Sunday, January 26, 2014

የአዲስ-አዳማን የፍጥነት መንገድ ስራ ሲጀምር የሚያስተዳድረው ድርጅት ሊቋቋምለት ነው




  በቅርቡ ለትራፊክ ክፍት የሚሆነው የአዲስ-አዳማ የፍጥነት መንገድ ከተያዘለት ጊዜ ቀድሞ እንደሚጠናቀቅ የኢትዮጵያ መንገዶችባለሥልጣንአስታወቀ። የባለሥልጣኑ ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ በቀለ ንጉሴ  እንደገለጹት በዓይነቱ የመጀመሪያ የሆነውና በከፍተኛ ወጪ የተገነባው መንገዱ ከተያዘለት ጊዜ ቀድሞ በመጪው ሁለት ወራት ውስጥ ተጠናቆ ለአገልግሎት ክፍት ይሆናል።
   
 መንገዱ ሲጠናቀቅ አጠቃላይ ወጪው 800 ሚሊዮን ዶላር ሊደርስ እንደሚችል ጠቅሰው መንገዱ ጥቅም ላይ የሚውለው በክፍያ እንደሆነ ገልጸዋል። በአሁኑ ወቅት ከአዲስ አበባ አዳማ ለመጓዝ ከሦስት እስከ አራት ሰዓት እንደሚፈጅ የገለጹት ምክትል ዳይሬክተሩ የፍጥነት መንገዱ ጉዞን ከ50 እስከ 60 ደቂቃ የሚቀንስ በመሆኑ ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታው የጎላ እንደሆነ ነው ያብራሩት።
 

    በመንገዱ ለመጠቀም የሚጠየቀውን ክፍያ ሁሉም ተሽከርካሪዎች እንደሚፈጽሙና ነገር ግን በተለየ መልኩ መንገዱን በረዥም ጊዜ ለሚጠቀሙና ከአደጋ ጋር በተያያዘ ለሚጓዙ ፈቃድ የሚሰጥበት አሰራር እንሚኖር አመልክተዋል። ስለ ክፍያውና የመንገዱን የወደፊት እንቅስቃሴ የሚያስተባብር ድርጅት ስለሚቋቋምበት ሁኔታ የተካሄዱ ጥናቶች መጠናቀቃቸውንና በቅርቡም ለመንግሥት ውሳኔ የሚቀርብ መሆኑን ተናግረዋል።

   የማጠናቀቂያ ግንባታ ሥራ እየተሰራበት ያለው ይኸው የፍጥነት መንገድ በተለያየ ርቀት ካሜራዎች የተገጠሙለት ሲሆን የክፍያ ሠራተኛውንና አሽከርካሪውን፣ የመንገዱን የትራፊክ እንቅስቃሴ፣ እንዲሁም የአየር ሁኔታና ሌሎች የማስጠንቀቂያ መልዕክቶች የሚተላለፍባቸውን ስክሪኖች የሚቆጣጠር ጣቢያ ተደራጅቶለታል። 

   በሌላ በኩል እጅግ ከፍተኛ ወጪ ወጥቶበት የተገነባውና አዳዲስ ቴክኖሎጂዎች የተገጠሙለት የዚህ የፍጥነት መንገድ የተለያዩ ንብረቶች ለዘረፋ እየተጋለጡ መሆናቸውን ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ ጠቁመዋል። ይህን የወንጀል ድርጊት ለማስቆም ኅብረተሰቡን የማወያየትና ሌሎችም ተገቢ ሥራዎች እየተሰሩ ቢሆንም የንብረት ዘረፋው ጉዳይ እጅግ ፈታኝ እንደሆነ ተናግረዋል።

 ባለሥልጣኑ ንብረቱን ከዘራፊዎች ለመከላከል በቅርቡ በወሰደው እርምጃ ከፌዴራል ፖሊስ እንዲሁም ከኦሮሚያ ክልል መንግሥት፣ ከትራፊክ ፖሊስና ከአካባቢው ነዋሪዎች ጋር በመተባበር የጥበቃ ኃይል ቢሰማራም 100 ኪሎ ሜትር ርቀት የመሸፈኑ ነገር ፈታኝ እንደሆነበት ነው ያብራሩት። መንገዱ ለትራፊክ ክፍት ሲሆን ችግሩ ሊቃለል ይችላል የሚል ግምት ቢኖርም ስጋቱን ግን ሙሉ በሙሉ የሚያስወግደው ባለመሆኑ የተጠናከረ ጥበቃ ሥርዓት መፍጠር እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
 

  የአዲስ-አዳማ የፍጥነት መንገድ የግንባታ ሥራው የተጀመረው ከሦስት ዓመት በፊት በቻይና የመንገድ ሥራ ተቋራጭ ነበር።  
                                                  ምንጭ ፡-  ኢዜአ

No comments:

Post a Comment