Monday, June 22, 2015

እነሆ ስጦታ……… ከሸዋንዳኝ ሀይሉ !!!



      በእነ ለንደን ቢት ቦብ ማርሌ እና አርኬሊ ሙዚቃን አሀዱ ያለው አርቲስት ሸዋንዳኝ የአማርኛ ሙዚቃ ዳዴው የእነ ግርማ በየነ ጌታቸው ካሳ እና ዳዊት መለሰ ስራዎች ነበሩ፡፡ ከዚያም በሳቂልኝ እና ስጦታሽ አልበሞቹ ከወዳጅ እና አድናቂዎቹ ጋር ተገኛኝቷል፡፡ .. 2004 በኮራ የሙዚቃ ሽልማት በወንዶች ከምስራቅ አፍሪካ ኢትዮጵያን ወክሎ 3ኝነት ደረጃን አግኝቷል፡፡

   ሙዚቃን ገና የ10ኛ ክፍል ተማሪ ሆኖ በሴንት ጆሴፍ ት/ቤት ነበር የጀመረው፡፡ በዚህ ት/ቤትም የተለያዩ የእንግሊዘኛ ዘፈኖችን በመጫወት ለሁለት አመታት ያህል ሰርቷል፡፡ ከትምህርቱ ጎን ለጎን ሙዚቃን ይጫወት የነበረው ሸዋንዳኝ ሀይሉ ከአባቱ ጠንካራ ተቃውሞ ገጥሞት እስከ መኳረፍ ደርሶ ነበር፡፡ በዚህም ከቴዲ አፍሮ ጋር ቤት ተከራይተው ለሶስት አመት ያህል አብረው ኖረዋል፡፡ ለዚህም ይመስላል ሸዋንዳኝ “ስቅ አለኝ” እና “ስጦታሽ” የተሰኙትን አልበሞቹን ሲያወጣ ቴዲ አፍሮ በርከት ያሉ ግጥም እና ዜማዎችን ሰጥቶታል፡፡
  

  “ስቅ አለኝ” አልበሙ ከአባቱ ጋር ያስታረቀው ሲሆን እሳቸውም ደውለው አበረታተውታል፡፡ ከዚህ አልበም በኋላም ግብፅ ፣ ደቡብ አፍሪካ ፣ ዱባይ ፣ አቡዳቢ ፣ ባህሬን ፣ እስራኤል ፣ አውሮፓ እና አሜሪካ ኮንሰርቶችን አቅርቧል፡፡ ቡፌ ድላጋር ፣ የቀድሞው ላየን ክለብ ፣ ኮፊ ሀውስ ፣ ሂልተን ፣ ሽራተን ፣ ኢሉዥን እና ሚሞ ክለቦች ሰርቷል፡፡ በኋላ ላይም እሱ እና ቴዲ አፍሮ ላየን ክለብ ይዘው በጋራ ይሰሩበት ነበር፡፡ በተጨማሪም በ1999ዓ.ም “ፋራናይት” የተሰኘ ክለብ ከጓደኞቹ ጋር ከፍቶ ነበር፡፡ በዚህም እዮብ መኮንን ፣ ፀደኒያ ገ/ማርቆስ ፣ ጆኒ ራጋ እና ሌሎችም ስራቸውን ያቀርቡበት ነበር ምንም እንኳን አሁን አገልግሎት ላይ ባይሆንም፡፡
  

  በሀገራችን ታዋቂ ከሆኑት አይቤክስ ፣ ኢትዮ ስታር ፣ ኤክስፕረስ ፣ መዲና ፣ አዲሰ ፣ ሌቫንስ እና አፍሮ ሳውንድ ባንዶች ጋርም ሰርቷል፡፡ “አፍሮ ሳውንድ” ቴዲ አፍሮ ፣ ግሩም መዝሙር እና ሸዋንዳኝ ሀይሉ በጋራ የመሰረቱት ባንድ ነው፡፡ ስያሜውን ያወጣው ሸዋንዳኝ ሀይሉ ሲሆን ባንዱ ለ10 ዓመት ያህል በጥሩ ሁኔታ ሲሰራ ቆይቷል፡፡ በጊዜውም እነ ኤልያስ መልካ ፣ ዳግማዊ አሊ ፣ ዳንኤል ክንደያ ፣ አሸናፊ አሊ እና ሁንአንተን የመሳሰሉ ታዋቂ የሙዚቃ ሰዎችን አፍርቷል፡፡ 


  አርቲስት ሸዋንዳኝ ሀይሉ “ስቅ አለኝ” የተሰኘ አልበሙን ከሰራ ከ8 ዓመት በኋላ “ስጦታሽ” የተሰኘ ሁለተኛ አልበሙን ለአድናቂዎቹ  ጀባ ብሏል፡፡ በነገራችን ላይ ይህ ስራ ገና ሳይጀመር ቅድመ ክፍያ (ቀብድ) የኤሌክትራ ባለቤት አቶ ተሾመ በራሳቸው ፍላጎት ሰጥተውት የተሰራ አልበም ነው፡፡ አልበሙም 6 ዓመታትን ወስዷል፡፡


   እዚሁ አዲስ አበባ መስቀል ፍላወር የተወለደው አርቲስት ሸዋንዳኝ ሀይሉ የአንደኛ ደረጃ ትምህርቱን ምስክያዞና ፣ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን ሴንት ጆሴፍ እንዲሁም አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ተከታትሏል፡፡ በዩኒቨርስቲ ቆይታ የመጀመሪያ አመት ኬሚስትሪን ቢመርጥም ከአንድ አመት በኋላ ወደ ማኔጅመት በመቀየር ለሶስት አመት ተምሮ ሳይጨርስ “ዊዝድሮዋል” አድርጓል፡፡ አሁን ሙሉ ጊዜውን ለሙዚቃ ሰጥቶ እየሰራ ይገኛል፡፡ ከሙዚቃው ውጪም ፊልም እና ግራውንድ ቴንስ ይወዳል፡፡ እግር ኳስ ከሀገር ውስጥ የቅድስ ጊዮርጊስ ፤ ከውጪ ደግሞ የብራዚል ብሄራዊ ቡድን ደጋፊ ነው፡፡ እኔ ይህን አልኩ እናንተ ደግሞ ቀሪውን ጨምሩበት…….

Monday, June 15, 2015

ወይ ሰኞ ገበያ………. !!!


   የኦሮሞ ብሄረሰብ ዞን በአማራ ክልላዊ ምንግስት ከተቋቋሙት ልዩ የብሄረሰብ ዞኖች አንዱ ነው፡፡ ዞኑ በ1986ዓ.ም አጋማሽ የተቋቋመ ሲሆን በውስጡም ሁለት የከተማ መስተዳድሮች እና አምስት የገጠር ወረዳዎችን አቅፏል፡፡ የዞኑ ዋና ከተማ ከሚሴም ከአዲስ አበባ በደሴ መስመር በ325 ኪ፣ሜ ከባህር ዳር ደግሞ በወልዲያ መስመር 555 ኪ.ሜርቀት ላይ ትገኛለች፡፡ አብዛኛው ህዝብ ኦሮሞ ሲሆን የአማራ ፣ የአርጎባ እና የአፋር ብሄረሰቦችም በዞኑ ውስጥ ይኖራሉ፡፡ የዞኑ የስራ ቋንቋም ኦሮምኛ ነው፡፡

 
  በኦሮሞ ዞን ውስጥ በተለያዩ ቦታዎች ገበያዎች ቢኖሩም የውጭ ሀገር ቱሪስቶችን ቀልብ በመሳብ ረገድ ከፍተኛውን ድርሻ የያዙት የባቲ እና የሰንበቴ ገበያዎች ናቸው፡፡ከኮምቦልቻ ጅቡቲ በሚወስደው መንገድ 41 ኪ.ሜ ርቀት ላይ የባቲ ከተማን እናገኛለን፡፡ ባቲ በተለያዩ የዘፈን ቅኝቶች ብዙ የተባለላት ታሪካዊ እና ዕድሜ ጠገብ ከተማ ነች፡፡ በተለይ ባቲ ከምትታወቅባቸው መካከል አንዱ ገበያዋ ሲሆን ከመርካቶ ቀጥሎ የሚገኝ ትልቅ ገበያም እንደሆነ ይነገርላታል፡፡


   ዘወትር ሰኞ ሰኞ የሚውለው የባቲ ገበያ የአርጎባ ፣ የአማራ ፣ የኦሮሞ እና የአፋር ብሄረሰቦችን ያገናኛል፡፡ ብሄረሰቦቹ ከእነ አለባበሳቸው እና አጋጌጣቸው በስፋት በገበያው ላይ መገኘታቸው ለጎብኚዎች ትልቅ እርካታን ይፈጥራል፡፡ በአፄ ኃይለስላሴ ዘመነ መንግስት የተሰራው የሰው መስቀያ ብረትም በገበያው መሀል ቆሞ ይገኛል፡፡ ይሄም የዘመኑን ታሪካዊ ገፅታ የሚያሳይ ቅርስ ነው፡፡


   ዘወትር እሁድ እሁድ የሚውለው የሰንበቴ ገበያም የተለያዩ ብሄር ብሄረሰቦችን ያገናኛል፡፡ ይህም የባህል ትስስር እና ልውውጥን ከመፍጠሩም ባሻገር የጎብኚዎችን ቀልብ ይስባል፡፡

Friday, June 12, 2015

ገንዘቤ ዲባባ በኦስሎ ዳይመንድ ሊግ አሸነፈች


  በኦስሎ በተካሄደ የ5ሺህ ሜትር ውድድር ገንዘቤ ዲባባ የእህቷን ክብረወሰን ባታሻሽልም አሸናፊ መሆን ችላለች። ገንዘቤ በውድድሩ ላይ ጥሩነሽ ዲባባ ከያዘችው የክብረወሰን ሰዓት በ10 ሰከንድ ዘግይታ በመግባቷ ነው ክብረወሰኑን ማሻሻል ያልቻለቸው። ጥሩነሽ ዲባባ ይህን የ5 ሺህ ሜትር ርቀት በጎርጎሮሳውያኑ 2008 ላይ 14:11.15 በሆነ ሰአት በመግባት የክብረ ወሰኑ ባለቤት ነች።


    ገንዘቤ ርቀቱን 14:21.29 በሆነ ሰዓት የሀግሯን ልጅ ሰንበሬ ተፈሪ እና ኬኒያዊቷን ቪዮላ ጂላጋት ኪቢዎትን በማስከትል አጠናቃለች። ገንዘቤ ከውድድሩ በኃላ ክብረ ወሰን ለማሻሻል አስባ ብትሮጥም አሯሯጮች በምትፈለግው ፍጥነት ስላልሄዱላት ክብረ ወሰኑን የማሻሻሽ እቅዷ እንዳልተሳካ ተናግራለች።