Thursday, February 27, 2020

የአዲስ አበባ ልዩ መገለጫ ይሆናል የተባለው የመሶብ ታወር ግንባታ በቅርቡ ሊጀመር ነው፡፡

 የመሶብ ታወር ሥራ አስኪያጅ አቶ ፀጋዬ ተክሉ እንደተናገሩት ከዓመት በፊት በባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ይፋ የተደረገው የመሶብ ቅርጽ ያለው ታወር ግንባታው ከመጪዎቹ አራት ወራት በኋላ ይጀመራል። እንደ ሥራ አስኪያጁ ገለጻ ፕሮጀክቱ ሁለት ሕንፃዎችን የሚያካትት ነው። የመጀመሪያው በመሶብ ቅርፅ የሚሠራው ባለ 70 ወለል ሕንፃ ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ በሙዳይ ምስል ቅርፅ የሚሠራውና ባለ 20 ወለል ሕንፃ ነው።

 በኢትዮጵያውያን አርክቴክቶች ዲዛይኑ የተሰራው  ይህ ህንፃ  የመሶብ ቅርፅ የያዘበት ምክንያትን ከኢትዮጵያውያን ቤት የማይጠፋው መሶብ ተምሳሌትነቱ የመሰባሰብ፣ የአንድነት፣ የደስታና የጋራ ቃልኪዳን የሚታሰርበት በመሆኑ ነው ተብሏል፡፡ ህንፃው ሲገነባ የሆቴልና ቱሪዝም ስራ ማሰልጠኛ ተቋምን የልህቀት ማእከል ከማድረጉም በላይ የአገራችንን ገጽታ በመገንባት የቱሪስት መዳረሻ ሊሆን እንደሚችልም ዲዛይኑን የሰሩት ባለሞያዎች አስታቀዋል፡፡የኢትዮጵያውያንን አኗኗር ያሳያል የተባለው ህንፃ 250 ሜትር ከፍታ ያለው ባለ 70 ወለል ህንፃ ነው፡፡ ህንፃው በውስጡ የተለያዩ ደረጃቸውን የጠበቁ ባህላዊና ዘመናዊ ሆቴሎች፣ የገበያ ማዕከል፣ ሁሉንም ክልሎች የሚወክል የባህል ማእከል፣ የጎልፍ ሜዳ፣ የልዩ ልዩ ስፖርት ማዘውተሪያ፣ ቢሮወዎች እና የቱሪዝምና ሆቴል ዘርፍ የልህቀት ማእከል እንደሚኖረው ተገልጿል፡፡ ህንፃው እውን ሲሆን በርዝመቱ ከአፍሪካ የመጀመሪያው ይሆናል፡፡


ግንባታው በአዲስ አበባ በተለምዶ ሜክሲኮ በሚባለው አካባቢ በሚገኘውና ገነት ሆቴል ያለበት ሥፍራ ላይ የሚከናወን መሆኑን የገለፁት አቶ ፀጋዬ ከፕሮጀክቱ የግንባታ ወጪ 40 እስከ 49 በመቶ የሚሆነው የሚሸፈነው ከውጪ ሀገራት በሽርክና ሊሠሩ ከሚችሉ አካላት ሲሆን እስከ 51 በመቶ የሚደርሰው ወጪ ደግሞ በሀገር ውስጥ ባለሀብቶች ተሳትፎ የሚሸፈን መሆኑን አስታውቀዋል። እንደ ሥራ አስኪያጁ ማብራሪያም፤ ከውጪ ሀገራት በሽርክና ይገኛል የተባለው ገንዘብ ሙሉ በሙሉ የተገኘ ሲሆን፤ በቀጣይ ሳምንታት ከእነዚህ አካላት ጋር ቀሪ የፕሮጀክቱ ሁኔታዎች ላይ ስምምነት በመፈራረም ወደ ቀጣዩ የፕሮጀክቱ ስራ ይገባል ተብሎ ይጠበቃል።


  የፕሮጀክቱ አንዱ ክፍል የሆነውና ባለ 70 ወለሉ መሶብ መሰሉ ህንፃ የንግድ ስራ የሚከናወንበት ሁለገብ ህንጻ እንደሚሆን የጠቆሙት ሥራ አስኪያጁ፤ ባለ 20 ወለሉ ሌላኛው ሕንፃ ደግሞ በባለአምሥት ኮከብ ደረጃ ተገንብቶ ለሆቴልና ቱሪዝም ማሠልጠኛ ተቋምነት የልህቀት ማዕከልነት ለባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር የሚሰጥ ነው ብለዋል። የፕሮጀክቱ ጠቅላላ ወጪ እስከ 20 ቢሊየን ብር እንደሚደርስ፣ ግንባታውም 20 ሺህ ዜጎች የሥራ ዕድል እንደሚፈጥርና ከአራት ዓመት በኋላ ይጠናቀቃል ተብሎ እንደሚጠበቅም ሥራ አስኪያጁ አስታውቀዋል።
                                 ምንጭ ፡- ኢ.ፕ.ድ እና ኢ.ቢ.ሲ

Wednesday, February 26, 2020

የአዲስ አበባ ምክትል ከንቲባ ከቋሚ ሲኖዶስ ጋር ተወያዩ፡፡


የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ ኢንጂነር ታከለ ኡማ ትናንት የካቲት 17 ቀን 2012 . በቦሌ ክፍለ ከተማ በተለምዶ 24 በሚባለው አካባቢ ተፈጥሮ የነበረውን ችግር በተመለከተ ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቋሚ ሲኖዶስ ጋር ተወያይተው ችግሩ ከሦስት አካላት በተውጣጣ ኮሚቴ እንዲጣራ ተስማምተዋል።


ከሦስት አካላት ማለትም ከቤተ ክርስቲያን፣ ከአካባቢው ሽማግሌች እና ከመንግሥት አካል የተቋቋመው ኮሚቴ በዐሥር ቀናት ውስጥ ችግር የፈጠሩትን አካላት ማንነት፣ በቦታው የነበረውን ንዋያተ ቅድሳት ሁኔታ እንዲሁም ስለቦታው በዝርዝር አጥንቶ እንዲያቀርብ ስምምነት ላይ ደርሰዋል። በተፈጠረው ችግር ምክንያት ታስረው የነበሩ ክርስቲያኖች ክሳቸው ተቋርጦ በዛሬው ዕለት እንደሚፈቱም ከንቲባው ለቋሚ ሲኖዶስ አባላት ተናግረዋል።
                                                ምንጭ ፡- ማህበረቅዱሳን

የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ወልዋሎ ዓዲግራት ዩኒቨርሲቲን ከውድድር አገደ


የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የወልዋሎ ዓዲግራት ዩኒቨርሲቲን ከማንኛውም ውድድር ማገዱን አስታወቀ። ፌዴሬሽኑ ለወልዋሎ ዓዲግራት ዩኒቨርሲቲ በጻፈው ደብዳቤ፥ ባለፈው ዓመት ክለቡን ካገለገሉት ስምንት ተጫዋቾች ጋር በተያያዘ ጥር 14 ቀን 2012 . በፍትህ አካላት 10 ቀናት ውስጥ ውሳኔውን እንዲተገብሩ የጊዜ ገደብ ተሰጥቷቸው እንደነበር አስታውቋል።


  ይሁን እንጅ ወልዋሎዎች በሚመለከተው የፍትህ አካል የተላለፈውን ውሳኔ በተሰጣቸው ጊዜ መሰረት አለመፈጸማቸውን ገልጿል። ይህን ተከትሎም የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ክለቡ ፌዴሬሽኑ ከሚሰጣቸው ማናቸውም አገልግሎቶች መታገዱን ነው ያስታወቀው።
                                                                          ምንጭ፦ ሶከር ኢትዮጵያ