Friday, March 24, 2017

አማርኛ ይሰማሉ ፣ ይናገራሉ ነገር ግን አያነቡም ፣ አይፅፉም…… ሀብተስላሴ ታፈሰ !!!


  ትውልዳቸው ኢትዮጵያ ቢሆንም ገና ከልጅነታቸው ጀምሮ በራሽያ እና በግሪክ እንዲሁም በሌሎች ሀገራት ነው አብዛኛውን ህይወታቸውን ያሳለፉት፡፡ ከአምስት በላይ ቋንቋዎችን የሚችሉ ሲሆን ራሽያኛ ፣ ግሪክኛ ፣ ጣሊያንኛ ፣ እንግሊዘኛ ፣ ስፓኒሽ እና አማርኛ ይጠቀሳሉ፡፡ ቋንቋን ስናነሳ ገራሚ ታሪካቸው የአማሪኛው ነገር ነው፡፡ አማርኛ ይሰማሉ ፣ ይናገራሉ ነገር ግን አያነቡም ፣ አይፅፉም፡፡
   

  ሌላው ገራሚ ነገራቸው ደግሞ የኢትዮጵያን የባህል ምግብ እና መጠጥ አለመጠቀማቸው ነው፡፡ በውጪ ሀገር ብዙ ጊዜ መቆየታቸው ተፅዕኖ ቢያደርግባቸውም ሌላም ምክንያት እናዳላቸው ይገልፃሉ፡፡ ይኸውም ከውጪ ወደ ትውልድ ሀገራቸው ሲመለሱ እናታቸው የፍቅራቸውን እና የእናትነታቸውን ልጃቸውን ሊያጎርሱ ይዘጋጃሉ፤ልጅ ለነገሩ እንግዳ ናቸው እና አሻፈረኝ ሲሉ እናት ቅስማቸው ይሰበራል፡፡ በዚህም እናቴ ረገመችኝ ከዚያ በኋላ ከአትክልት እና ፍራፍሬ ውጪ የባህል ምግቦች እና መጠጦችን እስካሁን ተጠቅሜ አላውቅም ሲሉም አጫውተውኛል፡፡ እኚህ ሰው የቱሪዝም አባት እየተባሉ የሚጠሩት ጋሽ ሀብተስላሴ ታፈሰ ናቸው፡፡
  
  ጋሽ ሀብተስላሴ የኢትዮጵያን ቱሪዝም ላሳደግ ብዙ መስዕዋትነት ከፍለዋል፡፡ የኢትዮጵያ ቱሪዝም ድርጅት እንዲመሰረትም የበኩላቸውን ጥረት አድርገዋል፡፡ እሳቸው በጀመሩት ከቀረጥ ነፃ(ዲዩቲ ፍሪ) ግብይት ኢትዮጵያ በአፍሪካ እና በአለም ስሟ እንዲጠራ አስችለዋል፡፡ ባለፉት ረጅም አመታት ኢትዮጵያ በአለም ላይ ትተዋወቅበት የነበረው “የ13 ወር ፀጋ” መርህ አመንጪም ናቸው፡፡


  የቀድሞው ልዑል መኮንን መታሰቢያ ሆስፒታል(የአሁኑ ጥቁር አንበሳ) እና ሽራተን ሆቴል መዲናችን አዲስ አበባ እንዲቋቋሙ በማድረጉ በኩል ትልቅ ሚና ነበራቸው፡፡ ከዚህም ባሻገር የኢትዮጵያ የህዝብ ለህዝብ ኪነት ቡድን ወደ አውሮፓ እና አሜሪካ በመሄድ የኢትዮጵያን ባህል እና ቅርሶች እንዲያስተዋውቁ ከፍተኛ ጥረት አድርገዋል፡፡ ለዚህም በካናዳ በ1960ዓ.ም የተካሄደውን “ኤክስፖ 67” መጥቀስ ይቻላል፡፡
  

     ጥሩ ፎቶግራፍ አንሽ የሆኑት ሀብተስላሴ ከመደበኛ ስራቸው በጡረታ ከተገለሉ በኋላም በግላቸው አሁንም በቱሪዝሙ ዘርፍ እየሰሩ ይገኛል፡፡ ሀገሪቱ በቱሪዝሙ ዘርፍ ማግኘት ያለባትን ባለማግኘቷ እና እሳቸውም የሚያስቡት ያህል ባለማድረጋቸው ይቆጫሉ፡፡ የ91 ዓመት የእድሜ ባለፀጋም ሆነው አሁንም ስለ ኢትዮጵያ ቱሪዝም ማበብ ያስባሉ ፣ ይጨነቃሉ፡፡ በርካታ ፕሮጀክቶችን በመቅረፅ እና በማማከርም ይሰራሉ፡፡ ከያዟቸው ፕሮጀክቶች ኢትዮጵያ የሰው ዘር መገኛ እንደመሆኗ የሉሲን ፎቶ በአንድ ብር ወይም በአምስት ብር ኖት ላይ አሳትሞ በማሰራጨት በመላው አለም ማስተዋወቅ የሚለው ይገኝበታል፡፡   


    ኢትዮጵያ ለረጅም አመታት ትተዋወቅበት የነበረው “የ13 ወር ፀጋ” መርህ ምድረ ቀደምት በሚለው ተቀይሯል፡፡ ሰሞኑን ደግሞ “የ13 ወር ፀጋ” መርህ አመንጪ እና የቱሪዝም አባት ተብለው የሚጠሩት ሀብተስላሴ ታፈሰ ብሄራዊ እውቅና ተስጥቷቸዋል፣ የወርቅ ኒሻን እና የገንዘብ ሽልማት ተበርክቶላቸዋል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ በሀገር ውስጥ እና በውጪ በርካታ ሽልማቶችን አግኝተዋል፡፡  ክብር ለሀገር ባለውለታዎቻችን !!!

Tuesday, March 21, 2017

ከዚህ እስከ እዚያ (Africa Vacation – Langano).....



ምስጋና ለአፍሪካ ቫኬሽን ክለብ 

ከዚህ ቀጥዬ ስለ እኛ እናገራለሁ፡፡ እኛ ማነን? ……ተከተሉኝማ…!

  ዕለተ ቅዳሜ መጋቢት ዘጠኝ 2009 . እኔና ባልደረቦቼ ለጉዞ ተነስተናል፡፡ ጉዞ ወደ አፍሪካ ቫኬሽን - ላንጋኖ፡፡ ይህ ጉዟችን የተለመደው ዓይነት - የሥራ ጉዞ አይደለም፡፡ ይልቁንም በህግና ደምብ በአለቃና ምንዝር የታጠረ አብርሆትን (formal communication) ሰብረን ሰብአዊ ቤተሰብን የምንፈጥርበት እንጂ፡፡ ማህበራዊ ቁርኝታችንን ወደ ላቀ ከፍታ 
የምናሳድግበት እንደ ሰራተኛና አለቃ ብቻ ሳይሆን እንደ እህት እንደ ወንድም፣ እንደ ታናሽ እንደ ታላቅ እኔ ላንተ አንተ ለኔ የምንባባልበት ልዩ የፍቅር ጉዞ ነው፡፡ ዓመት ሙሉ በሥራ የተወጠረ አዕምሮ ዘና የሚልበት ወይም ራሳችንን (Refresh)የምናረግበት ነው - ዓመታዊው የጉዞና የመዘናኛ ዝግጅታችን፡፡


   እናማ በዚህ መሰረት ነው የዘንድሮው ጉዟችን ፡፡ ለዚህ ጉዞ 20 የምንበልጥ ጋዜጠኞች በማለዳው ተገኝተናል፡፡ ጉዞ የሚጠይቀውን ጓዝም ሸክፈናል፡፡ የአንዳንዱ ሻንጣ አያይዝ ግን ላንጋኖ ሊዝናና ነው ብሎ ከማሰብ ይልቅ ላንጋኖ ቤት ሊቀይር ነው ብሎ ማሰብ የሚቀል ይመስለኛል፡፡ (ያዝ እንግዲህ)፡፡

አሁን ደግሞ ጥቂት ስለ መኪና ውስጥ አቀማመጣችንከፊል እውነትየተቀላቀለበት መረጃ እሰጣለሁ፡፡
ፊት ወንበር - - - -ከፍተኛ አመራር
መሀል ወንበር - - -መካከለኛ አመራር
ኋላ ወንበር - - - ሪፖርተር
ከመጨረሻ መጨረሻ - - - ተሰናባች ጋዜጠኛ


  እንግዲህ በስልጣን ተዋረዴ መሰረት ከኋላ ወንበሬ ላይ ተሰይሜያለሁ፡፡ ልብ በል በተሰናባቹ ጋዜጠኛ ቦታ አላልኩም፡፡ ሪፖርተር በሚለው ቦታ ማለቴ ነው፡፡ (በነገራችን ላይ ተሰናባቹ ጋዜጠኛ ያለኩት አንድ በቅርቡ ከኛ የለቀቀ - በፍቅር ብዛት ከኛ ጋር እንዲጓዝ ተጋብዞ የመጣ አንድ ጋዜጠኛ ስላለ ነው፡፡)

ከጋዜጠኛ ጋር ስትጓዝ ሁለት ነገሮች የተከለከሉ መሆናቸውን ባታምንም ታምናለህ፡፡ አቀርቅሮ ማሰብና ማንቀላፋት፡፡ በምትኩ - ከየማዕዘኑ በሚወረወሩ የቀልድ ጠጠሮች አናትህ እየተወቀረ ፈንዲሻ መስለህ መጓዝን አምነህ ትቀበላለህ፡፡ የሳቅ ነገር ከተነሳ የገረሙኝን ሁለት ነገሮች ልናገር፡፡

አንድ - ያንዳንዱ ሳቅ ከሰማይ መብረቅ የሚያወርድ ይመስል የሆነ ግግግገግግ የሚል ማስገምገም ያለው መሆኑ (ያዝ - እዚህ ውስጥ የምትካተት ራስህን ቁጠር)

ሁለት - አንዳንዱ ደሞ ሳቁ በአዋጅ የተከለከለ ይመስል ከንፈሩን ገጥሞ ሆዱን እንደ ፎጣ የሚጨምቅ ነው፡፡ (እዝችጋ እኔን አንድ በል)
   


  ከመኪናችን የኋላ ጥግ (corner) ተቀምጫለሁ፡፡ አቀማመጤ ለሌሎችና ለካሜራ እንዳልታይ ቢያረገኝም ሁሉንም አጮልቄ እንድሾፍ ግን ጠቅሞኛል፡፡ የሰርግ አስፈፃሚ ከመሰለው እስከ ባለሻንጣው - - - ለቀልዶች ሁሉ ሀሀሀሀ የሚል ሳቅ ከሚያዋጣው እስከ ሳትናገር ሄዳ ሳትናገር እስከተመለሰችው፡፡ ሁሉንም አያለሁ፡፡ (እነዚህ እነማናቸው እንደማትሉኝ ተስፋ አለኝ)፡፡

ጉዟችን ሞቅ ያለ ነበር፡፡ የሙቀቱ ምክንያት ግን ፀሐይዋ ብቻ አትመስለኝም፡፡ እንደኔ እንደኔ የስንታሁ እጅም ነበረበት፡፡ ምክንያቱም ያን ሁሉ የሳቅ ናዳ እያንከባለለ ባይጭንብን በሳቅ ሙቀት ተንጣጥተን መች ፈንዲሻ እንሆን ነበር፡፡ እንደውም አንዳዶች ለብዙ ሀይላንድ ውሃ መጠጣት አደጋ አጋልጦናል ብለዋል አሉ፡፡ ( ያዝ - ስንትሽ ቺርስ )

አሁን ደግሞ ከሳቅ ምንጮች ጥቂቶቹን እጠቅሳለሁ - - -ግን እኛ ብቻ እንዲገባን አድርጌ ነው ( ምን ታረጉታላችሁ)
ወርደን እንነጋገር - - - - - - (ስንቴ)
ጨምላቃ - - - - - - - - - (ስንቴ Vs ታዴ)
እምቡጥ - - - - - - - - -- -(ታዴ)
Yahoo.com - - - - - - - - - (አቤል)
ከፀሐይ ላይ ተነስ - - - - - - - (ሚሊ)
ፐብሊክ ባስ እየመጣ ነው - - - -(ጀሙ)
ሌሎችም - - - -



አፍሪካ ቫኬሽን - ላንጋኖ ስንደርስ ጊዜው ወደ መምሸቱ ነበር፡፡ ቢሆንም ግቢውን ዞረን ለማድነቅ ኳስ ለመጫወት የላንጋኖን ሐይቅ በምትጠልቀዋ ጀምበር ለማየት የሚያስችል ሰዓት አላጣንም፡፡
ከምሽቱ ዝግጅታችን እስከ እሁድ ረፋድ የነበረን ቆይታ በርግጥም አስደሳች ነበር ብል አልተጋነነም፡፡ የጀልባው ሽር ሽር ፈረስ መቀመጡ ዋናው - - - - በሥራ የታጨቀ መንፈሳችንን ማደስ ብቻ ሳይሆን - - - የማንረሳው ትዝታም የጣለብን ይመስለኛል፡፡



ከሳቅ ከጨዋታው ደምቆ የሚነበብ - መተሳሰብን ይበልጥ መቀራረብን እንደዋዛ የተነገሩ ነገር ግን የህይወት ስንቅ የሆኑ ልምዶችን ተለዋውጠናል፡፡ በኔ ዐይን ይህ ጉዞ ገንዘብ የማይገዛውን ውድ የመንፈስ ሀብት የሸመትንበት ነው እላለሁ፡፡ እናንተስ - - - -???