Wednesday, April 10, 2013







  በኢትዮጵያ  በተለያዩ  የኢንቨስትመንት  ዘርፎች ላይ እየተንቀሳቀሰ የሚገኘው የቻይናው ጉአንግዶንግ ቹአን ሁ ግሩፕ የተባለው ኩባንያ  በመዲናችን በርዝመቱ ቀዳሚ የሆነ ህንፃን  ሊገነባ መሆኑን  ገልጿል ።
   ኩባንያው ያወጣው ጋዜጣዊ መግለጫ  እንደሚያስረዳው  በከተማዋ  ኡራኤል አካባቢ ለሚገነባውና ለሆቴል  ግልጋሎት  ለሚውለው ህንፃ  የሚሆን 41 ሺህ ስ/ካሬ ሜትር  ቦታን ከከተማዋ አስተዳደር አግኝቷል ። በዲዛይኑ  መሰረት  ህንፃው 99  ወለሎች ሲኖሩት  448 ሜትር  ከፍታም  እንዲኖረውም ነው የታቀደው ።
  ኩባንያው ከሶስተኛ እስከ 55ኛ  ፎቅ ያሉትን ክፍሎች ለቢሮ ግልጋሎት እንደሚውሉና  ከ78ኛ  አስከ 94ኛ ፎቅ የሚገኙትን ደግሞ  ባለ አምስት ኮከብ  ደረጃ  ያላቸው 217 የሆቴል  ክፍሎችን  እንደሚይዙ አስታውቋል ። የኢትዮጵያ ፣የቻይናና  የጣሊያን  ባህላዊ  የምግብ ዓይነቶችም  በህንፃው ላይ በሚገኙ አምስት ምግብ  ቤቶች ይዘጋጃሉ ።
  ህንፃው  የመኪና ማቆሚያዎች ፣ መናፈሻዎችንና  ቤተ መፅሃፍትንም  አካቶ የሚይዝ ይሆናል ። ኩባንያው የህንፃውን ስም የቀድሞው ጠቅላይ  ሚኒስትር  መለስ ዜናዊን ለመዘከር በእርሳቸው ስም ለመሰየምም እቅድ አለኝ ብሏል ።

No comments:

Post a Comment