴጌ መነን ወንበሮች ፣ የነገስታቱ አልባሳት እንዲሁም ከሀገር ውስጥ እና ከውጪ የተበረከቱ ልዩ ልዩ ስጦታዎችም አሉ፡፡ ከ100 አመት በላይ የቆየ ነጋሪትንም በሙዚየሙ ውስጥ ይመለከታሉ፡፡ ዳግማዊ አፄ ምኒሊክይህን ነጋሪት ዘመቻ አልያም ለየት ያለ ነገር ሲኖር በማስጎሰም ለህዝባቸው ጥሪ ወይም መልዕክት ያስተላልፉበት ነበር፡፡ ከእነዚህም በተጨማሪ በሙዚየሙ ባሉ ሁለት መደርደሪያዎች በርካታ የብራና መፅሃፍትን ይገኛሉ፡፡


  በመጨረሻ የሌላ ሀገር ጎብኚ የእኛን ታሪክ ለማወቅ ሀገር አቋርጦ ፣ ባህር ተሸግሮ ሲመጣ ፣ እኛ ግን አጠገባችን ያለውን ለመጎብኘት ፣ ታሪካችንን ለማወቅ እንዴት ተሳነን? ምላሹን ለእናንተ ትቻለሁ………!!!

Friday, December 26, 2014

የሀረር ጀጎል - ግንብ


   የሀረር ህዝብ ታሪክ ባህል እና ማንነት ከሀረር ከተማ ጋር በእጅጉ የተቆራኘ ነው፡፡ ሀረሪዎች በረዥም ዘመን የስልጣኔ ታሪካቸው ያፈሯቸው ተንቀሳቃሽ እና የማይንቀሳቀሱ እንዲሁም የሚዳሰሱ እና የማይዳሰሱ በርካታ ቁሳዊ እና መንፈሳዊ ቅርሶች ባለቤት ናቸው፡፡ ከእነዚህ ቅርሶች መካከልም የከተማዋ ልዩ መለያ ምልክት ከመሆንም አልፎ .. 2006 በአለም ቅርስነት የተመዘገበው የጀጎል ግንብ በቀዳሚነት ይጠቀሳል፡፡ በግንቡ ውስጥም 82 በላይ መስኪዶች እና በርከት ያሉ የሀረሪ ባህላዊ ቤቶች ይገኛሉ፡፡
  

  ሀረር ከፍተኛ የስልጣኔ እድገት ደረጃ ላይ በደረሰችበት በ16ኛው ክፍለ ዘመንም በምስራቅ አፍሪካ የእስልምና ሀይማኖት ትምህርት እና የንግድ ማዕከል ሆናም አገልግላለች፡፡ ይህም የበርካታ ታሪካዊ እና ባህላዊ ቅርሶች ባለቤት እንድትሆን አድርጓታል፡፡ የጀጎል ግንብ የሀረሪ ህዝብ የኪነ ህንፃ ችሎታውን የሚያስመሰክር የታሪክ እና የጥበብ መዘክር ነው፡፡ ይህ ግንብ በ16ኛው ክፍለ ዘመን አጋማሽ በአሚር ኑር አማካኝነት እንደተገነባም ይነገራል፡፡
     የጀጎል ግንብ ከፍታ -------- ከ 4.5 እስከ 5 ሜትር
       ››     ›› ውፍረት ------- ከ40 እስከ 50 ኢንች
       ››     ›› ስፋት --------- 48
       ››     ›› በሮች ------ ሰባት ሲሆኑ አምስቱ ጥንታዊ በሮች ሲሆኑ ሁለቱ ደግሞ እ.ኤ.አ ከ1987 በኋላ የተከፈቱ እንደሆኑ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡

  ሀረር ከቅርስነት ባሻገር እ.ኤ.አ በ2003/4 በሰላም ፣ በመቻቻል ፣ በመፈቃቀር እና በልማት ከተማነት አለም አቀፍ ሽልማት እና እውቅናን አግኝታለች፡፡ ይህም የተለያየ እምነት ፣ ባህል እና ቋንቋ ያላቸው ህዝቦች ለዘመናት በሰላም እና በፍቅር የኖሩባት እና ዛሬም የሚኖሩባት ከተማ በመሆኗ የተቀዳጀችው ክብር እና እውቅና ነው፡፡

Thursday, December 25, 2014

ከሊስትሮንት እና ሎተሪ አዟሪነት እስከ አንጋፋ ተዋናይነት ---- አርቲስት ሱራፌል ተካ !!!

 
   ተዋናይ ሱራፌል ተካ ትውልድ እና እድገቱ ጎንደር ፒያሳ አካባቢ ነው፡፡ በብዙ ውጣ ውረድ ውስጥ ያለፈው ሱራፌል በወጣትነቱ በሊስትሮነት ፣ ሎተሪ አዟሪነት ረዘም ላሉ አመታት ሰርቷል፡፡ ከዚያም በ1982ዓ.ም መጀመሪያ አካባቢ በጎንደር ሲኒማ ቤት የሻይ ክበብ ባሪስታ ሆኖ ተቀጠረ፡፡ በዚህ ወቅት በጎንደር ከተማ የሚገኙ አማተር ከያኒያን “አፄ ቴዎድሮስ - የአንድ እናት ልጆች” የተሰኘ ትያትር ለህዝብ ለማቅረብ ዝግጅት ሲያደርጉ እሱ ሹልክ እያል እየገባ ይመለከት ነበር፡፡ በተደጋጋሚ እየተደበቀ ትያትሩን እየተመለከተ ተውኔቱን ያጠናል፡፡ ከያንያኖቹ ተለማምደው ሲጨርሱ እሱ መድረክ ላይ እየወጣ አንዴ ቴዎድሮስን ሌላ ጊዜ ድግሞ ገብርዬን ሆኖ ይጫወታል፡፡ ባጋጣሚ የተውኔቱ ፀሀፊ /ደራሲ/ አቶ ሲሳይ ታረቀኝ እቃ እረስተው ሲመለሱ እሱ ሲተውን ይመለከቱታል፤ በጣም ተገርመውም ያደንቁታል፡፡ ሀሳብ ተለዋውጠው ይለያያሉ፡፡

   ሱራፌል ከሻይ ክበቡ ስራውን እየተወ የከያንያኑን ልምምድ ይመለከታል፡፡ ስራውን ትቶ እየጠፋ ሲያስቸግራቸው የክበቡ ኃላፊ ይከታተሉታል፡፡ እናም በሲኒማ ቤት በተደጋጋሚ ሲያገኙት ከቃል ማስጠንቀቂያ እስከ መጨረሻ ማስጠንቀቂያ ተሰጠው፡፡ ከዚያም ትያትር መመልከቱን ትቶ የባሪስታነት ስራውን እየሰራ አንድ አጋጣሚ ተፈጠረ፡፡ ይኸውም “አፄ ቴዎድሮስ - የአንድ እናት ልጆች” የተባለው ትያትር በህዝብ ዘንድ ተቀባይነት በማግኘቱ በየጦር ካምፖቹ እንዲቀርብ ሲደረግ “ገብርዬን” ሆኖ የሚጫወተው ወጣት ይጠፋል፡፡ 

      ይኸን ጊዜ የተውኔቱ ደራሲ አቶ ሲሳይ ታረቀኝ ባንድ ወቅት መድረክ ላይ የገብርዬን ገፀ ባህሪ ሲጫወት የነበረው ሱራፌል ትዝ ይላቸዋል፡፡ አንዳንድ ነገሮችን አስተካክሎ እንዲተውን ይመረጣል፡፡ይህ አጋጣሚ ነው እንግዲህ ሱራፌልን ወደ ተውኔቱ ያመራው፡፡ በወቅቱም የገብርዬን ገፀ ባህሪ ማለትም ታማኝነቱን ፣ ገርነቱን እና የዋህነቱን ስለሚወደው በግሩም ሁኔታ ተጫውቶ ያልተጠበቀ ነገር አሳየ፡፡ በዚህም አድነቆት ከየአቅጥጫው ጎረፈለት፡፡ ተዋናይ ሱራፌል ተካ ከሚሰራበት የሻይ ክበብ ሳያስፈቅድ በመሄዱ ሌላ ሰው ተቀጥሮ ይጠብቀዋል፤ እሱም የትወና ሙያውን በአጫጭር ስልጠናዎች በማጠናከር ይቀጥላል፡፡ 


  በጎንደር ቆይታውም “ዞብል” የሚባል አማተር የትያትር እና የስነ ፅሁፍ ክበብን በመመስረት ሊቀመንበር ሆኖም አገልግሏል፡፡ ከዚያም የቀድሞው የብአዲን ኪነት ፣ የዘመናዊ እና የባህላዊ ቡድንን ተቀላቀለ፡፡ ባህር ዳር ሙሉዓለም አዳራሽ ከተሰራ በኋላ የአማራ ክልል የባህል፣ የዘመናዊ እና የትያትር ቡድን ተባለ፡፡ ትንሽ ከቆየ በኋላ በአማራ ፖሊስ ኮሚሽን ስር ተጠቃለለ፡፡ በዚህም በቋሚ ሰራተኝነት ለረጅም አመታት አገልግሏል፡፡ ተዋናይ ሱራፌል ተካ በአማራ ክልል ቆይታው በርካታ ትያትሮችን ሰርቷል፡፡ ከእነዚህ ውስጥ “ መጢቃ ፣ ቅርሻት ፣ አማጭ ፣ ጉድና ጅራት ፣ ሙት ይዞ ይሞታል ፣ አንድ ጡት ፣ ማሪኝ ፣ ሽፍንፍን ፣ የዘመን ምጥ እና እርጉም ሀዋሪያ ይጠቀሳሉ፡፡ የቴዎድሮስ ራዕይም እዚያ ተሰርቶ አዲስ አበባ ብሄራዊ ትያትር ነው የተመረቀው፡፡ ከ15 በላይ ትያትሮችን የተጫወተ ሲሆን ከ10 በላይ ባሉት መሪ ተዋናይ ፣ በ3 ያህሉ በዋና አዘጋጅነት እና በተቀሩት ደግሞ በረዳት አዘጋጅነት ተሳትፏል፡፡


  “አማጭ ፣ ጉድና ጅራት  እና ሙት ይዞ ይሞታል” - የመምህር ጎይቶም ሀይሌ ሲሆኑ “የዘመን ምጥ” ደግሞ የዶ/ር በድሉ ዋቅጅራ ድርሰት ነው፡፡ በአማራ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን ቆይታውም “የኢንስፔክተርነት” ማዕረግ አግኝቷል፡፡ ከባህር ዳር ወደ አዲሰ አበባ ከመጣ በኋላም በተለያዩ ትያትሮች እና ፊልሞች ላይ ልዩ ልዩ ገፀ ባህሪያትን ተላብሶ ተጫውቷል፡፡ ቴያትሮችን ስናስቀድም ፡- የጠለቀች ጀምበር ፣ ደጋግ ሰይጣኖች ፣ ጓደኛሞቹ ፣ ግዳይ ፣ የቴዎድሮስ ራዕይ ፣ ቶፓዝ ፣ ሶስተኛው ችሎት ፣ ቅጥልጥል ኮኮቦች ላይ ተውኗል፡፡ በተወሰኑት ላይ አሁንም እየሰራ ይገኛል፡፡ በቅርቡ የሚታዩ ስራዎችም አሉት፡፡ ከእነዚህ ውስጥ “የፍቅር ማዕበል” የተሰኘው ትርጉም ትያትር ይጠቀሳል፡፡


   የፊልም ስራን የጀመረው “ዘቢግ ባታለየን” / ግዙፉ የሻለቃ ጦር እንደማለት ነው/ አለም አቀፍ እውቅና ካላቸው እንግሊዛውያን እና አንጋፋ ኢትዮጵያን ተዋናዮች ጋር ነው፡፡ ፊልሙ በአውሮፓ እና በአሜሪካ ሲሆን የታየው በጊዜው ከፍተኛ የሆነ ብር አግኝቶበታል፡፡ 8,000 ብር ማለት ነው፡፡ ከዚያ በኋላም ላሎምቤ ፣ ባለስልጣኑ ፣ አባይ ወይስ ቬጋስ ፣ ኤማንዳ ፣ ፀረ ሚሊዮን ፣ ህይወት በደረጃ ፣ የባል ጋብቻ ፣ ጀግኖቹ እና አልበም ጥቂቶቹ ናቸው፡ 

   በተጨማሪም በሰው ለሰው ተከታታይ የቴሌቭዥን ድራማ ላይ “ኩራን” ሆኖ በመጫወት ከፍተኛ ተወዳጅነትን አግኝተዋል፡፡ ከባለቤቱ አርቲስት ገበያነሽ ኃይለማሪያም ጋር የአማራ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን የባህል ፣ የዘመናዊና የትያትር ቡድን ክፍል ሳሉ ተዋውቀው አሁን ሁለት ወንድ ልጆችን አፍርተዋል፡፡ አርቲስት ገበያነሽ የተለያዩ የሬድዮ ጭውውቶችን እና ድራማዎችን የምትፅፍ እና የምትጫወት ሲሆን በሰው ለሰው ድራማ ላይም የይጥና ባለቤት ሆና ተውናለች፡፡