Saturday, August 22, 2015

“ከስጋ ቤት እስከ ታዋቂ ተዋናይነት......” አርቲስት ተዘራ ለማ

   
    ከስጋ ቤት እስከ ህብረት ሱቅ ሽያጭነት…… ከተወዛዋዥነት እና ጊታር ተጨዋችነት እስከ ታዋቂ ተዋናይነት ለመድረስ በቅቷል፡፡ በከፍተኛ18 ኪነት ቡድን ውስጥ አሁን ታዋቂ ከሆኑት ከእነ ፋሲካ ዲሜትሪ እና ዳዊት መለሰ ጋር ተጫውቷል፡፡ በጊዜውም በኪነት ቡድኑ ውስጥ በተወዛዋዥነት እና በጊታር ተጫዋች ነት ያገለግል ነበር፡፡ ከ1983 ዓ.ም በኋላ ኪነት ቡድኑ በመበተኑ እሱም ከጥበቡ አለም ርቆ ወደ ሹፍርና ሙያ ይገባል፡፡ በሹፍርናም ለ20 ዓመታት ያህል ሰርቷል፡፡ በሹፍርና በአገለገለበት ዘመንም የተለያዩ የሀገራችን አካባቢዎችን የዞረ ሲሆን በርካታ ውጣ ውረዶችን እና ገጠመኞችን አስተናግዷል፡፡ (በመሳሪያ ከማስፈራራት እስከ መደብደብ ድረስ……) ይህ ሰው አርቲስት ተዘራ ለማ ነው፡፡

   ለ20 ዓመት የሰራበት የሹፍርና ሙያ ወደ ትወናው አለም እንዲገባ በር ከፍቶለታል፡፡ በቶም ቪዲዮ አማካኝነት ውሳኔ ፊልም ሲሰራ በሹፌርነት ሰርቶ ነበር፡፡ 500 ብር ቢነጋገርም ተባባሪነቱ እና ቅንነቱን ያየችው የቶም ቪዲዮ ባለቤት ገነት ተጨማሪ 500 ብር በማከል 1000ብር ተከፍሎታል፡፡ 

   እሱ ግን በክፍያው ደስተኛ አልነበረም፡፡ ምክንያቱም የትወና ፍላጎቱ እና በካሜራ እይታ ውስጥ ለመግባት መሻቱ ስላልተሳካለት፡፡ ይሁንና በሁለተኛው ቀን ለዚሁ ለውሳኔ ፊልም ቀረፃ አለም ገና በሄደበት ጊዜ አለቃ ሆኖ የሚሰራበት አጭር ሲን (ትዕይንት) ይሰጠዋል፡፡ 

  በዚህ ጊዜ አርቲስት ተዘራ ደስታው ወደር አልነበረውም፡፡ ይህ ነበር እንግዲህ ፊልምን እና አርቲስት ተዘራን ያስተዋወቃቸው፡፡ የልጅነት ሀሳቡ እና ምኞቱ ሰመረ፡፡ “ወሳኔ ፊልም” የበኩር ስራው ሆነ ማለት ነው፡፡ ከዚያም ከኩርባው በስተጀርባ የተሰኘ ፊልም ላይ ተውኗል፡፡ አርቲስት ተዘራ ለማ እስካሁን ከ20 በላይ ፊልሞች ላይ የተለያዩ ገፀ ባህሪትን ተጫውቷል፡፡ እነርሱም ፡- 
         -  ውሳኔ   -  ከኩርባው በስተጀርባ  -  ፍቅር ባጋጣሚ  -  ታሰጨርሺኛለሽ
       -  ፍቅር በይሉኝታ  - አልወድሽም   - ወንድሜ ያቆብ  - ኢንጂነሩ
          - ጥቁር እና ነጭ   - ፍፃሜው       - ሀማርሻ         - ሰውዬው
          -  የፍቅር ቃል      - ቪዳ          - ባዶ ነበር        - ፀሀይ የወጣች ቀን
          -  ጣምራ           - የበኩር ልጅ   - እሷን ብዬ       - ጉደኛ ነች
      - ሰበበኛ       - ዘውድና ጎፈ ፤በመሰራት ላይ ያሉ እና በቅርብ የሚወጡ ፡- ታላቁ ሩጫ ፣ ሰንሰለት ፣ እስክትመጪ ልበድ እና ሌሎችም ይተቀሳሉ፡፡ በአለም ሲኒማ የታየ “የእኔ እውነት” የተሰኘ ትያትር ሰርቷል፡፡ ይህ ትያትር ሀገር ፍቅር ለመታየት ወረፋ እየጠበቀ ነው፡፡ የኩኩ ሰብስቤ ቻልኩበት ክሊፕ ላይም ተሳትፏል፡፡

   
    በ “በኩር ልጅ” ፊልምም ባሳየው የገፀ ባህሪ አጨዋወት በ9ኛው የኢትዮጵያ ፊልም ፌስቲቫል ላይ “የአመቱ ምርጥ ተዋናይ” ተብሎ ተሸልሟል፡፡ በ”ፍቅር ቃል” ፊልም ላይም እንዲሁ ባሳየው ብቃት ከእነ ቤተሰቡ የዋንጫ ሽልማት ተበርክቶለታል፡፡ የከፍተኛ 18 ኪነት ቡድን ውስጥ ከተዋወቃት ባለቤቱ ተወዛዋዥ ፋንቱ አርጋው በ1977ዓ.ም ጋብቻውን የፈፀመው አርቲስት ተዘራ ለማ አራት ልጆችን አፍርቷል፡፡ ልጆቹም የእሱን ፈለግ የተከተሉ ሲሆን በተለይ ሰላም የተባለችው ልጁ ከ “ኩርባው በስተጀርባ” ፊልም ላይ አብረው ሰርተዋል፡፡


   በ1954ዓ.ም ፍቼ የተወለደው አርቲስት ተዘራ ለማ እድገቱ እዚሁ መዲናችን አዲስ አበባ ርቼ አካባቢ ነው፡፡ ይህ አርቲስት ወደ ጥበቡ ከገባበት ጊዜ ጀምሮ በፊልም ፣ በቴሌቭዥን ተከታታይ ድራማ ፣ በትያትር እና በልዩ ልዩ ማስታወቂያዎች ላይ ሰርቷል፡፡ በቀጣይም በአዳዲስ ስራዎቹ እንደምናየው ተስፋ አለኝ፡፡ ያሰብከው ይሳካ ፣ እድሜ ከጤና ጋር ይስጥህ ብያለሁ……

Wednesday, August 5, 2015

በትምህርት ቤት ስሟ እሌኒ አሁን ደግሞ ኩኩ .... ድምፃዊት ኩኩ ሰብስቤ


   ለስለስ ባሉ ዜማዎቿ ትታወቃለች ፡፡ በልጅነቷ የወንድ የሴት ሳትል ከእሷ ድምፅ ጋር የሚሄዱትን ሙዚቃዎች ተጫውታለች፡፡ የእነ ሙሉቀን መለሰ ፣ ጌታቸው ካሳ ፣ ሽሽግ ቸኮል ፣ እታገኘሁ ሀይሌ እና ብዙነሽ በቀለን እና ሌሎችንም ሰርታለች፡፡ በጊዜው ቆየት ያሉትን የእንግሊዘኛ ሙዚቃዎች በማድመጥ እስከማንጎራጎርም ደርሳ ነበር፡፡ ተወዳጇ ድምፃዊት ኩኩ ሰብስቤ፡፡

   ገና ከልጅነቷ ጀምሮ ት/ቤት ውስጥ በማንጎራጎር ነው ሙዚቃን የጀመረችው፡፡ በጊዜውም ሙሉቀንን ታደንቀው ስለነበረ ከአባቷ ከደጃዝማች ሰብስቤ ሽብሩ እየወሰደች (የእሳቸውን እና የሌሎችም) የግጥም ስራዎች ትሰጠው ነበር፡፡ ሙሉቀን መለሰም “ናኑ ናኑ ነይ” የተሰኘ አልበሙን ሲያወጣ በጊዜው የግጥም ደራሲዬ ኩኩ ሰብስቤ ናት እስከ ማለትም ደርሶ ነበር፡፡ 

   ድምፃዊት ኩኩ ሰብስቤ የመጀመሪያ የመድረክ ስራዋን ያቀረበችው ከአይቤክስ እና ዋልያስ ባንድ ጋር በመሆን በሂልተን ሆቴል በተዘጋጀ የተማሪዎች ፓርቲ ላይ ነበር፡፡ በዚህ መድረክ ላይ የታጨችው ድምፃዊት ኩኩ ራስ ሆቴል በ300ብር ተቀጥራ ከመሀሙድ አህመድ ጋር በአይቤክስ ባንድ አጃቢነት በሳምንት ሁለት ቀን ትጫወት ነበር፡፡ በኋላ ላይም ወደ ሂልተን ሆቴል በመዛወር በ600ብር በየቀኑ ከዋልያስ ባንድ ጋር ትሰራ ነበር፡፡ በጊዮን ሆቴል ከሮሃ ባንድ ጋርም ትጫወት ነበር፡፡ በዚሁ ባንድ አጃቢነትም ከአለማየሁ እሸቴ ጋር “እንግዳዬ ነሽ” የተሰኘ የመጀመሪያ ስራዋን ለህዝብ አድርሳለች፡፡ ቀስ በቀስም ከሮሃ ባንድ ጋር ሶስት ያህል አልበሞችን አውጥታለች፡፡ 


    ከተለያዩ አንጋፋ ድምፃውያን ጋር በቅብብሎሽ የሰራቻቸውም በሮሃ ባንድ የተቀናበሩ ናቸው፡፡ በአጠቃላይ ከአይቤክስ ፣ ዋልያስ  ፣ ሮሃ ፣ ኢትዮ ስታር እና ኤክስፕረስ ባንዶች ጋር በተለያዩ ጊዜያት ሰርታለች፡፡ በተለይ በትዝታ ስራዎቿ የምትታወቀው ድምፃዊት ኩኩ ሰብስቤ እስካሁን ስምንት ያህል አልበሞችን ሰርታለች፡፡ የመጨረሻ አልበሟ “ቻለኩበት” የተሰኘው ሲሆን በቀጣይም ሌላ አልበም ለመስራት እየተዘጋጀች ነው፡፡ በርከት ያሉ ነጠላ ዜማዎች ያሏት ሲሆን በቅርቡም “ሰበቤ” የተሰኘ ነጠላ ዜማዋን ለአድናቂዎቿ ጀባ ብላለች፡፡ እሳካሁን ባላት የካበተ ልምድ በሀገር ውስጥ እና በውጪ ኮንሰርቶቿን አቅርባለች፡፡ በጅቡቲ ጀምራ ሰነዓ፣ አቡዳቢ ፣ የመን ፣ ዱባይ ፣ አሜሪካ (በተለያዩ ከተሞች) እና በታላላቅ የአውሮፓ ከተሞች በመዘዋወር ሙዚቃዎቿን ለአድናቂዎቿ ተጫውታለች፡፡


     በ1980ዎቹ ወደ አሜሪካ የሄደችው ድምፃዊት ኩኩ ሰብስቤ በዚያው ለ15 አመታት ያህል ቆይታለች፡፡ በዚያም አንድ ልጅ አፍርታለች፡፡ ልጇ ካሌብ የአሜካ ዜግነት ያለው ሲሆን በቅርቡም የከፍተኛ ትምህርቱን ለመከታተለ ወደ አሜሪካ ይጓዛል፡፡ ልጇ ከፍተኛ የኳስ ፍቅር እንዳለው የምትናገረው ኩኩ በአንድ ወቅትም እንግሊዝ ሀገር ወስዳ የማንቺስተር ስታዲየምን አስጎብኝታዋለች፡፡ድምፃዊት ኩኩ የትምህርት ቤት ስሟ እሌኒ ሲሆን 12ኛ ክፍልን ስትጨርስ እና ዘፋኝ ስትሆን ነው “ኩኩ” የሚል ስሟን በጋዜጣ ያሳወጀችው፡፡
  

    በሀገር ውስጥ እና በውጭ በርከት ያሉ የምሽት ክለቦች ውስጥ ሰርታለች፡፡ በሀገር ውስጥ ፍራንክ አዲስ ፣ እንዲጎ . ሀረር መሶብ ፣ ወረገኑ ፣ ሀርለም ጃዝ ፣ ጃዝ አምባ ፣ በአሜሪካ ደግሞ ከቴዲ ማክ ጋር በመስከረም ሬስቶራንት ስራዎቿን ታቀርብ ነበር፡፡ አሁን ደግሞ “Club H2O እና ማማስ ኪቺን ሙዚቃዎቿን ትጫወታለች፡፡ እኔ በዚሁ ላብቃ ቀሪውን እናንተ ጨምሩበት ……  እድሜ እና ጤና ለተወዳጇ እና አንጋፋዋ ድምፃዊ ኩኩ ስብስቤ ተመኘሁ፡፡