Thursday, April 27, 2017

ሰዎች ትዳር ለምን ይፈራሉ….. ?

  
   “... ትዳር ማለት ችግርን ወይም ተግዳሮትን ለሁለት የሚያካፍል፣ ደስታ እና ስኬታችንን ደግሞ በሁለት የሚያበዛ ወዳጅ ማግኘት ማለት ነው፡፡...” ምንም እንኳን በጋብቻ መልካምነት ላይ ብዙዎች ቢስማሙም ጥቂት የማይባሉ ሰዎች በግል ህይወታቸው ከተለማመዱት፣ በአካባቢያቸው ካዩት እና ከሰሙት ነገሮች በመነሳት ስለ ጋብቻ አሉታዊ የሆነ አስተሳሰብን ሊያራምዱ ይችላሉ የሚሉት ባለሙያው የሰዎች ድርጊት በአብዛኛው የሚወሰነው በአእምሮአቸው ውስጥ ባለው አስተሳሰብ በመሆኑ ሰዎች የጋብቻን መልካምነት እንዳይረዱ ብሎም የተሳሳተ አመለካከት እንዲኖራቸው ምክንያት የሚሆኑ አስተሳሰቦች ወይም ልምምዶች በርካታ እንደሆኑም ጨምረው ይጠቅሳሉ፡፡
 


   ሁሉም ሰው ጋብቻን አይፈራም፡፡ ነገር ግን ጋብቻን የማይፈልጉ እና ሀላፊነት ወዳለበት ህብረት ለመግባት የሚፈሩ ሰዎች ይኖራሉ፡፡ እንግዲህ ይህ ፍርሀት ወይም አሉታዊ የሆነ አመለካከት የእራሱ የሆነ መነሻ ምክንያት ይኖረዋል፡፡ የሁሉም ምክንያት ግን ተመሳሳይ ላይሆን ይችላል፡፡  እነዚህ ምክንያቶች እጅግ በርካታ እና የተለያዩ ቢሆኑም የቤተሰብ የኋላ ታሪክ አንዱ እና ግንባር ቀደም ከሚባሉት ውስጥ ሊጠቀስ የሚችል ነው፡፡ ሰዎች በቤተሰቦቻቸው የትዳር ህይወት ውስጥ ከሚያዩት ነገር በመነሳት ስለጋብቻ መልካም ወይም መጥፎ አመለካከት ሊኖራቸው ይችላል፡፡


   ጋብቻ የተጋቢዎች የመጨረሻ ግብ ሳይሆን የጥምረት ጉዞ መጀመሪያ ነው፡፡ ይህ ጉዞ ተጋቢዎች የብቻቸው የሚያደርጉት ሳይሆን በጥምረት የሚያደርጉት የሕይወት ዘመን ጉዞ ነው፡፡ በዚህ ጉዞ ውስጥ ሁለቱም እያደጉና እየጎለመሱ ይሄዳሉ፡፡ ከስህተታቸው እየተማሩና አንዱ ለሌላው ያለው ፍቅር እየጎለበተ የሚሄድበት ጉዞ ነው፡፡ ይህ ጉዞ ረዥም መንገድ ስለሆነ ብዙ አስደሳች እንዲሁም አሳዛኝ ነገሮች ያጋጥማሉ፡፡ በዚህ ጉዞ ፈቃደኝነታቸው ካለ በውጣ ውረዶች ውስጥ አንድነታቸውን ጠብቀው ደስታውንና ሐዘኑን እየተካፈሉ መሄድ ይችላሉ፡፡

    ላገባችሁም ሆነ በቅርቡ ወደ ትዳሩ አለም ለምትገቡ መልካም ትዳር ተመኝተናል!!!

ኢትዮጵያዊው አስትሮ ፊዚስት ዶ/ር ለገሰ ወትሮ ከዚህ ዓለም በሞት ተለዩ፡፡


   ዶ/ ለገሰ በቀድሞ አጠራር በአሩሲ ክፍለ ሀገር ስሬ ወረዳ 1942 . ነበር የተወለዱት፡፡ የአንደኛ እና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን በተወለዱበት አካባቢ ተከታትለዋል፡፡ የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን ከቀዳማዊ ኃይለስላሴ (የአሁኑ አዲስ አበባ  ዩንቨርሲቲ) ያገኙት / ለገሰ ሁለተኛ ዲግሪያቸውንም በዚሁ ዩኒቨርስቲ  በፊዚክስ ትምህርት አጠናቀዋል፡፡  በውጭ ሀገር ከሼፊልድ ዩናይትድ  በፊዚክስ ሁለተኛ ዲግሪያቸውን ያገኙ ሲሆን ሶስተኛ ዲግሪያቸውን ደግሞ ከከሎምቢያ ስቴት ዩንቨርሲቲ በአስትሮኖሚ/አስትሮፊዚክስ አግኝተዋል፡፡


 በንፋስ ስልክ አጠቃላይ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ለአራት ዓመታት ያስተማሩት / ለገሰ 40 ዓመታት ያህል በመምህርነትና በተመራማሪነት በአዲስ አበባ ዩንቨርሲቲ አገልግለዋል፡፡ዶ/ ለገሰ ወትሮ  አስትሮኖሚ/አስትሮ- ፊዚክስ ምርምር የሚታወቁ እና አዳዲስ ፅንሰ - ሀሳቦችን ያበረከቱ ታላቅ ሰው ነበሩ ብሏል የአዲስ አበባ ዩንቨርሲቲ መግለጫ፡፡


  ዶ/ ለገሰ ወትሮ በኤፍ ኤም አዲስ 97.1 “የህዋ ሳይንስ” የተሰኘ ፕሮግራም በማዘጋጀት ለአድማጮች ስለ ህዋ ሳይንስ ሰፊ ግንዛቤ ይሰጡም ነበር፡፡ በተወለዱ 67 ዓመታቸው ያረፉት / ለገሰ የአንድ ወንድና የሁለት ሴት ልጆች አባት ነበሩ፡፡ የዶ/ ለገሰ ወትሮ ስርዓተ ቀብር ሚያዝያ 20/2009 ከቀኑ 900 ሰዓት በጴጥሮስ መካነ መቃብር ይፈጸማል ሲል አዲስ አበባ ዩንቨርሲቲ አስታውቋል፡፡
       ለቤተሰቦቻቸው እና ወዳጅ ዘመዶቻቸው መፅናናትን እንመኛለን!!!

Thursday, April 20, 2017

ታላቁ የስነ ስዕል ባለሟል ፣ የስነ ጥበብ ት/ቤት መስራች እና የመጀመሪያው መምህር .....


  አያታቸው ሰዓሊ አለቃ ህሩይ ልጃቸው ፈለገሰላም በጉጉስ ጨዋታ ወቅት በአደጋ ህይወታቸው በማለፉ በሀዘን ላይ ናቸው፡፡ ሀዘናቸው ይበልጥ መሪር የሆነው ደግሞ ልጃቸው ገና 40 ቀን ብቻ ያስቆጠረ ጨቅላ ህፃን እንደ ወለዱ በመሞቱ ነው፡፡ እናም አያቱ አለቃ ህሩይ ህፃኑን ትኩር ብለው ቢመለከቱት ሟች ልጃቸውን መስሏቸው ተፅናኑ፡፡ አልሞተም ልጄ አሉ፡፡ አለ ልጄም ሲሉ ተናገሩ፡፡ በዚህ ምክንያት የህፃኑ መጠሪያ ለአባቱ ማስታወሻ እንዲሆን “አለ” ተባለ፡፡ አለፈለገሰላም ህሩይ ይህ የሆነው የዛሬ 93 ዓመት ፣ ሀምሌ 24 1915ዓ.ም ነው፡፡
   

  አለቃ ህሩይ የነገስታት እና መንፈሳዊ(መለኮታዊ) ስዕሎችን በመስራት የተደነቁ ነበሩ፡፡ የልጅ ልጃቸው “አለ”ም የአያታቸውን ፈለግ በመከተል ከጥበብ እና ከስራ ሁሉ ስዕልን አስበልጠዋል፡፡ በአሜሪካ ቺካጎ የከፍተኛ ስነ ጥበብ ትምህርታቸውን ተከታትለው የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን አግኝተዋል፡፡ በ1947ዓ.ም ከአሜሪካ የትምህርት ቆይታቸው በኋላ ወደ ኢትዮጵያ ተመልሰው የዘመናዊ ስዕል ት/ቤት እንዲቋቋም አድርገዋል፡፡  የስነ ጥበብ እና ዲዛይን ት/ቤት መስራች ሲሆኑ በዳይሬክተርነትም  ከ1951 - 1966ዓ.ም አገልግለዋል፡፡


   ለዘመናዊ የኢትዮጵያ ስነ ስዕል ትምህርት መሰረት የጣሉት አለ ፈለገሰላም የስዕል ጅማሮአቸው መልክዓ ምስል (ፖርትሬት ኪነ ንድፍ) ላይ ያተኮረ ነበር፡፡ እውነታዊ ፣ ባህላዊ እና ትውፊታዊ ስራዎች ላይ ያተኩራሉ፡፡ ብዙዎቹ ስራዎቻቸውም በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ይገኛሉ፡፡ በርካታ የቤተ ክርስቲያን ግድግዳዎች እና ጉልላቶች በእኚህ ስመ ጥር ሰዓሊ ቡርሾች የተዋቡ ናቸው፡፡ ሂልተን ሆቴልም የሚገኝ ስዕል አላቸው፡፡


   ከስነ ጥበባት እና ዲዛይን ት/ቤት ዳይሬክተርነታቸው ባሻገርም በቅርስ ጥናት እና ጥበቃ የቅርስ ጥበቃ ክፍል ሀላፊም ሆነው ሰርተዋል፡፡ በተደጋጋሚ ከልዩ ልዩ አደጋዎች በመትረፋቸው ከሞት የተፋጠጡ የአልሸነፍ ባይነት ተምሳሌት ተደርገው ይቆጠራሉ፡፡



    በኢትዮጵያ ትውፊታዊውን ከዘመናዊ አሳሳል ጋር አዋህደው የሚሰሩት አለ ፈለገሰላም በሙያቸው ላበረከቱት አስተዋፅኦም የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የስነ ጥበባት እና ዲዛይን ት/ቤት በስማቸው እንዲጠራ ተደርጓል፡፡ “አለ የስነ ጥበባት እና ዲዛይን ት/ቤት” ተብሎም ተሰይሟል፡፡ በህይወት ዘመናቸው ለነበራቸው አበርክቶም ከሀገር ውስጥ እና ከውጪ ልዩ ልዩ ሽልማቶችን አግኝተዋል፡፡ በ93 ዓመታቸው ይህቺን አለም የተሰናበቱት አለ ፈለገሰላም በደብረሊባኖስ ገዳም ሀምሌ 6፣ 2008 ዓ.ም የቀብር ስነ ስርዓታቸው ተፈፅሟል፡፡

Monday, April 17, 2017

ከተላላኪነት እስከ ብሄራዊ ባንክ ገዢነት…. የባንክ ሙያ ተፈራ ደግፌ


“ሀገርን መውደድ የሚገለፀው በመስራት ነው፡፡ ቀደም ሲል የነበሩት በአብዛኞቹ ውጭ ሀገር ተምረው ወደ ሀገራቸው የመመለሱ ሁኔታ ሰፊ ነው፡፡ ውጭ የመቅረት ሀሳብም አልነበረንም፡፡ ይህ ለሀገራችን የነበረንን አክብሮት እና ፍቅር የሚያሳይ ነው፡፡ እናም ወጣቱን ትውልድ ይህንኑ ነው የምለው፤ በዚች ምስኪን (ድሃ) ሀገር ውጭ ተምሮ በቂ ደምወዝ ፣ ምቹ የስራ ሁኔታ የለም ብሎ መቅረት የታሪክ እና የትውልድ ተጠያቂነትን ያስከትላል፡፡”  ክብር ዶ.ር ተፈራ ደግፌ

  ስራ የጀመሩት በኢትዮጵያ መንግስት ባንክ ሲሆን ፣ ባንኩ በተቋቋመ በዓመቱ ነው፡፡ አቶ ተፈራ ባንኩ የውጭ ትምህርት እድል (ስኮላርሺፕ) ሰጥቷቸው ከተማሩት ኢትዮጵያውያን መካከል አንዱ ናቸው፡፡ በወቅቱእርሳቸውና በጓደኞቻቸው ጥረት የተቋቋመው የውጭ ሃገር ተማሪዎች ህብረት የመጀመሪያው ሰብሳቢ የነበሩ ሲሆን በቀጣይም ግርማሜ ንዋይ ስልጣኑን እንደተረከቡም ይነገራል።
  አቶ ተፈራ 1950ዎቹና 60ዎቹ ውስጥ የኢትዮጵያ የባንክ ስራ ስርአትን ከዘረጉት ሰዎች መካከል አንዱ ነበሩ። በኢትዮጵያ የመጀመሪያው የመንግስት ባንክ ዋና ስራ አስኪያጅ ሆነው ስራቸውን ከጀመሩ በኋላ በሀገሪቱ የባንክ ዘርፍ እንዲያድግ፤ በርካታ ቅርንጫፎች እንዲከፈቱ እንዲሁም የባንክ ሙያ ማሰልጠኛ እንዲቋቋም አድርገዋል፡፡
  በኢትዮጵያ መንግስት ባንክ፤ በሱዳን የኢትዮጵያ ባንክ፤ በመድህን ድርጅትበሲቪል አቬሽን ዳይሬክተርነት፤ በመጨረሻም የኢትዮጵያ ብሄራዊ ባንክ ገዢ ሆነው ሰርተዋል፡፡ በአብዮቱ ዘመንም ታስረው እንደነበር ይነገራል። ከእስር ከተፈቱ በኋላ፤ አቶ ተፈራ ደግፌ በቫንኩቨር በሚገኘው የብሪቲሽ ኮሉምቢያ ዩኒቨርስቲ ህግ ፋክልቲ የክብር ዶክትሬት የተሰጣቸው ሲሆን፤ ጡረታ ከወጡ በኋላ ረጅም ጊዜያቸውን የኖሩት በቫንኩቨር ካናዳ ነበር።
  ክብር ዶክተር ተፈራ ደገፌ በቶሮንቶ የሚገኘው ቢቂላ የሽልማት ድርጅት ባዘጋጀው የመጀመሪያ ሽልማት ላይ በህይወት ዘመን አስተዋጽኦ ተሸልመዋል፡፡ ATripping Stone, and Minutes of an Ethiopian Century የተሰኙ ሁለት መጻህፍትም ጽፈዋል።



  የሩሲያ፣ ጣሊያን ፣ ፈረንሳይ እና እንግሊዘኛ ቋንቋዎችን የሚናገሩት ዶ.ር ተፈራ ደገፌ በ2007ዓ.ም በ89 ዓመታቸው ከዚህ አለም በሞት ተለይተዋል፡፡ የሁለት ልጆች አባት ሲሆኑ በኑዛዜያቸው ላይ በኢትዮጵያ ያላቸው ንብረት ለፌስቱላ ሆስፒታል እንዲሰጥላቸው መናዘዛቸውም ተሰምቷል፡፡ በተገኘው አጋጣሚ የሀገር ባለውለታዎችን  ማስታወስ ተገቢ ነው፡፡                        
                                                ክብር እና ምስጋና ለባለውለታዎቻችን!!!