Monday, March 30, 2015

የክቡር ዶክተር አሊ ቢራ የወርቅ ኢዮቤልዩ በዓል ተከበረ፡፡


   በኦሮሚኛ ሙዚቃው የሚታወቀው እና በዚሁ ዘርፍ ግማሽ ክፍለ ዘመንን ያስቆጠረው ክቡር ዶክተር አሊ ቢራ የወርቅ ኢዮ ቤልዩ በዓሉን በደመቀ ሁኔታ አክብሯል፡፡ ይህንን ምክንያት በማድረግም ላበረከተው አስተዋፅኦ በአዳማ ከተማ የምስጋና ስነ ስርዓት ተዘጋጅቶለት ነበር፡፡ በዚሁ ስነ ስርዓት ላይ ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናት ፣ የተለያዩ ድምፃውያን ፣ የአርቲስቱ አድናቂዎች እና ወዳጅ ዘመዶቹ ተገኝተዋል፡፡ በወቅቱም በድምሩ 5 ሚሊዮን ብር የሚያወጡ የመኪና እና የመኖሪያ ቤት ስጦታ ከኦሮሚያ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት ተበርክቶለታል፡፡ በመድረኩ ላይም ድምፃዊ ቀመር የሱፍ እና ታደለ ገመቹ የእሱን ስራዎች ተጫውተዋል፡፡

   ስምንት ያህል ቋንቋዎችን የሚናገረው አሊ ቢራ በድሬዳዋ ከተማ ነው የተወለደው፡፡ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርቱን በድሬድዋ ከተማ በመድረስ ጀዲድ እና በልዑል ራስ መኮንን ት/ቤት እንዲሁም የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን ደግሞ በአዲስ አበባ ካቴዴራል ተከታትሏል፡፡ በኋላም በካሊፎርኒያ ሳንታሞኒካ ት/ቤትም በሙዚቃ ትምህርት ዘርፍ የከፍተኛ ትምህርቱን መማር ችሏል፡፡ 

  ሶስት በአሊ ስም የሚጠሩ ታዳጊዎች በነበሩበት የአፈረን ቀሎ የሙዚቃ እና የባህል ቡድን 14 ዓመቱ መሳተፍ የጀመረው የያኔው ታዳጊ ከቀሪዎቹ እንዲለይ በማለት ጓደኞቹ አሊ ቢራ በማለት መጥራት ጀመሩ፡፡ ቢራ የሚለው ስያሜ ለመጀመሪያ ጊዜ መድረክ ላይ ከተጫወተውብራዳ ብርሄ /Birraadahaa Barihee/” የመጣ እንደሆነ ይነገራል፡፡ቤተሰቦቹ ያወጡለት ስም ግን አሊ መሀመድ ሙሳ ነው፡፡ አርቲስቱ የተጓዘባቸው 50 ዓመታት በሀገራችን ሙዚቃ ታሪክ ውስጥ የራሱን ጉልህ ምዕራፍ የፃፈባቸው እና በዚህ ሂደትም በርካታ ውጣ ውረዶችን እንዲሁም ፈተናዎችን አልፎ ለታላቅ ስኬት የበቃባቸው አመታት ናቸው፡፡


 አሊ ቢራ ከአፈረን ቀሎ ቆይታው በኋላ ክቡር ዘበኛን ተቀላቅሎ በኦሮምኛ ሀደሬኛ ሶማሌኛ እና አማርኛ ስራዎቹን አቅርቧል፡፡ ፒያኖ ጊታር እና ኡዱ አሳምሮ የሚጫወተው አሊ ቢራ በባህር ማዶ ቋንቋዎችስዋህሊ አረቢኛ እና እንግሊዘኛም የማይረሱ ስራዎችን ተጫውቷል፡፡ አርቲስት አሊ ቢራ በእነዚህ ቋንቋዎች እስካሁን ከ260 በላይ ተወዳጅ ዘፈኖችን ሰርቷል፡፡




  አርቲሰት አሊ ቢራ ለራሱ እና ለሌሎች ድምፃውያን በርካታ ግጥም እና ዜማዎችን ደርሷል፡፡ የራሱን ለየት ያለ የአዘፋፈን ስልትም ፈጥሯል፡፡ በሀገራችን ታሪክ ታላላቅ ከሚባሉ የሙዚቃ ቡድኖች ጋርም ሰርቷል፡፡ በሀገር ውስጥ እና በውጪም በዛ ባሉ መድረኮች ላይ ተጫውቷል፡፡ በሙዚቃው ዓለም በቆየባቸው ዘመናት በሀገር ውስጥ እና በአለም አቀፍ ደረጃ የህዝብ ፍቅር እና አክብሮትን ተቀዳጅቷል፡፡ በርከት ያሉ ሽልማቶችንም አግኝቷል፡፡ ከጅማ ዩኒቨርስቲ የተሰጠው የክብር ዶክትሬትም ከእነዚህ ውስጥ አንዱ ነው፡፡

  ክቡር ዶክተር አሊ ቢራ ከሙዚቃው ጎን ለጎን “Birra Children’s Education Fund” የተባለ ምግባረ ሰናይ ድርጅት ከባለቤቱ ጋር አቋቁሞ ለህፃንት ትምህርት ድጋፍ እያደረገ ይገኛል፡፡ ድርጅቱ አሁን በድሬዳዋ አካባቢ ባሉ ት/ቤቶች ላይ እየሰራ ሲሆን በቀጣይነት በመላው የሀገሪቱ ክፍሎች የተጠናከረ ስራ ለመስራት እቅድ አለው፡፡ 


አርቲስት አሊ ቢራ እንደገለፀው ከሆነ ካሁን በኋላ እራሱን ከሙዚቃው አግልሎ በበጎ አድራጎቱ ስራ ላይ ያተኩራል፡፡ ለኦሮምኛ ሙዚቃው ንጉስ ለክቡር ዶክተር አሊ መሀመድ ቢራ እንኳን ደስ አለህ እድሜ እና ጤና ይስጥህ ፣ ያሰብከው ይሳካ ብያለሁ ……..

ኮሜዲያን ዳኒ ቁንጮ በ37 ዓመቱ አረፈ



   ከእናቱ / አስራት ሰቤ እና ከአባቱ ወልዴ ኪሮ 1970. አዲስ አበባ 4ኪሎ - ፊት በር ነበር ተወለደው፡፡ አንደኛ እና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን በዳግማዊ ምኒሊክ ተምሯል፡፡  በተለያዩ ክበባት ትያትርን ይሰራ የነበረው ዳኒ ቁንጮ ስዕልም ይሞክር  ነበር፡፡ ዳኒ ቁንጮ  በተለያዩ ክለቦች ሙዚቃን ያጫውት የነበረ ሲሆን በተለይ በኮሜዲ ስራዎቹ ነው የሚታወቀው፡፡ በዚህም በርካታ የኮሜዲ ስራዎቹን ለአድናቂዎቹ አበርክቷል፡፡ ኮሜዲያን ዳኒ ተክለሃይማኖት ሆስፒታል ለህክምና ከገባ በኋላ በሀኪሞች እርዳታ ቢደረግለትም ሊተርፍ አልቻለም፡፡ ባደረበት የኩላሊት ህመም በዚሁ የህክምና ተቋም ሲረዳ ቆይቶ መጋቢት 19 ቀን 2007ዓ.ም ማምሻውን ይህቺን ዓለም ተሰናብቷል፡፡

   ቀብሩም እሁድ መጋቢት 20 ቀን 2007ዓ.ም ከቀኑ 6፡00 ጉርድ ሾላ በሳሊተ ምህረት ቤተ ክርስቲያን ተፈፅሟል፡፡ ለኮሜዲያኑ ቤተሰቦች ፣ ወዳጅ ዘመዶች እና አድናቂዎች መፅናናትን እመኛለሁ፡፡

Sunday, March 29, 2015

DIBABA RUNS SECOND-FASTEST 5KM IN HISTORY AT CARLSBAD 5000

  
   Two-time world indoor champion Genzebe Dibaba narrowly missed out on breaking the world best at the Carlsbad 5000, but her winning time of 14:48 was the second-fastest ever recorded for 5km on the roads.

   The 24-year-old owns the fastest times in history across four distances indoors, and had been hoping to add another mark to her growing collection. Just like three of her indoor record-breaking performances, she was targeting a time that had been set by Meseret Defar. The two-time Olympic champion ran 14:46 on this course in 2006.

  
Burka, the 2006 world cross-country champion and 2008 world indoor 1500m champion, finished second in 15:13, taking 13 seconds off the PB she set when winning in Carlsbad two years ago.

   Ayalew, the 2009 world 10,000m bronze medalist, also set a PB, clocking 15:18 in third place. It was just the second time in the 30-year history of the Carlsbad 5000 that Ethiopians had swept the podium positions in the women’s race. 


                                                             Source:- IAAF

Saturday, March 28, 2015

ኢትዮጵያ በቻይና ጉያንግ የአለም አገር አቋራጭ ውድድር በበላይነት አጠናቀቀች ።


   41ኛውን የአለም አገር አቋራጭ ውድድር ኢትዮጵያ በአጠቃላይ 5 የወርቅ 3 የብርና 3 የነሃስ ሜዳሊያ በማግኘት ነው ቀዳሚ የሆነችው። ኢትዮጵያ በስድስት ኪሎ ሜትር ወጣት ሴቶች እና በስምንት ኪሎ ሜትር ወጣት ወንዶች የወርቅ ሜዳሊያዎችን ስታገኝ፥ በስምንት ኪሎ ሜትር አዋቂ ሴቶች ደግሞ የብርና የነሃስ ሜዳሊያ አግኝታለች።

 በሴቶች ስድስት ኪሎ ሜትር ወጣት ሴቶች ለተሰንበት ግደይ፣ ደራ ዲዳ እና እታገኝ ወልዱን አስከትላ በመግባቷ ኢትዮጵያ በቡድንም የወርቅ ሜዳሊያ እንድታገኝ አድርገዋል። በ8 ኪሎ ሜትር ወንዶችም ያሲን ሀጂ በአንደኝነት በማጠናቀቅ የወርቅ ሜዳለያ አግኝቷል።

  በ8 ኪሎ ሜትር አዋቂ ሴቶች በተካሄደው ውድድር ሰንበሬ ተፈሪ እና ነፃነት ጉደታ የብር እና የወርቅ ሜዳልያ ለአገራቸው አስገኝተዋል።

   በ12 ኪሎ ሜትር አዋቂ ወንዶች ውድድር ሙክታር እንድሪስ 3ኛ ሆኖ በማጠናቀቅ የነሃስ ሜዳልያ ለኢትዮጰያ ሲያስገኝ፣ ሀጎስ ገብረህይወት እና ታምራት ቶላ 4ኛ እና 5ኛ ሆነው አጠናቀዋል።  በዚህም በቡድን ባመጡት ውጤት 5ኛ ወርቅ ኢትዮጵያ ማግኘት ችላለች። 
                                                ምንጭ ፡- ኤፍ.ቢ.ሲ 

Friday, March 27, 2015

ከአርባ ምንጭ ወደ ጅቡቲ የተፈጥሮ ጋዝ ማስተላለፊያ ቱቦ ዝርጋታ ሊጀመር ነው፡፡

   
  የሚዘረጋው 1 231 ኪሎ ሜትር የተፈጥሮ ጋዝ ማስተላለፊያ ቧንቧ ከአርባምንጭ ተነስቶ በአዋሳ በድሬዳዋ አድርጎ በመጨረሻም ጁቡቲ ወደብ እንደሚደርስ ታውቋል። ይህን ስራ ለማስጀመር የሚስችል ፈንድ መገኘቱን እንዲሁም በኢትዮጵያ መንግስትና በጅቡቲ መካከል የስምምነት ውል መፈረሙንም የዘገበው ሰንደቅ ጋዜጣ ነው፡፡

   በአርባምንጭ የተገኘው የተፈጥሮ ጋዝ ክምችት በዓለም ከፍተኛ ክምችት ካላት ሩሲያ የሚበልጥ መሆኑ ተገልጿል። በአርባ ምንጭ የተገኘው የጋዝ ክምችት አዋጭነቱ ከካሉብ የተፈጥሮ ጋዝ ክምችት ጋር ፈጽሞ የማይገናኝና ለአበዳሪ ሀገራትም ከፍተኛ የሆነ መተማመን የፈጠረ በመሆኑ ለቱቦው ዝርጋታ ፈንድ እንዲለቀቅ አስችሏል።ኢትዮጵያም በዓለም ደረጃ ቁጥር አንድ የተፈጥሮ ጋዝ ክምችት ባለቤት የሚያደርጋት ከመሆኑም በላይ በቀጣይ በኢኮኖሚዋ ላይ አይነተኛ ድርሻ ይኖረዋል ሲል ጽፏል ጋዜጣው፡፡ 



    የጁቡቲ
መንግስት በበኩሉ የኢትዮጵያን የተፈጥሮ ጋዝ ለማከማቸት፣ ለማጣራት እና ለዓለም ገበያ ለማቅረብ 2 ነጥብ 6 ቢሊዮን ዳላር አዳዲስ ተርሚናሎች እየገነባ ነው። ጅቡቲ በዓመት ቢያንስ 10 ሚሊዮን ኪዩቢክ ሜትር የተፈጥሮ ጋዝ ከኢትዮጵያ ወደ ቻይና ለመላክ እየተሰናዳች መሆኑም ተጠቁሟል።  የአርባምንጩን የተፈጥሮ ጋዝ እያለማ የሚገኘው አፍሪካ ኦይል ኮርፖሬሽን የተባለ የካናዳ ኩባንያ ነው። ኩባንያው በነዳጅና በተፈጥሮ ጋዝ ፍለጋና ማምረት ላይ የተሰማራ ሲሆን፤ በአሁኑ ሰዓት ኩባንያው በኬኒያ፣ በኢትዮጵያ እና በፑንትላንድ ሥራዎቹን እያከናወነ ይገኛል፡፡

Tuesday, March 24, 2015

“አዞ ያስለቅሳል እንጂ አያለቅስም....”


     አዞ ሲበላ ያለቅሳል ይባላል የሚበላ ከሆነ ለምን ያለቅሳል ፤ እውንስ አዞ ያለቅሳልን ? አዞ ቆዳው በጣም ጥቅጥቅ ነው፡፡ ስለዚህ በላብ መልክ በቆዳው የሚወጣለት ነገር የለም፡፡ በጥርሶቹ ደግሞ ቁርጥ እያደረገ ዋጥ ያደርጋል እንጂ አያኝክም ፣ አያላምጥም፡፡ ስለዚህ በቆረጠው ልኬት ወደ ውስጥ እንዲገባ ነው የሚያደርገው እና አንዳንድ ከፍ ያሉ ነገሮች ሲያጋጥሙት ጉሮሮው ይጨናነቃል፡፡ በዚህ ጊዜ ላቡ በአይኑ ዱብ ዱብ ይላል፡፡ ይህ ደግሞ ላብ እንጂ እምባ አይደለም፡፡ አዞ ያስለቅሳል እንጂ አያለቅስም ስትል የአርባ ምንጭ አዞ ማደለቢያ የጉብኝት ባለሙያ ወ/ሪት ህይወት አሰፋ አጫወተችኝ፡፡

     አስጎብኛችን ጨዋታ አዋቂ ናት ፡፡ እያዋዛች ቁም ነገር ማስኮምኮሟን ቀጥላለች…… በአለማችን ላይ 25 አይነት የአዞ ዝርያ አይነቶች አሉ፡፡ በአፍሪካ 4 ዓይነቱ ሲገኙ በኢትዮጵያ ደግሞየናይል አዞየተባለው ብቻ ነው የሚገኘው፡፡ 

  የናይል አዞ ካሉት ሁሉ ተፈላጊ ተመራጭ ተወዳጅ ሲሆን ግን ኃይለኛ ቢሆንም ካልነኩት አይነካም፤ ከነኩት ግን አይለቅም ፡፡ ልክ እንደ ኢትዮጵያዊ ነው ባህሪው ስትል አከለችልኝ፡፡   አዞዎች ከእንቁላል ሲፈለፈሉ መናከስ ይጀምራሉ፤ ምክንያቱም ከጥርስ ጋር ስለሚፈጠሩ፡፡ ተንቀሳቃሽ ምላስ የላቸውም፡፡ ጥርሳቸው ግን ከ62 - 66 ይደርሳል፡፡ አዞ አያኝክም ፣ አያላምጥም ፣ አያጣጥምም ስለዚህ ቁርጥም እያደረገ ዋጥ ያደርጋል ማለት ነው፡፡ 



   የጉብኝት ባለሙያዋ ወ/ሪት ህይወት አንዳጫወተችኝ በማዕከሉ ያሉ አዞዎች ከ3 - 6 ዓመት ባለው ጊዜ ውስጥ ለእርድ የሚፈለጉበት /ቆዳቸው የሚፍለግበት/ ጊዜ ነው፡፡ ሲታረዱም የራሳቸው የሆነ መያዣ ዘዴ እና መምቻ ጥይት አለ፡፡ በዚህም ኢላማ የሚችል ሰው አናታቸው ላይ ይመታቸውና በማጅራታቸው/በጀርባቸው/ በኩል ይታረዳሉ፡፡


      አንድ አዞ ከ120 -150 አመት መኖር ይችላል፡፡ ከ7 - 8 ሜትር መርዘም ይችላል፡፡ ከ500 - 700 ኪ.ግ መመዘን ይችላል፡፡ ናይል ኮሮኮዳይል (ትልቁ አዞ ) ማለት ነው፡፡ አንድ የአዞ እንቁላል ከ40 - 140 ግራም ይመዝናል፡፡ አንድ አዞ በአንድ ጊዜ ከ30 - 70 እንቁላል ትጥላለች፡፡ 30ም ሆነ 70 በአመት አንድ ጊዜ ብቻ ነው የምትጥለው፡፡  ከጣለችው እንቁላል ውስጥም 75 በመቶ የመፈልፈል እድል አላቸው፡፡ ለመፈልፈል ከእሷ የሚፈልጉት ነገር የለም፡፡ በአሸዋው ሙቀት ብቻ ነው የሚፈለፈሉት፡፡


     የፆታቸው ሁኔታም የሚወሰነው በአሸዋው ሙቀት እና ቅዝቃዜ ነው፡፡ ሙቀቱ ከፍተኛ ከሆነ ወንዶች ይሆናሉ፤ ቀዝቀዝ ያለ ከሆነ ደግሞ ሴቶች በማለት አስጎብኚዋ ወ/ሪት ህይወት መረጃውን በሳቅ እና በፈገግታ እያዋዛች ማስኮምኮሟን ቀጠለች፡፡ አዞ ለአቅመ አዞ የሚደርሰው ከ10 ዓመት በኋላ ነው፡፡ በማዕከሉ አንድ ሴት እና አንድ ወንድ አዞ ከእርድ ውጪ ሆነው በአንድ ገንዳ ውስጥ ለጎብኚዎች እይታ ተብለው ተቀምጠዋል፡፡ እነዚህ አዞዎች 26 ያህል አመታትን ስላስቆጠሩ የማዕከሉ ፈርጥ ናቸው፡፡ እንደ አስጎብኚያችን እከ እና ትርፌ የሚል ቅፅል ስምም ተሰጥቷቸዋል፡፡


     እኔም የዛሬ ጡመራዬን እዚህ ላይ ገታ ላድርግ፤ በሌላ ጊዜ ሌሎች መረጃዎች ይዤላችሁ ከች እላለሁ ፡፡ በተረፈ ግን እናንተ ጨምሩበት የምታውቁትንም መረጃ አካፍሉኝ…..