Saturday, November 28, 2015

ከሜጋ ትያትር እስከ ኮራ እና አፍሪማ ተሸላሚነት …….. አርቲስት ፀደንያ ገብረማርቆስ


   “ገዴ” እና “ቢሰጠኝ” የተሰኙ ሁለት አልበሞች አሏት፡፡ እ.ኤ.አ በ2004 “እወድሃለሁ” በሚለው ስራዋ የኮራ ሙዚክ አዋርድ ተሸላሚ ናት፡፡ በቅርቡ ደግሞ በናይጄሪያ ሎጎስ በተካሄደው ኦል አፍሪካ ሙዚክ አዋርድስ /አፍሪማ/ በምስራቅ አፍሪካ ምርጥ የሴት ድምፃውያን ምድብ አሸናፊ ሆናለች፡፡ ለተለያዩ ፊልም እና ድራማዎች ሳውንድ ትራክ /ማጀቢያ ሙዚቃ/ ሰርታለች፡፡ ቀደም ሲል በኤፍ ኤም አዲስ 97.1 በሚቀርበው የ “አይሬ” ፕሮግራም ትሰራ የነበረ ሲሆን አሁን ደግሞ በሸገር ኤፍ ኤም 102.1 “ዜማ ፍቅር” የተሰኘ ፕሮግራምን ታቀርባለች፡፡ ሶስተኛ አልበሟንም ሰርታ አጠናቃለች፤ አርቲስት ፀደንያ ገብረማርቆስ፡፡
   አርቲስት ፀደንያ በሀገር ውስጥ እና በውጭ ልዩ ልዩ ሽልማቶችን አግኝታለች፡፡ በኮራ እና በአፍሪማ አራት ጊዜ ተወዳድራ ፣ ሶስት ጊዜ ለእጩነት ቀርባ በሁለቱ አሸንፋለች፡፡ እ.ኤ.አ በ2004 ከኬንያዊቷ አቺንግ አቦራ ጋር “እወድሃለሁ” በተሰኘው ስራዋ በምስራቅ አፍሪካ ምርጥ የሴት ድምፃዊት ተብላ የሽልማቱ ተጋሪ ሆናለች፡፡ ዘንድሮ ደግሞ በ2015 ለሀርየት ፊልም ማጀቢያ በሰራችው “የት ብዬ” ዘፈን  በ24 ካራት ወርቅ የተለበጠ የአፍሪማን የዋንጫ ሽልማት አግኝታለች፡፡ በሸገር ኤፍ ኤም 102.1 የለዛ ፕሮግራም የአመቱ የአድማጮች ምርጥ የፊልም ማጀቢያ በሚል “የት ብዬ” በተሰኘው ዘፈን አሸናፊ ሆናለች፡፡


  በቀድሞው ደብረ ያሬድ (ሜጋ ትያትርም) ለተወሰኑ አመታት ሰርታለች፡፡ በእንግሊዘኛ ዘፈኖች ሙዚቃን አሀዱ ያለችው አርቲስት ፀደንያ ገብረማርቆስ ቀስ በቀስ ወደ አማርኛ ስራዎች በማምራት ሁለት ያህል አልበሞችን እና በርከት ያሉ ነጠላ ዜማዎችን ለአድናቂዎቿ አድርሳለች፡፡ “ገዴ” የተሰኘው የመጀመሪያ አልበሟ በኬንያዊው አቀናባሪ ዴቪድ ኦቴኖ የተሰራ ሲሆን አምባሰል ሙዚቃ ቤት ነው የታተመው፡፡ “ቢሰጠኝ” የተሰኘው አልበሟ ደግሞ ጥበቡ ወርቅዬ ኢንተርቴይመንት የታተመ ሲሆን ቅንብሩን ዳግማዊ አሊ ሰርቶታል፡፡


   አሁን ደግሞ ሶስተኛ አልበሟን አጠናቃ ለአድናቂዎቿ ለማድረስ ጉድ ጉድ እያለች ትገኛለች፡፡ የዚህ አልበም በዛ ያሉት ግጥሞች የይልማ ገብረአብ ሲሆኑ ጌትነት እንየው፣ አብዲራዋ (የህመሜ ደራሲ) እና ፋሲል ከበደ ተሳትፈዋል፡፡ አብዛኛዎቹን ዜማዎች እሷ እራሷ ናት የሰራቻቸው፡፡ ቅንብሩን ደግሞ አቤል ጳውሎስ፡፡ ሙዚቃ ስትጀምር አማርኛ እንዳትዘፍን የተባለችው ይህቺ ድምፃዊት የሀገሯን ሙዚቃ በአለም መድረክ እያስተዋወቀች ትገኛለች፡፡ በዚህም በርካታ ሽልማቶችን ተጎናፅፋለች፡፡


  እ.ኤ.አ በ2003 ከግርማ ይፍራሸዋ ጋር የተለያዩ የአፍሪካ ሀገራትን በመዘዋወር ስራዎቿን አቅርባለች፡፡ በ2009ም በወርልድ ሙዚክ ከእነ ፈለቀ ሀይሉ (ሳክስፎን) ፣ ሳሙኤል ይርጋ (ፒያኒስት) ፣ ተራማጅ ወረታው (ማሲንቆ) እንዲሁም ስንታየሁ ዘነበ እና እሷ ሆነው ሁለት አልበሞችን ሰርተው በአለም አቀፍ ፌስቲቫሎች ላይ ተሳትፈዋል፡፡
   

  ከኤዘር ኦርኬስትራ ጋርም አልያንስ - ኢትዮ ፍራንሲስ ከውጪ በመጡ የሙዚቃ ባለሙያዎች ታጅባ “ባቲ” የተሰኘ ስራዋን አቅርባለች፡፡ ከዚያም በኋላ ከጋሽ መሀሙድ አህመድ ጋር በፈረንሳይ ሀገር ዝግጅቶቿን አሳይታለች፡፡ ድምፃዊት ፀደንያ ገብረማርቆስ ከድምፃዊነት፣ ዜማ ደራሲነት እና ፕሮግራም አቅራቢነት ባሻገር ቀደም ብላ ማስታወቂያዎችንም ትሰራ ነበር፡፡ ለአብነትም አብወለድ ፣ ገርልጊ ፣ ካዲስኮ እና ሌሎችንም መጥቀስ ይቻላል፡፡

  ትውልዷ እና እድገቷ እዚሁ መዲናችን አዲስ አበባ የሆነው ፀደንያ የመንታ ወንድ ልጆች እናት ናት ፡፡ ቀሪ ዘመኗም የስኬት እና ብልፅግና እንዲሆን በመመኘት እኔ ፅሁፌን በዚሁ ላብቃ ሌላውን እናንተ ጨምሩበት ……

No comments:

Post a Comment