Tuesday, December 22, 2020

ቆይታ ከዘፈን ግጥም እና ዜማ ደራሲ፤ ተውኔት ፀሀፊ እና አዘጋጅ ክቡር ዶክተር አርቲስት ተስፋዬ አበበ ጋር...

ሁለቱ ተስፋዬ አበበዎች ወግ...

 1960ዎቹ በአቋቋሙት የትያትር እድገት ክበብ /የተስፋዬ አበበ የኪነ ጥበባት ማዕከል/ እጅግ በርካት የጥበብ ሰዎችን አፍርተዋል፡፡ ለአብነትም -

- ሲራክ ታደሰ - አለሙ /አብ - ቴዎድሮስ ተስፋዬ

- ወጋየሁ ንጋቱ - ፋንቱ ማንዶዬ - ይገረም ደጀኔ

- ተክሌ ደስታ - ትሩፋት ገብረየስአለምፀሀይ ወዳጆ 

- አላዛር ተስፋዬ   - ትዕግስት ግርማ ጥቂቶቹ ናቸው፡፡


ባለፉት 60 ዓመታት የጥበብ ቆይታቸው 500 በላይ የዘፈን ግጥም እና ዜማዎችን ደርሰዋል፡፡ የእሳቸውን ድርሰቶች ከተጫወቱ ድምፃውያን መካከል ሂሩት በቀለ (ኢትዮጵያ፣ ህይወት አንደሸክላ፣ ቤቱ ቤቴ በላይ ጭራ አለ ጎጆዬ - 35 በላይ ስራዎች) ሙሉቀን መለሰ (እናቴ ስትወልደኝ፣ እምቧይ ሎሚ መስሎ እና ያልጅነት) አለማየሁ እሽቴ (ማን ይሆን ትልቅ ሰው፣ ማሪኝ ብዬሻለሁ የንጋት ኮኮብ መኖር ብቻ አይበቃም፣ አስቤሽ ነበር…) ዘሪቱ ጌታሁን ( እንቁጣጣሽ፣ ትዝታን በፖስታ ጊዜአለም …) ጥላሁን ገሰሰ (ያም ሲያማ ሰው ማን ይመስላል) መሀሙድ አህመድ (መቼ ነው) ታደለ በቀለ (አላስቀየምኳትም፣ ቅጠል ነጋዴዋ፣ የዘጠኝ ወር ቤቴ የኔ ቆንጆ ውብ አይናማ እና ገላዋ) ፖሊስ ኦርኬስትራ (መማር ያስከብራል) በሀይሉ እሸቴ(እግሬ በእጄ ሄደ..) ለአብነት ይጠቀሳሉ፡፡ ጋሽ ተስፋዬ ከግጥም እና ዜማ ድርሰት ባሻጋር ፒያኖ እና ክራር ይጫወታሉ፡፡ ድምፃዊት ሂሩት በቀለ እና መስፍን ሀይሌ ጋር የተጫወቱትንየፍቅር ቃጠሎየተሰኘ ዘፈን በክራር አጅበዋል፡፡


40 በላይ ትያትሮችን በመተወን፣ በማዘጋጀት እና በመድረስ አንቱታን አትርፈዋል፡፡

 በመተወን የተሳተፉባቸው ትያትሮች፡- ዳዊት እና ኦሪዮን ስነ ስቅለት ሀኒባል አፄ ቴዎድሮስ (የግርማቸው ተክለሃዋሪያት ድርሰት) ጥቂቶቹ ናቸው፡፡

በድርሰት እና በዝግጅት የተሳተፉባቸው፡- ህይወት ያለው በድን፣ ወሬ ፈላስፋ፣ ፀረ መናፍስት፣ 12 እብዶች በከተማ፣ የደም ቀለበት፣ ቀዩ ማጭድ፣ ታጋይ ሲፋለም፣ ያውሬው እርግቦች፣ ከጀግኖች ማህደር፣ የንጋት ኮኮብ የአውሬው እርግቦች፣ የትውልድ እምባ፣ አጋጣሚ፣ የኤርትራ አምባ፣ ጥቁር ድምፅ እና ባሻ ዳምጤ ጥቂቶቹ ናቸው፡፡

በቀዳሚዊ ኃይለስላሴ (የአሁኑ ብሄራዊ ትያትር) ቤት - 4 ዓመት ክብር ዘበኛ - የጀኔራል መንግስቱ ነዋይ የግል ጋዜጠኛ በመሆን 6 ወራት ወታደር እና ጊዜው የሚል ጋዜጣ ላይ ሰርተዋል፡፡ ከዚያም ፖሊስ ሰራዊት ሙዚቃ እና ትያትር ክፍል ገብተው የድርሰት እና ዝግጅት ክፍል ኃላፊ በመሆን በተለይ ሙዚቃ ክፍሉን በማጠናከር ተወዳጅ እና አንጋፋ ድምፃውያንን በማፍራት 35 ዓመታት በላይ ሰርተዋል፡፡ ይህ ሙዚቃ ክፍልም በኢትዮጵያ የመጀመሪያው የተባለ ሲንፈኒ እና ማርሽ ባንድ ነበረው፡፡


ሚያዚያ 12, 1932. እዚሁ መዲናችን አዲስ አበባ ልደታ አካባቢ የተወለዱት ጋሽ ተስፋዬ አበበ የከበርቴ/አርበኛ/ ልጅ ናቸው፡፡ እናታቸው የፈረንሳይ ተማሪ ሲሆኑ በገና ይጫወቱ ነበር፤ አባታቸው ደግሞ በማይጨው አርበኛ ሲሆኑ የከፍተኛ ፍርድ ቤት ዳኛም ነበሩ፡፡ አባታቸውም በገና እና ክራር ይጫወታሉ፡፡ ወንድሞቻቸውም በስዕል ጥበብ ውስጥ ያለፉ እና ያሉ ናቸው፡፡ በዚህ ቤተሰብ ውስጥ ያደጉት ጋሽ ተስፋዬም ወደ ኪነ ጥበቡ አድልተው ውጤታማ ሆነዋል፡፡ ይህ የትውልድ ቅብብሎሸ ቀጥሎም የእሳቸው ልጆች በጥበቡ ውስጥ ናቸው፡፡


በኪነ
ጥበቡ ላበረከቱት አስተዋፅኦም በርካታ የምስጋና እና እውቅና ሽልማቶችን አግኝተዋል፡፡ የበጎ ሰው ሽልማትን ጨምሮ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ (2006.) የክብር ዶክትሬት ተበርክቶላቸዋል፡፡ ከዘፈን ግጥም እና ዜማ ደራሲ፤ ተውኔት ፀሀፊ እና አዘጋጅ ክቡር ዶክተር አርቲስት ተስፋዬ አበበ ተዝቆ ከማያልቀው የህይወት ልምድና ተሞክሯቸው እንዲሁም ስራዎቻቸው ብዙ ቁም ነገሮችን መማር ይቻላል፡፡ ፅሁፌን እዚህ ላይ መቋጨት ግድ ይለኛልና ለጋሽ ተስፋዬ እድሜ ከጤና ጋር ተመኘሁ፡፡ ከብዙ በጥቂቱ ስለ እሳቸው የተወሰኑ መረጃዎችን ለማጋራት ሞክሬያለሁ በተረፈ እናንተ ጨምሩበት….!!!

No comments:

Post a Comment