Saturday, December 27, 2014

ለእይታ ያልታደሉ ቅርሶች ...



  የታዕካ ነገስት በዓታ ለማርያም ህንፃ ቤተ ክርሲቲያንን ለመስራት 10 ዓመታትን ፈጅቷል፡፡ ከ1910 እስከ 1920 ዓ.ም ድረስ፡፡ ህንፃ ቤተ ክርስቲያኑን  ያሰሩት የዳግማዊ አፄ ምኒልክ 3ኛ ልጅ የነበሩት ግርማዊት ንግስተ ነገስት ዘውዲቱ ምኒሊክ ናቸው፡፡ ንግስት ዘውዲቱ ይህን ህንፃ ቤተ ክርስቲያን እና በውስጡ ያለውን ሙዚየም ለአባታቸው መልካም ስራ መታሰቢያ እና ለአፅማቸው ማረፊያ በማለት እንዳሰሩት ይነገራል፡፡


  በቤተ ክርስቲያኑ የውስጥ ክፍል አራቱም አቅጣጫ የሀገሪቱን ታሪክ የሚያወሱ ስዕሎችን ተመልክተው  ወደ ምድር ቤት ሲወርዱ አነስ ያለችውን የበዓታ ሙዚየም ያገኛሉ፡፡ በዚች አነስተኛ ሙዚየም ውስጥ ለአይን የሚያስገርሙ ተጎብኝተው የማይጠገቡ ቅርሶችን ያያሉ፡፡ እነሱም የትላንት የጥበብ እድገታችን እና የስልጣኔ ጉዞአችን የት ድረስ እንደነበር ያመላክታሉ፡፡

  በቅድሚያ 1924 ከግሪክ ቤተ ክርስቲያን ለግርማዊት ንግስተ ነገስት ዘውዲቱ ምኒልክ የተበረከተላቸውን የእየሱስ ክርስቶስ የግንዘት ምስል ከመስተዋት በተሰራ ሳጥን ያገኛሉ፡፡ ከዚህ እይታ ባሻገር አይንዎትን ሲያማትሩ ሶስት መካነ መቃብሮችን በመደዳ ተሰድረው ይመለከታሉ፡፡ / የዳግማዊ አፄ ምኒልክ የግርማዊት እቴጌ ጣይቱ ብጡል የንግስተ ነገስት ዘውዲቱ ምኒልክን/፡፡ ከዚህ ፈንጠር ብለው ደግሞ የግብፁን ሊቀ ጳጳስ የአቡነ ማቴዎስ እና የልዕልት ፀሀይ ኃይለስላሴን መካነ መቃብሮች ያገኛሉ፡፡ 

   እነዚህ ብቻ አይደሉም በሙዚየሙ ውስጥ 100 አመት በላይ እድሜ ያላቸው ወንበሮችን አይተው ይደነቃሉ፡፡ እነዚህ ወንበሮች አንዱ የዳግማዊ አፄ ምኒልክ ተንቀሳቃሽ ወንበር ሲሆን በአደዋ ጦርነት ጊዜም አብሯቸው ሄዶ ሲያስቀድሱ ይጠቀሙበት እንደነበር ይነገራል፡፡ ሌላው ወንበር ደግሞ የግርማዊት ንግስተ ነገስት ዘውዲቱ ሲሆን እሱም ንግስቲቱ ዳዊት ሲደግሙ ይጠቀሙበት እንደነበር የሙዚየሙ አስጎብኚ ይገልፃሉ፡፡ አይንዎትን ዘወር አድርገው ቀና ሲያደርጉ ደግሞ 115 አመት በላይ እድሜ ያላቸው እና ከትልቅ ግንድ በሰው ቁመት ልክ ተፈልፍለው የተሰሩ ሁለት ወርቃማ ቅብ ያላቸው ዙፋኖችን ያያሉ፡፡ 


  አፄ ምኒልክ እና እቴጌ ጣይቱ ይጠቀሙባቸው የነበሩ የወርቅ ጥላዎች ፣ የአፄ ኃይለስላሴ እና የእቴጌ መነን ወንበሮች ፣ የነገስታቱ አልባሳት እንዲሁም ከሀገር ውስጥ እና ከውጪ የተበረከቱ ልዩ ልዩ ስጦታዎችም አሉ፡፡ ከ100 አመት በላይ የቆየ ነጋሪትንም በሙዚየሙ ውስጥ ይመለከታሉ፡፡ ዳግማዊ አፄ ምኒሊክይህን ነጋሪት ዘመቻ አልያም ለየት ያለ ነገር ሲኖር በማስጎሰም ለህዝባቸው ጥሪ ወይም መልዕክት ያስተላልፉበት ነበር፡፡ ከእነዚህም በተጨማሪ በሙዚየሙ ባሉ ሁለት መደርደሪያዎች በርካታ የብራና መፅሃፍትን ይገኛሉ፡፡


  በመጨረሻ የሌላ ሀገር ጎብኚ የእኛን ታሪክ ለማወቅ ሀገር አቋርጦ ፣ ባህር ተሸግሮ ሲመጣ ፣ እኛ ግን አጠገባችን ያለውን ለመጎብኘት ፣ ታሪካችንን ለማወቅ እንዴት ተሳነን? ምላሹን ለእናንተ ትቻለሁ………!!!

No comments:

Post a Comment