Sunday, October 16, 2016

ለአሜሪካው ፕሬዚዳንት ቡሽ ደብዳቤ የፃፈች ኢትዮጵያዊት ….. አርቲስት አሰለፈች አሽኔ

   
  በውበቷና ቁመናዋ ዓይነ ግቡ የሆነችው ይህች ጉብል፤ በሀገር ፍቅር ቴአትር ቤት መድረክ በአካልም በሙያም አድጋ ታላቅ የጥበብ ሰው ለመሆን በቅታለች፡፡ አርቲስቷ ሁለገብ የጥበብ ሰው ስትሆን እጅግ በርካታ አጫጭርና ረጃጅም ቴአትሮችን በመድረክ ተጫውታለች። በግሏ እና ከሌሎች ጋር በማዜም በሸክላ ያስቀረፀቻቸው የሀገር እና የፍቅር እንዲሁም የትዝታ ዜማዎቿ ዘመን ተሻጋሪነታቸውን ያስመሰከሩ ናቸው። ዛሬም ቀልብ ይስባሉ፣ ልብ ያሸፍታሉ። የሀገር ፍቅሯ ንግስት አርቲስት አሰለፈች አሽኔ፡፡
   
  አሰለፈች በአገር ፍቅርና በብሔራዊ ቴአትር እንዲሁም በሲኒማ ራስ (ራስ ቴአትር) 80 በላይ ትያትሮች ላይ ተወናለች፡፡ ለአብነትም ኪሊዮ ፓትራ፣ ሮሚዮ እና ጁሌት ፣ ህይወት፣ አቦዘነች እኔ ላነቺ ክፉ፣ የቬኑሱ ነጋዴ ፣ ቀዩ ማጭድ፣ የልጃገረድ ሳሎን፣ የቆጡን አወርድ ብላ የብብቷን ጣለች፣ እብዷ ጎረቤቴ ፣ የህይወት መራራ ፣ ስራ ለሰሪው እሾህ ላጣሪው ፣ ዞሮ ዞሮ ሁሉም ዜሮ ፣ የሰው ሆዱ የወፍ ወንዱ ፣ ታጋይ ሲፋለም ፣ ቃልኪዳን አፍራሹ ውለታ ደምሳሹ ፣ ቆራጥ ፣ ያላቻ ጋብቻ ፣ የልጃገረድ ሳሎን እና ባሻዳምጤ ጥቂቶቹ ናቸው። በአብዛኞቹ ላይ መሪ ተዋናይ ሆና ነው የሰራችው፡፡ ሁለገቧ አርቲስት አሰለፈች አሽኔ በሲኒማ ራስ (ራስ ቴአትር) ከትወና ባሻገር በምክትል ስራ አስኪያጅነትም አገልግላለች ረጅሙን የስራ ዘመኗን በአገር ፍቅር ቴአትር ቤት ያሳለፈችው አርቲስቷ "አገር ፍቅር ለኔ አሳዳጊ ወላጄ ነው" ትላለች።


  አሰለፈች ከጓደኛዋ ጌጤነሽ ክብረት ጋር በ1968ዓ.ም አካባቢ “ሸገኔዎች” የተሰኘ የሙዚቃ ሸክላ አሳትማም ነበር ፡፡ “እየው ድማሙ  መቼ ነው  ዛሬ ነው  ፍቅር እንደገና  ሠላም ለምወድህ  እንዲህም እንዲህም  የንብ አውራ መሳይ  ሳብዬየሚሉ ዜማዎቿ ለአብነት ይጠቀሳሉ። “ማንጠግቦሽ” ተሰኘ ሙዚቃዊ ድራማም አላት፡፡ ከጥላሁን ገሠሠ፣ ከፍሬው ኃይሉ ከአሰፋ አባተ ፣ ከተማ መኮንን ፣ አሰፋ ሀይሌ ፣ ታጠቅ ገብረወልድ እና ከሌሎችም ታዋቂ ዘፋኞች ጋር በህብረት የዘፈነቻቸው በርካታ ስራዎች አሏት። በውዝዋዜ ረገድም ከነ ሙናዬ መንበሩ፣ ዘነበች ታደሰ እና ሌሎችም ጋር የሀገር ፍቅር ቴአትር ቤት መድረክን አድምቃለች። ታዳሚውን አስደስታለች። በሙያዋ ከሌሎች አርቲስቶች ጋር የተለያዩ አገራት በመሄድ ሙዚቃዎችን፣ ትርኢቶችንና ባህላዊ ውዝዋዜዎችን አሳይታለች። ለአፍሪካ አንድነት ድርጅት(አፍሪካ ህብረትም) ቀደም ሲል ከጓደኞቿ ጋር ህብረ ዝማሬ ሰርታለች፡፡ አሰለፈች ድምፃዊ ፣ ተወዛዋዥ እና ተዋናይ ከመሆኗም ባሻገር ግጥም እና ዜማ ትደርሳለች፡፡


  
  በሀገር ፍቅር ቆይታዋ በርካታ ስራዎችን የሰራችው አርቲስት አሰለፈች ለንጉሱ ፣ ለግርማዊት እቴጌ መነን እና ለውጪ መሪዎች በልዩ ልዩ በዓላት ወቅት አበባ እና ሌሎች ስጦታዎችን ታቀርብም ነበር፡፡ ንጉሱም በተለያዩ ጊዜያት ልዩ ልዩ ሽልማቶችን አበርክተውላታል፡፡ በ1937ዓ.ም ጅሩ ተወልዳ አዲስ አበባ ያደገችው አሰለፈች አሽኔ በተለያዩ የአለም ሀገራትም ስራዎቿን አቅርባለች፡፡ በአንድ ወቅትም በአሜሪካ ቆይታዋ ለፕሬዚዳንት ጆርጅ ቡሽ ደብዳቤ ፅፋ ከፕሬዚዳንቱም ለፃፈቻ ደብዳቤ ምላሽ ተሰጥቷታል፡፡ ከስፖርት እግር ኳስ እና ሩጫን ትወዳለች፡፡ ቀደም ባለው ጊዜም የቅድስ ጊዮርጊስ ክለብ ደጋፊ ነበረች፡፡ በሩጫው አለም እነ አበበ ቢቂላ ፣ ሀይሌ ገ/ስላሴ ፣ ደራርቱ ቱሉ ፣ ጥሩነሽ እና ገንዘቤ ዲባባን እንደምታደንቅም ገልፃለች፡፡


  በ1947 , በሀገር ፍቅር ቴአትር ስራን አሀዱ ያለችው አርቲስት አሰለፈች አሽኔ፤ በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ ብሄራዊ የኪነጥበብ ማዕከል ጥላ ስር ሆና ደጋፊ አጥተዉ የሚገኙትን አንጋፋሞያ ባልደረቦችዋን በመርዳት ላይ ትገኛለች፡፡  ረጅም እድሜ እና ጤና በመመኘት መረጃዬ በዚሁ አበቃሁ ቀሪውን እናንተ ጨምሩበት ….