Monday, December 14, 2015

ፊቼ - ጫምባላላ በዓለም ቅርስ ነት ተመዘገበ


  የሲዳማ ሕዝብ የዘመን መለወጫ በዓል ‹‹ፊቼ - ጫምባላላ›› የሰው ልጆች ወካይ ቅርስ (Representative List of Intangible Cultural Heritage of Humanity) ሆኖ መመዝገቡን ዩኔስኮ (የተባበሩት መንግሥታት የትምህርት የሳይንስና የባህል ድርጅት) አስታወቀ፡፡
ፊቼ፣ ኢትዮጵያ ከመስቀል በዓል ቀጥሎ ያስመዘገበችው ሁለተኛው ወካይ ቅርስ እንዲሆን የተወሰነው የዩኔስኮው በይነ መንግሥታዊ ኮሚቴ 10ኛውን ጉባኤ በናሚቢያ መዲና ዊንድሆክ ኅዳር 22 ቀን 2008 .. ባካሄደበት ጊዜ ነው፡፡ 

  ዩኔስኮ በድረ ገጹ እንዳስታወቀው፣ ... 2003 የማይዳሰሱ ባህላዊ ቅርሶች ጥበቃ ዓለም አቀፍ ስምምነት መስፈርትን ያሟሉና ከተለያዩ አገሮች የተወከሉ ተጨማሪ 19 ወካይ ቅርሶችም ተመዝግበዋል፡፡ ከአፍሪካ ቅርሷን ያስመዘገበችው ሁለተኛዋ አገር ጉባኤውን ያስተናገደችው ናሚቢያ ስትሆን የፍራፍሬ ፌስቲቫልዋ ይሁንታን አግኝቷል፡፡ 
በወርሀ ክረምት የሚውለው የፊቼ በዓል ታሪካዊ አመጣጥ በአፈ ታሪክ እንደሚወሳው ከጥንት ጀምሮ ሲሆን፣ የበዓሉ ስያሜ መነሻ ፊቾ ከምትባል ሴት ነው፡፡ ይህች ሴት በየዓመቱ ለወላጆቿና ወንድሞቿ ቡርሳሜ (የተነኮረ እና በቅቤ የተለወሰ ቆጮ) እና ወተት በቃዋዶ ዕለት ይዛ መጥታ እንደምትጠይቃቸውና የተዘጋጀውንም ቡርሳሜ ጎረቤት ተሰብስቦ ይጋበዝ እንደነበር ይነገራል፡፡ በአፈ ታሪኩ መሠረት ምግቡ ይበላ የነበረው ማታ ነው፡፡ ፊቼ ይህንን በተደጋጋሚ ስትፈጽም ቆይታ ትሞታለች፡፡ ቀደም ሲል የግብዣው ታዳሚ የነበሩ ሰዎች እርሷ የምትመጣበትን ጊዜ ጠብቀው በራሳቸው ለመደገስ ይስማማሉ፡፡ የግብዣውን ስያሜም በስሟ ፊቼ ብለው ጠሩት፡፡ በዚህ መሠረት የበዓሉ አከባበር በሁሉም ሲዳማ አካባቢ ፊቼ የሚል ስያሜ ተሰጥቶት እየተከበረ መምጣቱ እንደሚነገር፣ በዓሉን አስመልክቶ ኢትዮጵያ ለዩኔስኮ የላከችው መረጃ ያመለክታል፡፡


  የፊቼ - ጫምባላላ በዓል በርካታ ባህላዊና ማኅበራዊ ፋይዳዎች ያሉት፣ አገር በቀል የሆነ የዘመን አቆጣጠር ዕውቀትን አካቶ የያዘ ዓመታዊ የዘመን መለወጫ ክብረ በዓል ከመሆኑም በላይ፣ የሲዳማ ብሔር አንኳር የሆኑ ባህላዊ ገጽታዎች የሚንጸባረቁበት የማይዳሰስ (ኢንታንጀብል) ቅርስ መሆኑም ተመልክቷል፡፡ በሲዳማ ባህል ከትውልድ ትውልድ ሲተላለፍ የቆየው ‹‹ፊቼ›› የዘመን መለወጫ በዓል ከሁለት ሳምንት ላላነሰ ጊዜ በድምቀት የሚከበር ሲሆን፣ አከባበሩም ቅደም ተከተላዊ ሒደትና በደረጃ እየሰፋ የሚሄድ የጋራ የአከባበር አንድምታ ያለው ነው፡፡ በዓሉ በቤተሰብ ወይም በጎረቤት ደረጃ ተሰባስቦ በማክበር የሚያበቃ ሳይሆን፣ ሰፋ ባለ መልኩም በባህላዊ አደባባዩ ጉዱማሌ፣ በጋራና በድምቀት የማክበር ሒደትን የሚያካትት ነው፡፡
 
‹‹ፊቼ ፋሎ›› የሚባለው በጋራ በባህላዊ አደባባይ በድምቀት የማክበር ሥነ ሥርዓት ሲሆን፣ ኅብረተሰቡም በዓሉን የሚያከብረው በጎሳ በጎሳ በመሆን በተለያየ ባህላዊ ጭፈራና ባህላዊ አልባሳት ተጊጦ ነው፡፡ በክብረ በዓሉ የባህላዊው ሃይማኖት አባቶችና የጎሳ መሪዎች እንደ ማኅበራዊ ደረጃቸው በየተራ ንግግር ያደርጋሉ፣ ይመርቃሉ፣ ባሮጌው ዘመንና በአዲሱ ዘመን ላይ ያተኮሩ መልዕክቶች ያስተላልፋሉ፡፡ በጎው እንዲጎለብት አስከፊው እንዳይደገም ምክር አዘል መልዕክት ያስተላልፋሉ፤ ዘመኑ የሰላም፣ የብልጽግና የልማት ይሆን ዘንድ ቃለ ቡራኬ ያደርሳሉ፡፡
የሲዳማ ባህላዊ የዘመን መለወጫ በዓል ፊቼ - ጫምባላላ በዩኔስኮ የዓለም ቅርስ ውክልና ጊዜያዊ መዝገብ ውስጥ የገባው በሐምሌ 2006 .. እንደነበር ይታወሳል፡፡ ኢትዮጵያ ሐቻምና /2006ዓ.ም/ የመጀመሪያውን መንፈሳዊ ባህላዊ ቅርስ የመስቀል ክብረ በዓልን ማስመዝገቧም ይታወቃል፡፡ 
                                                                     ምንጭ፡- ሪፖርተር ጋዜጣ