Wednesday, October 12, 2022

የመስቀል ወፍ እና የአደይ አበባ ...

የመስቀል ወፍን ለአይን ያበቃት የመስከረም ውበት ነው፡፡ የመስከረም ውበት ምስጢር አበቦች ናቸው፡፡ መስከረም ምድር በአበቦች ቀለም አዲስ ልብስ የምትለብስበት ወር ነው፡፡ አደይም እንደመስቀል ወፍ የመስከረም ጌጥ ናት፡፡ በኢትዮጵያ ብቻ የሚገኘው የአደይ አበባ ዝርያ የዕድገት ጊዜውን ሲጨርስ የሚሞት ሲሆን ፍሬው ብቻ መሬት ውስጥ ተቀብሮ የሚቀር ነው፡፡ የሌሎች ግን ግንዳቸው ወይም ስራቸው ተርፎ ይቀራል ፡፡ ዋናው የአበባ ጊዜ በመስከረም ወቅት የሆነበት ምክንያት ግን የአበባ ማውጣት ዑደታቸው መስከረም ስለሆነ እና የዚህ የአደይ አበባ ዝርያ ፍሬ አፍርቶ ደርቆ ተክሉ ከሞተ በኋላ ፍሬው መሬት ተቀብሮ ከስድስት ወር እስከ ሁለት አመት ሊቆይ ስለሚችል ነው፡፡ ይህ ወቅትም የሽልብታ ጊዜ /የዶርማንሲ ፔሬድ/ ይባላል፡፡ በነዚህ ጊዜያት ውስጥ ምቹ ሁኔታዎች ሲፈጠሩ ብቻ ፍሬው እንደገና እንዲበቅል ያደርጋል ማለት ነው ፡፡ ይህም ማለት ለዕፅዋት ብቅለት አስፈላጊ የሆኑት እርጥበት፣ አየርና ሙቀት በበቂ ሁኔታ ሲስተካከል ማለት ነው፡፡ ለማበብ ደግሞ ክረምቱ መውጣት አለበት፡፡ ምንም እንኳን ሐምሌና ነሐሴ ቢበቅልም መስከረም ሳይጠባ አያብብም፡፡
እንደሚታወቀው የዝናብም ይሁን የመስኖ ውሃ ካገኙ በርካታ የሣርና የተክል ዓይነቶች ይበቅላሉ፣ ያብባሉ፣ ያፈራሉ፡፡ የአደይ አበባ አስገራሚው ነገር የቱንም ያክል በበጋ ዝናብ ቢያገኝ ወይም በየትኛውም የመስኖ እርሻ ባለበት አካባቢ አይበቅልም፡፡ ሐምሌ ከገባ ጀምሮ ግን በየእርሻውና በየዳገቱ በተለይ ከሰውና እንስሳት ንክኪ ነፃ የሆኑ ቦታዎች ሁሉ መብቀል ይጀምራል፡፡ አበባው አንዴ ካበበ በኋላ እንደፈካ ምድርን አስውቦ የሚቆየው ለረጅም ጊዜ አይደለም ፡፡ ቢበዛ ለሶስት ወራት ብቻ ጋራና ሸንተረሩን፤ ሜዳና ተራራውን በተስፋ ሰጪው ቢጫማ ቀለም አስውቦ ይቆይና ይጠፋል ፡፡ ይህም ሌላው የአደይ አበቦች መለያ ባህሪ ነው ፡፡ የመስቀል ወፍ እና የአደይ አበባ ቀጠሮ እንዳላቸው መስከረም ሲጠባ ማን ያውቃል...? ይላል ባለቅኔ መንግሥቱ ለማ
"የመስቀል ወፎች ለረጅም ጊዜ ሳይታዩ ቆይተው መስከረም ወር ላይ የሚከሰቱ ዓመታዊ እንግዶች ሳይሆኑ አብረውን ቆይተው በተፈጥሮ ሂደት የላባቸው ቀለም የሚቀየር ቤተኛ አእዋፋት እንደሆኑ በዘርፉ ጥናት እና ምርምር ያደረጉ ባለሙያዎች ይገልፃሉ ፡፡ እንደ ባለሙያዎቹ ገለፃ የመስቀል ወፍ በተለይ በመስከረም ወር አጋማሽና ቀደም ብለው በጥቁር ፡ ቢጫ ፡ ነጭ እና ብሩህ ደማቅ ቀለም አሸብርቀው የሚገለጡ እንጂ ጠፍተው የሚከሰቱ አይደሉም።
እንደየቋንቋውና እንደየአካባቢው እነዚህ ወፎች የየራሳቸው ስያሜና መጠሪያም ሊኖራቸው ይችላል። የመስቀል ወፍ ተብለው የሚታወቁት እነዚህ አእዋፋት ከኢትዮጵያ ባሻገር በኬንያ፣ ሱዳን ፣ በኡጋንዳ ፣ በታንዛንያ ፣ ሴኔጋል ፣ ደቡብ አፍሪካና ሌሎች ሀገራትም ይገኛሉ።

No comments:

Post a Comment