Thursday, April 21, 2022

የመንዝ - ግሼ ወረዳ ስያሜና ታሪካዊ ዳራ !!!

የግሼ ወረዳ በአማራ ክልል ሰ/ሸዋ ዞን ይገኛል፡፡ ዛሬ በአዲስ ዓለም የምትገኘው ታቦተ ማርያም ለመጀመሪያ ጊዜ በአባ ሰላማ ካሴቴ ብርሃን እጅ ከአክሱም መዲና ወደ መንዝ መጥታ ጋን ሸን ከሚባል ተራራ ላይ የነበረው ምኩራበ ኦሪት በአባ ሰላማ ተባርኮ ንጉሡ አጽብሐ ባለበት ገብታለች። ለአካባቢው አማኞችም ምስዓል ወምስጋድ በመሆን ለብዙ ዘመናት ኖራለች፡፡ተራራው ቁብብ ያለና ላዩ ሜዳ ሆኖ የጋን ቅርጽ ያለው ሲሆን ጋን ሸን እንደተባለ ይነገራል፡፡ ይህንን ስያሜ ያገኘው ዙሪያውን ለታላላቅ ወንዞች ውሃ ስለሚያመነጭ ነበር ይባላል፡፡ ያ ቦታ ዛሬ ግሼ እየተባለ፤ምክንያቱም የግሼ ተራራ ጠላትን በርቀት ለመቆጣጠር ስለሚያስችል የጥንት ገዥዎች የድንኳን ከተማ እንደነበርም ይተረካል፡፡ በድርሳነ ኡራኤል "ወእመንቱ ነገሥት አኃው ዘሐነፁ በብሔረ ሸዋ ኀበ አሐቲ ሀገረ ዘይብልዋ ፍሉይ ወበዛቲ ገብሩ ዐቢየ ቤተክርስቲያን በስማ ለእግዝትነ ማርያም።" ትርጉም ፦ እነዚህ ወንድማማቾች ነገሥታት(አብርሃና አጽብሓ) በሸዋ ክፍለ አገር ፍሉይ በሚሏት ቦታ ላይ በእመቤታችን ስም ታላቅ ቤተክርስቲያን ሠሩ። ፍሉይ የተባለችውም ቦታ ምድረ ግሼ እንደሆነች ይታመናል፡፡


ዓፄ አምደ ጽዮን በዚህ አካባቢ የሀገሩን ሕዝብ ሰብስቦ ብዙ ክፍሎች ያሉትን የጥንት ዋሻ አስጠርጓል፡፡ ዋሻውንም ያስጠረገበት ዋናው ጉዳይ እንደ ዮዲት ጉዲት ያለ ሕዝባዊ ጠላት በአገር ላይ ሲነሳ በጦርነቱ ወቅት እንዳይጎዱ ለነዋዬ ቅድሳት መደበቂያ ፣ ለስንቅ ማሸሻ፣ ለሕፃናትና ለአቅመ ደካሞች ማሳረፊያ ለማድረግ ነው፡፡ በዋሻው ውስጥ ውሃ እንዳለ ይነገራል፡፡ ይህም ዋሻ በአካባቢው ሕዝብ አጤ ዋሻ የሚል ስም ስለተሰጠው እስከ አሁን እየተጠራበት ይገኛል፡፡

ምንጭ ፦ የአዲስ ዓለም ማርያም ቤ/ክ በ2000ዓ.ም ከተዘጋጀ መጽሔት ላይ የተወሰደ

No comments:

Post a Comment