Thursday, January 2, 2014

የአቶ መላኩ ፈንታ የት ይዳኝ ውዝግብ መቋጫ አገኘ


የአቶ መላኩ ፈንታ የክስ ሂደት በፌደራል ከፍተኛው ፍርድ ቤት መታየቱ እንዲቀጥል የፌደሬሽን ምክር ቤት ወሰነ፡፡

 ከፍተኛው ፍርድ ቤት 15 የወንጀል ችሎት በሙስና ወንጀል የተከሰሱት የአቶ መላኩ ፈንታ ክስ መታየት ያለበት በፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ይሁን ወይንስ በፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት በሚል ለፌዴሬሽን የቀረበውን የህግ ትርጉም ጥያቄ ለምክር ቤቱ አቅርቦ ነበር፡፡ ቤቱ ታህሳስ 24 /2006 ባካሄደው 4ኛ የም/ቤቱ ዘመን 4ኛ ዓመት 1ኛ አስቸኳይ ስብሰባ የአቶ መላኩ ፈንታ የክስ ሂደት በፌደራል ከፍተኛው ፍርድ ቤት መታየቱ እንዲቀጥል ውሳኔ አሳልፏል፡፡

    ውሳኔው የተላለፈው የፌደራል ፍርድ ቤቶች የማቋቋሚያ አዋጅ ቁጥር 25/88 አንቀፅ 8(1)ና የተሻሻለው የፀረ-ሙስና ልዩ የስነ-ስርዓትና የማስረጃ ህግ አዋጅ ቁጥር 434/97 አንቀፅ 7(1) ከህገ-መንግስቱ አንቀፅ 20(6)ና አንቀፅ 25ን ይጥሳሉ ወይንስ አይጥሱም የሚል የህግ ትርጉም ጥያቄ ለፌደራል ከፍተኛው ፍርድ ቤት በቀረበው መሰረት ነው፡፡ 

  የምክር ቤቱ የህገመንግስት አጣሪ ጉባኤም በህገመንግስቱ በተሰጠው ስልጣን መሰረት የቀረበለትን የትርጉም ጥያቄ መርምሮ ግለሰቦች የመንግስት ባለስልጣን በመሆናቸው ብቻ ከሌሎች ተለይተው በፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ክሳቸው እንዲታይ ማድረግ በህገ-መንግስቱ ለሰዎች የተሰጠውን በህግ ፊት እኩል የመሆን መብት ስለሚጥስ ተግባራዊ እንዳይሆኑ ወስኗል፡፡


  በሌላ በኩል ምክር ቤቱ ባደረገው ውይይት ባለሥልጣናት ጥፋት ሲፈፅሙ በጠቅላይ ፍርድ ቤት የሚጠየቁ ከሆነ ጥፋተኛ ወይም ነፃ ቢባሉ እነሱ ወይም መንግሥት ይግባኝ የሚሉበት ዕድል አይኖርም፡፡ ይህ ደግሞ ሁለቱንም ወገን የሚጎዳና የይግባኝ መብትን የሚፃረርነው፡፡ በመሆኑም ም/ቤቱ የመዳኘቱ ሂደት በፌደራል ከፍተኛው ፍርድ ቤት መታየቱን እንዲቀጥል ውሳኔ አሳልፏል ፡፡ ከፍተኛ ክርክር በተደረገበት የአቶ መላኩ ፈንታ የክስ ሂደት የት ይታይ ጥያቄ በ76 የምክር ቤቱ አባላት አብላጫ ድጋፍ ያገኘ ሲሆን በ8 ተቃውሞና 2 ድምፀ ተአቅቦም ቀርቦበታል፡፡

  የከተማ መሬት ይዞታ ምዝገባ ረቂቅ አዋጅም ህግ ሆኖ እንዲወጣ በፌዴሬሽን ምክር ቤት ይሁንታ እንዲያገኝ ከህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በተላከው ረቂቅ ሰነድ ላይም ምክር ቤቱ ውሳኔ አሳልፏል፡፡ በህገመንግስትና ክልሎች ጉዳይ ቋሚ ኮሚቴ በረቂቅ ሰነዱን ከመረመረ በኋላ የከተማ መሬት ይዞታ ምዝገባ ረቂቅ አዋጅም ህግ ሆኖ እንዲወጣ ለፌደሬሽን ምክር ቤት መላኩ ህገመንግስታዊ መሰረት እንዳለው በማየት ምክር ቤቱ ይሁንታውን ሰጥቷል፡፡

No comments:

Post a Comment