Wednesday, July 27, 2016

ብዙዎች ቶሚ ብለው ያንቆለጳጵሱታል …. ድምፃዊ ፣ግጥም እና ዜማ ደራሲ ቶማስ አበበ፡፡

  በሙዚቃው አለም ከ3ዐ አመት በላይ አሣልፏል፡፡ በአንድ ወቅት ለአንድ ሠው ደብዳቤ ለማድረስ ሀረር ይሄዳል፡፡ በዚህ አጋጣሚ በሀረር ፖሊስ ምስራቅ ሰጎን ኦርኬስትራ ዳንስና ሙዚቃ ተፈትኖ ገና በ13 አመቱ አካባቢ የኪነ ጥበቡን አለም ተቀላቀለ፡፡ በሀረር ፖሊስ ለ3 ዓመታት ያህል ከሠራ በኋላም አዲስ አበባ ተመልሶ የቀድሞው ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ /የአሁኑ ብሄራዊ ትያትር/ ቤት ሰው ሊጠይቅ ይሄዳል ፡፡ እዚያም በዚሁ አጋጣሚ በትያትር ቤቱ “ዳዊት ባንድ” ውስጥ ተቀጥሮ ለትንሽ ጊዜ አገልግሏል፡፡ በዚህ ያላቆመው ይህ ሰው ፖሊስ ፣ ምድር ጦር እና ሀገር ፍቅር ኦርኬስትራዎች ውስጥም በተለያዩ ጊዜያት ገብቶ ሠርቷል፡፡ ድምፃዊ ፣ግጥም እና ዜማ ደራሲ ቶማስ አበበ፡፡

  በተፈጥሮው የዘፋኝነት ተሰጥኦ ያለው ቶማስ አበበ በልጅነቱ የጥላሁን ገሰሰ፣ በተለይም የመስፍን ሀይሌ እና ሌሎች ድምፃውያን ስራዎችን ይጫወት ነበር፡፡ ረዘም ያለውን ጊዜ በምድር ጦር ያሳለፈው ቶማስ አበበ ለራሱ ከደረሣቸው ግጥምና ዜማዎች ባሻገር ለአባይ በለጠ "ሙናዬ" እና ለታምራት ሞላ "ሙዚቃ " የተሰኙትን ድርሰቶች አዘጋጅቷል፡፡ በምድር ጦር እስከ1969ዓ.ም ድረስ በድምፃዊነት እና በግጥም እና ዜማ ደራሲነት ቆይቷል፡፡ ከዚህ በኋላ ደግሞ የኢትዮጵያ ሙዚቀኞች ማህበርን በስራ አስፈፃሚነት እና በዋና ፀሃፊነት፤ ሀገር ፍቅርን ደግሞ በህዝብ ግንኙነት ባለሙያነት አገልግሏል፡፡
 ድምፃዊ ፣ግጥምና ዜማ ደራሲ ቶማስ አበበ በደርግ ዘመነ መንግስት የሳንሱር ቀንጥጫን ቀመሷል፡፡ ቤተ መንግስት ቀርቦ ፣ ማዕከላዊን ጎብኝቶ በውህኒ ቤት ለሁለት አመት ከግማሽ በእስር ቆይቷል፡፡ እዚሁ መዲናችን አዲስ አበባ ተወልዶ ያደገው ቶማስ አበበ በግጥም እና ዜማ ደርሰቱ ፤ ራሱም ሆነ ሌሎች በተጫወቱት ስራዎቹ ማህበራዊ ሂሶችን እና ትችቶችን በመስጠት፣ ስለፍቅርም ሆነ ስለ ፖለቲካ እና ስለ ሀገር ጉዳዮች አንስቷል፡፡ እሱ ከተጫወታቸው ስራዎች መካከል “አበቦች ሲያብቡ” ፣ “የጋራ ኑሮ ነው” ፣ “ጊዜው ለጨነቀው” ፣ “ቃልሽ ይገባኛል” ፣ “መስለው እየታዪት” ፣ “ያለምንም ደም እንከኗ ይውደም” እና ሌሎችም ይጠቀሳሉ፡፡

Tuesday, July 5, 2016

“የጦር ሜዳው ቀሲስ” ….. መምህር ፣ ደራሲ እና ጋዜጠኛ አበራ ለማ !!!


 አበራ ለማ  የተወለደው በ1943 ዓ.ም. ፍቼ ሰላሌ ውስጥ ነው። እድገቱ ወሊሶንና አዲስ አበባን ያካትታል። ከኮተቤ መምህራን ማሰልጠኛ ኮሌጅም በዲፕሎማ መርሃ ግብር ከፍተኛ ውጤት በማግኘቱ “የአመቱ ታላቅ ተማሪ” የሚል ሽልማትንም አግኝቷል፡፡  በዲግሪ ፕሮግራምም በኢትዮጵያ ቋንቋዎችና ሥነ ጽሑፍ ጥናት ከአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የማዕርግ ተመራቂ ነው። በጋዜጠኝነት ሙያ በኢትዮጵያ ሬዲዮና ፕሬስ መምሪያዎች ሠርቷል። ከጦር ግምባር ጋዜጠኝነት እስከ ኪነጥበባት ዘርፎች ሃያሲነት ዘልቋል።በጦር ሜዳ ዘገባውም “የጦር ሜዳው ቀሲስ” የሚል ቅፅል ስም ተሰጥቶት ነበር ፡፡


   እስከ 1980ዎቹ አጋማሽ ድረስ፥ የኢትዮጵያ ደራስያን ማኅበር ዋና ጸሃፊ ሁኖ አገልግሏል። ዛሬ የኖርዌይ ነዋሪ ነው። በኖርዌይ ደራስያን ማኅበር ብቸኛውና የመጀመሪያው ጥቁርና በአፍ መፍቻ ቋንቋው የሚፅፍ አባል ደራሲ ነው። በዚህ ማኅበር ውስጥ የዓለም አቀፍ ኮሚቴው የረዥም ዘመን አባል በመሆንም ይታወቃል። ባለቅኔ ሎሬት ጸጋዬ ገብረ መድህንንና (1997) ስዊድናዊ/ኤርትራዊ የሆነውን የአስመራውን እስረኛ፣ ደራሲና ጋዜጠኛ ዳዊት ይስሐቅን (2009 እ.ኤ.አ.) ሃሳብን በነጻ የመግለፅ ሽልማት እንዲሸለሙ በእጩነት አቅርቦ ማሸለሙም ይታወሳል።


ከአበራ ለማ የታተሙ ሥራዎች መካከል፡-
·         1967 ኩል ወይስ ጥላሸት እና አውጫጭኝ የግጥም መድብል፣
·         1974 ሽበት፣ የግጥም መድብል፣
·         1975 ሕይወትና ሞት፣ የአጫጭር ልብ ወለዶች መድብል፣
·         1976 ሞገደኛው ነውጤ፣ ኖቭሌት፣
·         1978 አባደፋር፣ ከሌሎች ደራስያን ጋር…ስብስብ፣
·         1978 ጽጌረዳ ብእር፣ ከሌሎች ገጣሚያን ጋር… ስብስብ፣
·         1980 የማለዳ ስንቅ፣ ያጫጭር ልቦለዶችና ግጥሞች መድብል፣
·         1980 መቆያ፣ ያጫጭር ልቦለዶችና ግጥሞች መድብል፣
·         1981 ትዝታን በጸጸት፣ ያጫጭር ልቦለዶች ትርጉም….በጋራ፣
·         1994 አውጫጭኝ፣ የግጥም መድብል፣
·       1994 ሙያዊ ሙዳዬ ቃላት፣ ኢልቦለድ… የቋንቋ ጉዳይ፣
·         1998 የእውቀት ማኅደር፣ ኢልቦለድ… ጠቅላላ እውቀት፣
·         2003 E.C. ULIKE HORIZON Norsk Saksprosa samling med andre forfatterer
·         እውነትም እኛ... የግጥሞች ስብስብ ቪዲዮ በዲቪዲ፣ ታህሳስ 2003 ዓ.ም.
·         ጥሎ ማለፍ.....ታሪካዊ ልቦለድ፣ ጥር 2003 ዓ.ም.
·         ሽፈራው... ሞሪንጋ   - 2006ዓ.ም
·          “ቅንጣት - የኔዎቹ ኖቭሌቶች” - 2007ዓ.ም የሚሉት ከስራዎቹ መካከል ይጠቀሳሉ፡፡ ጥቂት ድርሰቶቹም በሬዲዮ ተተርከዋል ፡፡ በተደጋጋሚ የተደመጠው እና በኢትዮጵያ ሬዲዮ በአርቲስት ፍቃዱ ተክለማሪያም አማካኝነት የተተረከው “ሞገደኛው ነውጤ” በቀዳሚነት ይቀመጣል፡፡
  

   ደራሲ ፣ ገጣሚ እና ጋዜጠኝ አበራ ለማ ከድርሰት ስራው ባሻገርም በመምህርነት ፣ በህዝብ ግንኙነት ባለሙያ እና በጋዜጠኝነት ሙያዎች በተለያዩ ተቋማት አገልግሏል፡፡ የተወሰኑ የግጥም ስራዎቹንም የተለያዩ ድምፃውያን ተጫውተውለታል፡፡ ለአብነትም ፀሀይ እንዳለ (ያሉትን ይበሉ እና ስውሩ መውደዴ) ፣ ጌታቸው ካሳ (ሀገሬን አትንኳት እና አደሴዋ) ፣ አበበች ደራራ ፣ ትዕግስት እና ሌሎችም ይጠቀሳሉ፡፡ አማርኛ ፣ ኦሮምኛ ፣ እንግሊዘኛ ፣ ኖሪጃን(የኖርዌ ቋንቋ) እና ፈረንሳይኛ ቋንቋዎችን ይናገራል፡፡

  ኑሮውን በኖርዌ ያደረገው አበራ ለማ ሰሞኑን ወደ ትውልድ ሀገሩ መጥቶ ስለ ስራዎቹ እና የህይወት ልምዱ ተጨዋወተን ነበር ፤ከዚህም በጥቂቱ አካፈልኳችሁ፡፡ ለጋሽ አበራ ለማ እድሜ እና ጤና ፣ በቀሪ ስራዎቹም ስኬትን ተመኘሁ፡፡ የቀረውን እናንተ ጨምሩበት …..