Monday, October 12, 2020

የቴአትር ምሁር፣ ደራሲና ተርጓሚ ተባባሪ ፕሮፌሰር ተስፋዬ ገሠሠ…

የመድረክ ፈርጥ፣ የተውኔት ፀሃፊ እና አዘጋጅ እንዲሁም ምሁር ናቸው፡፡ በሃገር ፍቅር እና በብሄራዊ ትያትር ቤት እንዲሁም በአዲስ አበባ ዩንቭርስቲ ባህል ማዕከል /ቤተ ኪነ ጥበባት ትያትር/ በሰራተኝነት እና በኃላፊነት ስርተዋል፡፡ ለረጅም አመታትም በመምህርነት ሙያ አገልግለዋል፡፡ በጥበቡ አለም 60 አመታት በላይ ያገለገሉ ሲሆን በእነዚህ አመታትም 100 በላይ የጥበብ ስራዎችን ለህዝብ አቅርበዋል፡፡ ተባባሪ ፕሮፌሰር ተስፋዬ ገሠሠ፡፡

 በ1929ዓ.ም በሀረርጌ  የተወለዱት ተሰፋዬ ገሠሠ የአንደኛ እና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን በተፈሪ መኮንን የተማሩ ሲሆን የመጀመሪያ ዲግሪያቸውንም ከአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ በ1951ዓ.ም አግኝተዋል፡፡ የሁለተኛ ዲግሪያቸውን ወደ አሜሪካ በመሄድ በቴአትር ጥበባት ተምረዋል፡፡ በውጪ ተምረው ከመጡ በኋላ በቀድሞው ቀዳማዊ ኃይለስላሴ /የአሁኑ ብሄራዊ ትያትር/ የመድረክ አስተባባሪ ወይም ስቴጅ ማናጀር ሆነው አገልግለዋል፡፡ 

የጋሽ ፀጋዬ ገ/መድህን “የእሾህ አክሊል” ትያትርን በአዘጋጅነት እና በመሪ ተዋናይነት ሰርተዋል፡፡ከዚህም በተጨማሪ በርከት ያሉ ስራዎች ላይ በተዋናይነት ፣ በደራሲነት እና አዘጋጅነት ተሳትፈዋል፡፡ ለአብነትም ፡-  

-    እዮብ     - ሀምሌት    -  ጴጥሮስ ያቺን ሰዓት   -  የእሾህ አክሊል

-    ኡመር   - ፍርዱን ለእናንተ  - የገና ገበያ   - የሺ   - ቴዎድሮስ

-    አሉላ አባነጋ  - አጎቴ ቫኒያ  - ሮሚዮና ዡሌት  - ባለካባ እና ባለዳባ

-    ጠልፎ በኪሴ  - ላቀችና ማሰሮ   -  አባት እና ልጆቹ እና ተሀድሶ ጥቂቶቹ ናቸው፡፡

ጋሽ ተስፋዬ ከተውኔት ፀሀፊነት: አዘጋጅነት እና ተዋናይነት ባሻገር በጋዜጠኝነት ሙያም በኢትዮጵያ ሬዲዮ "በኪነ ጥበባት ጉዞ" እና በኢትዮጵያ ቴሌቭዝን "ህብረት ትርኢት" የተሰኙ ፕሮግራሞች ላይ ሰርተዋል፡፡

 "ህልም እና እውነት" የተሰኘ የሬዲዮ ድራማ ድርሰታቸው 1988. በኢትዮጵያ ሬዲዮ የቀረበ ሲሆን እነወጋየሁ ንጋቱተክሉ ምናሴየወንድወሰን ገብረየሱስ እና ሌሎችም ተሳትፈውበታል፡፡ "አባት እና ልጆቹ" በተሰኘው ድርሰታቸው ደግሞ የፊልም ባለሙያ ሀይሌ ገሪማ(ፕሮፌሰር) ፣ ወንድወሰን ገብረየሱስ(ጋዜጠኛ) ፣  ታደሰ ሙሉነህ(ጋዜጠኛ) ፣ ዶክተር ዮናስ አድማሱ ፣ አያልነህ ሙላት እና ሌሎችም ተውነውበታል፡፡ የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ባህል ማዕከል/ቤተ ኪነ ጥበባት ወ ትያትር/ በሚመሰረትበት ወቅት ከፍተኛ አስተዋፅኦ አበርክተዋል፡፡ እነ አባተ መኩሪያ ፣ ወጋየሁ ንጋቱ ፣ ደበበ እሽቱ ሌሎች አንጋፋ እና ወጣት የጥበብ ሰዎችን በሙያ ቀርፀዋል/አፍርተዋል/፡፡ ጋሽ ተስፋዬ ገሠሠ "የመድረክ ተውኔት ነፍሱ ተዋናይ ነው" የሚል እምነትም አላቸው፡፡ በኪነ ጥበቡ ውስጥ ላበረከቱት አስተዋፅኦም ልዩ ልዩ ሽልማቶችን አግኝተዋል፡፡ በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የሚገኘው ባህል ማዕከልም በስማቸው ተሰይሞላቸዋል፡፡


10 በላይ መፅሃፍትን ለአንባቢ አድርሰዋል፤ እነሱም ፡-

1.  ዕቃው (ተውኔት) 1961ዓ.ም

2.  መተከዣ (ግጥም እና አጭር ልቦለድ) 1967ዓ.ም

3.  መልክአ ዑመር (አዛማጅ ትርጉም) በ1986ዓ.ም

4.  የወጣቱ ቨርተር ሰቀቀኖች (ትርጉም) 1997 ዓ.ም

5.  የዑመር ኻያም ታሪካዊ ልቦለድ (አዛማጅ ትርጉም) 1999ዓ.ም

6.  ጥንወት (ልቦለድ) 2000ዓ.ም

7.  ጎህ ሲቀድ (የግጥም መድብል) 2001ዓ.ም

8.  ሽልማቱ (ልቦለድ) 2002ዓ.ም

9.  ይሉኝታ እና ፍቅር (ልቦለድ) 2002ዓ.ም

10.  ረጅም ጉዞ ወደ ነፃነት (ትርጉም) 2009ዓ.ም

11.  የመጨረሽታ መጀመርታ (ልቦለድ) 2010ዓ.ም

12.  አሰብ እና ክበር (አዛማጅ ትርጉም) 2011ዓ.ም

13.  መደበሪያ (ልቦለድ) 2013 ዓ.ም - ይህ መፅሃፍ የ84 አመታቸውን ባከበሩበት ወቅት ለአንባቢያን ያበቁት ነው፡፡ ከእሳቸው ጋር ጥቂት ደቂቃዎችን ማሳለፍ መፅሃፍ ገልጦ እንደማንበብ ይቆጠራል፡፡  እኔም ይህን እድል በማግኘቴ በጣም ደስተኛ ነኝ፡፡ በነበረችን ጥቂት ደቂቃዎች ብዙ እውቀት አግኝቻለሁ፡፡ ግለ ታሪካቸው በሌላ ሰው እየተፃፈ እንደሆነ ሹክ ብላኛል፡፡ እሱ ለንባብ ሲበቃ ስለ እሳቸው ብዙ ነገር እናገኛለን ብዬም አስባለሁ፡፡ ከእሳቸው ስራዎች እና የህይወት ልምድ እኔ በጥቂቱ አጋራኋችሁ፤ ቀሪውን እናንተ ጨምሩበት….  

Monday, October 5, 2020

የእርቅ ፣ የምስጋና ፣ የሰላም እና የፍቅር በዓል ነው - ኢሬቻ

 ኢሬቻ የኦሮሞ ህዝብ በህብረት ወደ ተራራ እና መልካ ወይም በወንዝ ዳር ወርዶ ፈጣሪውን የሚለምንበት እና የሚያመሰግንበት ስርዓት ነው፡፡ይህ በዓል በተለያዩ ቦታዎች ቢካሄድም ዋናዋናዎቹ በሁለት ይከፈላሉ፡፡ እነርሱም “ኢሬቻ ቱሉ” እና “ኢሬቻ መልካ” በመባል ይታወቃሉ፡፡

የበጋ ወቅት አልፎ በበልግ ወቅት ላይ የሚከበረው የኢሬቻ በዓል “ኢሬቻ ቱሉ” ይባላል፡፡ይህም በበጋ ወቅት ሰው እና እንሰሳት በድርቅ ሲጠቁ ወይም ሲጎዱ ወደ ተራራ በመውጣት የበልግ ዝናብ እንዲዘንብላቸው ፈጣሪን የሚለማመኑበት ስርዓት ነው፡፡

ክረምት አልፎ በፀደይ መግቢያ ወቅት ላይ በቢሸፍቱ ከተማ - (ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ በአዲስ አበባ) በድምቀት የሚከበረው ደግሞ “ኢሬቻ መልካ” ይባላል፡፡ ይህ በዓል ከክረምት ወደ በጋ በሰላም ስላሸጋገራቸው እርጥብ ሳር እና አደይ አበባ በመያዝ ወንዝ ዳር ወጥተው ፈጣሪን የሚያመሰግኑበት ስርዓት ነው፡፡ በዚህ በዓል ላይም ከሀገር ውስጥ እና ከውጪ በርካታ ሰዎች የሚሳተፉበት በመሆኑ እንደ አንድ የቱሪዝም መዳረሻም ሆኗል፡፡

በዚህ በዓል ላይ ከህፃን እስከ አዋቂ ፣ ሴት ወንድ ሳይል ሁሉም በባህል አልባሳት አምረው እና ደምቀው ያከብራሉ፡፡ ሴቶች ደግሞ ከባህል አልባሳታቸው ባሻገር ስንቄን ይይዛሉ፡፡ ስንቄ በኦሮሞ ሴቶች ዘንድ ትልቅ ቦታ አላት፡፡ በተለይም የአርሲ እና የባሌ ሴቶች ሲዳሩ ከቤተሰቦቻቸው ፣ በክብር ተዘጋጅቶ የሚሰጣቸው ስጦታ ቢኖር ስንቄ ናት፡፡ ስንቄ የሴቶች መብት ማስከበሪያ ቀጭን በትር ናት፡፡ እናቶች ከቆዳ የተሰሩ አልባሳትን ለብሰው ፣ በአንገታቸው ጌጣጌጦችን አጥልቀው ፣ በእጃቸው ከእንጨት የተዘጋጀችውን ቀጭን በትር ይይዛሉ/ስንቄን ማለት ነው/፡፡

ስንቄ የተጣላን ማስታረቂያ፣ የሴቶች መብት ማስከበሪያ እና ሰላም እንዲሰፍን ማድረጊያ ናት፡፡ በመሆኑም በኦሮሞ ማህበረሰብ ዘንድ ለስንቄ የተለየ ቦታ እና ከበሬታ ይሰጣል፡፡ ለመነሻ ያህል እኔ ይህን ካጋራኋችሁ ቀሪውን እናንተ ጨምሩበት …..

Thursday, October 1, 2020

አቶ መላኩ አለበል የ2020 የአፍሪካ ቢዝነስ ሥራ አመራር ሽልማት አሸናፊ ሆኑ፡፡

 የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስትር አቶ መላኩ አለበል 2020 የአፍሪካ ቢዝነስ ሥራ አመራር ሽልማት አሸናፊ ሆኑ።

አቶ መላኩ ለዚህ የላቀ ሽልማት የበቁት የንግድና ኢንዱስትሪ አጠቃላይ መዋቅሩን ከፌዴራል እስከ ክልል እና ከተማ አስተዳደር ድረስ በማነቃነቅ በሀገር ደረጃ የተረጋጋ የግብይት ሥርዓት እንዲፈጠር በመሥራታቸው መሆኑን ሚኒስቴሩ አስታውቋል።

ሚኒስቴሩ አያይዞም ለኮቪድ-19 ተጽዕኖ የማይበገርና የሰከነ ንግድና ኢኮኖሚ እንዲኖር፣ የሀገር ውስጥ ንግድ እንዲያንሰራራ፣ ሀገራዊ የኤክስፖርት ንግድ እንዲነቃቃ በማድረጋቸው መሆኑንም አመልክቷል። አቶ መላኩ አምራች ኢንዱስትሪዎች የኮቪድ-19 ወረርሽኝ መከላከያ ግብዓቶችን እንዲያመርቱ በማድረግ አርአያነት ያለውን አመራር በመስጠታቸው መሆኑም ተገልጿል።


ሽልማቱ የንግድና ኢንዱስትሪ ሴክተር አመራሮችና ሠራተኞች የጋራ ጥረት፣ የንግዱ ማኅበረሰብና የአምራች ኢንዱስትሪ ተዋናዮች ከፍተኛ ተሳትፎና ትብብር ውጤት እንደሆነም ተመልክቷል።

የአፍሪካ ቢዝነስ ሥራ አመራር ሽልማት በተቋም፣ በሀገርና በአህጉር ደረጃ በቢዝነስ አመራር በላቀ ደረጃ ውጤታማ ለሆኑ ጥቂት መሪዎች የሚበረከት የመልካም ተግባር ዕውቅና ሽልማት መሆኑን ከንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።