የመለስ ፋውንዴሽን ተመሰረተ
ባለፈው ዓመት ከዚህ ዓለም በሞት የተለዩት የቀድሞው የኢፌድሪ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ በምጣኔ ሀብት እድገት ፣ በሰላምና ደህንነት መሻሻል እንዲሁም በዓለም ዓየር ንብረት ለውጥ ላይ ለሀገራቸው ፣ ለአፍሪካና ለዓለም ያበረከቱት አስተዋፅኦ ሁሌም የሚዘከር ነው ።
አቶ መለስ በማህበረ ኢኮኖሚ ዘርፍ ያበረከቷቸውን አስተዋፅኦዎችን ከመዘከር ባለፈ የእሳቸውን ራእይ አስቀጥሎ ለኢትዮጵያና ለአፍሪካ ብሎም ለዓለም ብልፅግና የሚሰራ ፋውንዴሽንም ዛሬ አዲስ አበባ ላይ ተመስርቷል ።
በምስረታ ጉባኤው ላይም ወይዘሮ አዜብ መስፍን የፋውንዴሽኑ ፕሬዚዳንት አቶ ካሳ ተክለብርሃን ደግሞ ምከትክ ፕሬዚዳንት በመሆን ተመርጠዋል ።
የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባፀደቀው አዋጅ መሰረት የተቋቋመው ይህ የመለስ ፋውንዴሽን በጅማሬው በኢትዮጵያ የሰብዓዊ እርዳታዎችን በማቅረብና የማህበራዊ አገለግሎቶች እንዲስፋፉ በማገዝ በሂደት ስራውን በቀሪው የአፍሪካ ክፍል ለማድረስ ራእይ ይዟል ። የአቶ መለስ ዜናዊ ራአይዎች እውን መሆናቸውን የሚያስቀጥሉ ተግባራትን ለመከወንም እቅድ ይዟል ።
ይህ ፋውንዴሽን በይፋ በአፍሪካ ህብረት አዳራሽ በተካሄደ ጉባኤ የተመሰረተ ሲሆን በጉባኤው ላይ የተገኙት የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ሀይለማርያም ደሳለኝ ታላቁ መሪ በመልካም ስነምግባርና እንከን በሌለዉ የስራ አፈፃፀም ብቃት አርዓያ ሆነው አልፈዋል ነው ያሉት ። ጠቅላይ ሚኒስትሩ አቶ መለስ ያለፉበት የትግል ሂደትና የምርጥ ሰራዎቻቸዉ አፈፃፀም ጥልቀት ያለዉ በመሆኑና ይህንንም ጠንቅቆ ማወቅ አገሪቱ ለጀመረችው የህዳሴ ጉዞ ስኬት ወሳኝ ስለሆነ ለጥናትና ምርምር ስራዎች የሚዉለዉን ይህን ፋዉንዴሽን ማቋቋም አስፈልጓል” ብለዋል ። የአቶ መለስ ዜናዊ ባለቤት ወይዘሮ አዜብ መስፍን በበኩላቸው ፋውንዴሽኑ የአቶ መለስ ስራዎች ለምርምር እንዲበቁና ነፃ የትምህርት እድሎችን በማመቻቸት የእሳቸው ራእይ እውን መሆኑን የሚያስቀጥል መሆኑን ተናግረዋል ።
በጉባኤው ላይ የአፍሪካ ህብረት ሊቀመንበር ድላሚኒ ዙማ ፣ የሱዳን ፕሬዝዳንት ኦማር አል በሽር ፣ የኡጋንዳ ፕሬዝዳንት ዩዌሪ ሙሶቮኒ ፣ የጅቡቲ ፕሬዝዳንት እስማዒል ኦማር ጊሌ ፣ የሶማሊያ ጠ/ሚ/ር አብዲ ፋራህ ሺርዶንና የቀድሞዉ የናይጀሪያ ፕሬዝዳንት ኦሊሴንጎ አባሳንጆ ንግግር አድርገዋል፡፡ ለፋዉንዴሽኑ ማቋቋሚያ ሱዳን ሁለት ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር ፣ ደቡብ ሱዳን አንድ ሚሊዮን ዶላር ፣ ጅቡቲ ግማሽ ሚሊዮን ዶላርና ኡጋንዳ 300 ሺህ ዶላር ለግሰዋል፡፡ በጉባኤው ላይ አራት የአቶ መለስ ዜናዊ ቤተሰብ አባላትን ጨምሮ 13 የሚሆኑ የፋውንዴሽኑ የቦርድ አመራር አባላትም ተመርጠዋል ።
የተመረጡ የቦርድ አባላት
ጀነራል ሳሞራ የኑስ ዶክተር ቴዎድሮስ አድሃኖም
አቶ ሱፊያን አህመድ ዶክተር ቴዎድሮስ ሀጎስ
አቶ ሽፈራው ሽጉጤ ወይዘሮ አስቴር ማሞ
አቶ አብዲ መሀመድ አቶ አህመድ ናስር ናቸው ።
የፋውንዴሽኑ ፕሬዚዳንት ሆነው የተመረጡት ወይዘሮ አዜብ መስፍን የተሰጣቸው ሀላፊነት ትልቅ ቢሆንም ከህዝብ ጋር በመሆን ተልዕኮውን ለማሳካት እረባረባለሁ ብለዋል ። አቶ መለስ እስከ ህልፈተ ህይወታቸው ድረስ እንዳገለገሉት እኛም እስከ ህልፈታችን ድረስ እንሰራለን ሲሉ ነው ቃል የገቡት ።
መጋቢት 28 ፣ 2005 (ኤፍ ቢ ሲ)
FBC (Fana Broadcasting Corporate S.C.) |
No comments:
Post a Comment