Sunday, April 28, 2013

የዳግማዊ ሚኒልክ ሞት!


ዳግማዊ አጼ ሚኒልክ ሕመሙ ፀንቶባቸው ነበርና ታህሳስ 3 ቀን 1906 ዓ.ም በዕለተ ዓርብ ሞቱ፡፡ ወዲያው እንደሞቱ የግቢ ሥራ ቤቶች ለቅሶ ጀምረው ነበር፡፡ ነገር ግን የልጅ ኢያሱ ባለሟሎች አገር እንዳይሸበር ሰግተው በቶሎ ዝም አሰኙዋቸው፡፡ አቤቶ ኢያሱ በዚያ ዕለት ፍልውሃ በመታጠቢያ ቤታቸው ውስጥ ነበሩ፡፡ የአባታቸውን የአጼ ሚኒልክ ሞት በሰሙ ጊዜ ደንግጠው ወደቤታቸው ወጡና ተቀመጡ፡፡ ሆኖም አገርእንዳይሸበር በማለት ሐዘናቸውን በይፋ አላሳዩም፡፡

       እንዲያውም አንዳች ሐዘን አለመኖሩን ለማስረዳትና ለማሳመን ሲሉ በማግስቱ ቅዳሜ ወደ ጃንሆይ ሜዳ ወጥተው ከአሽከሮቻቸው ጋር በፈረስ ጉግስ ሲጫወቱ ዋሉ፡፡ ይህም ለአገር ፀጥታ ሲባል ምሥጢር ሆኖ ተደበቀ፡፡ የአፄ ሚኒልክ አስክሬን አሽከሮቻቸው አምሮ በተሰራ በብረት ሳጥን አድርገው በቤተ መንግሥቱ ግቢ ባለችው በሥዕል ቤት ኪዳነ ምሕረት ቤተክርስቲያን አጠገብ በልዩ ሆኖ በተሠራውቤት ውስጥ በክብር አስቀመጡት፡፡

     ባለቤታቸው እቴጌ ጣይቱና ልጃቸው ወይዘሮ ዘውዲቱ ከዚያ ይለዩ ዳዊት እየደገሙ ያለቅሱ ነበር፡፡አፄ ሚኒልክ በ1881 መጋቢት ወር የኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥትነት ሥልጣን የያዙ ሲሆን በድምሩ24 ዓመት ከዘጠኝ ወራት በንጉሡ ነገሥትነት ሥልጣን ቆይተዋል፡፡ ባለቤታቸው እቴጌ ጣይቱና ልጃቸው ወ/ሮ ዘውዲቱ ስለምኒልክ ሞት ስንኝ ቋጥረዋል፡፡

የወ/ሮ ዘውዲቱ ግጥም
ቀድሞ የምናውቀው የለመድነው ቀርቶ
እንግዳ ሞት አየሁ ከአባቴ ቤት ገብቶ፡፡
እጅግ ያስገርማል ያስደንቃል ከቶ
ከሁለታችን በቀር እሚያውቀው ሰው ጠፍቶ፡፡
ምልክቱ ይህ ነው የንጉሥ ሞት ሐዘን
ጣይቱ ስትጨልም ጨረቃ ደም ስትሆን
ወልደውኛል እንጂ እኔ አልወለድሁዎ
አንጀቴን ተብትበው ምነው መያዝዎ፡፡
እጅግ አዝኛለሁ አላቅሰኝ አገሬ
የሁሉ አባት ሞቶ ተጎድተሃል ዛሬ፡፡
ድርቅ ሆኗል አሉ ዘንድሮ አገራችሁ
ዝናሙ ሲጠፋ ምነው ዝም አላችሁ፡፡
አሻግሬ ሳየው እንዲያው በሰው ላይ
መከራም እንደሰው ይለመዳል ወይ፡፡
ያች የሰጡኝ በቅሎ መጣባት ባለቤት
አልገዙም መሰለኝ ሊገለኝ ነው እፍረት፡፡

የእቴጌ ጣይቱ ግጥም
እምቢልታ ማስነፋት ነጋሪት ማስመታት ነበረ
ሥራችን
ሰው መሆን አይቀርም ደረሰ ተራችን፡፡

                       የ20ኛው ክ/ዘመን መባቻ ከመርስዔ ሐዘን ወልደቂርቆስ

No comments:

Post a Comment