Wednesday, March 11, 2015

የላሊበላ ፍልፍል አብያተ ክርስቲያን ……



  የላሊበላ ፍልፍል አብያተ ክርስቲያናትን ከአለት በመፈልፈል ያነፃቸው 11 የዛጉዬ ነገስታት አንዱ የሆነው ቅዱስ ላሊበላ /1120 - 1197 ./ ነው፡፡እነዚህ በአሰራር ጥበባቸው ዓለምን ያስደመሙና በመንፈሳዊ መዓዛ የተሞሉ አብያተ ክርስቲያናት፤ ከኢትዮጵያን የጥበብ መኩሪያ እና ሃብትነት ባሻገር የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የትምህርት፣የሳይንስ እና የባህል ድርጅት (ዩኔስኮ) 1979 የአለም ቅርስ ሆነው ተመዝግበዋል፡፡
 

  የቅዱስ ላሊበላ ፍልፍል አብያተ ክርስቲያናት፡- ቤተ ማሪያም ቤተ መድኃኔዓለም፣ ቤተ ደናግል፣ ቤተ መስቀል፣ ቤተ ደብረሲና፣ ቤተ ጎለጎታ፣ ቤተ አማኑኤል፣ ቤተ አባ ሊባኖስ፣ ቤተ መርቆሬዎስ፣ ቤተ ገብርኤል ወሩፋኤል፣ ቤተ ጊዮርጊስ የተሰኙ ቤተ ክርሰቲያናትን ይዟል፡፡ ቤተ ብረሲና አልፎ አልፎ ቤተ ሚካኤል በመባል ይጠራል፡፡ የቅዱስ ላሊበላ መካነ መቃበር የሚገኘውም በዚሁ በቤተ ደብረሲና ነው፡፡ ይሄ ቤተክርስቲያን ከቤተ ጎለጎታ ጋር ተያይዞ የታነፀም በመሆኑ(Twin Churches) ቤተ ሚካኤል ወጎለጎታ ተብሎ እንደ አንድ ስለሚቆጠር የላሊበላ አብያተ ክርስቲያናት ቁጥር 10 ናቸው የሚልም አስተያየት አለ፡፡
 

  ቤተ ማሪያም የቅዱስ ላሊበላ የመጀመሪያ ስራ ስትሆን ታህሳስ 29 የልደት በዓልም በዚች ቤተክርስቲያን ነው በድምቀት የሚከበረው፡፡ ቤተ መድኃኔዓለም በመጠን ከሁሉም የሚበልጥ እናአፍሮ አይገባየተባለው መስቀል የሚገኝበት ነው፡፡ ቤተ ጊዮርጊስ የሚባለው ደግሞ በመስቀል ቅርፅ የታነፀ እና ከሌሎቹ በተለየ ሁኔታ ረቂቅ የኪነ ህንፃ ጥበብ የተከናወነበት ነው፡፡


  ቅዱስ ላሊበላ እነዚህን አብያተ ክርሰቲያናት ለማነፅ 22 - 30 ዓመታት ፈጅቶበታል ይባላል፡፡ 1512 - 1518 ኢትዮጵያን የጎበኘው የፖርቹጋል ቄስ ፍራንሲስኮ አልቫሬዝ /ላሊበላን የጎበኘ የመጀመሪያው አውሮፓዊ/ እንዲህ ብሎ ነበር፡-ስለ ላሊበላ ፍልፍል አብያተ ክርስቲያናት ስራዎች ብዙ ብፅፍ የሚያምነኝ ሰው መኖሩ በጣም ያሳስበኛል፤ያስጨንቀኛል፡፡ እስካሁን ያልኩትንም እንኳን ቢሆንውሸት ነውየሚሉኝ፡፡ ነገር ግን የፃፍኩት በሙሉ እውነት ለመሆኑ በኃያሉ እግዛብሔር ስም እምላለሁ፡፡ እንዲያውም ከዚህ በላይ ማለት ይቻላል፡፡ ሆኖም በቀጣፊነት ስሜ እንደማይነሳ ተስፋ አደርጋለሁ፡፡
                                 ምንጭ - ህብር ኢትዮጵያ መፅሃፍ

No comments:

Post a Comment