Monday, April 15, 2013



ከቤኒሻንጉል ክልል ዜጎችን ያፈናቀሉ ኃላፊዎች ተባረሩ

       በቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልል የካማሽ ዞን አስተዳዳሪ የሆኑትን አቶ መልከጅ ባጋሎንን ጨምሮ፣ ተፈናቃዮቹ ባሉበት የያሶ ወረዳ በአመራርነት የሚሠሩ አምስት ኃላፊዎች ከኃላፊነት መባረራቸውን አዲስ የተሾሙት የዞኑ አስተዳዳሪ ተናግረዋል፡፡ በአቶ መልከጅ ቦታ የተተኩት የካማሽ ዞን አስተዳዳሪ አቶ አበበ ዱቤ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ የክልሉ መንግሥት ውሳኔ ያላረፈበት ዜጎችን የማፈናቀል ድርጊት መፈጸሙ አሳዛኝ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ 

   ለበርካታ ዓመታት የኖሩት የአማራ ክልል ተወላጆች የተፈናቀሉት በድንገት በመሆኑ እህላቸውን በርካሽ እንዲሸጡ ተገደዋል፡፡ አካባቢው ገጠራማ በመሆኑ፣ ገዢ በማጣታቸውና ማጓጓዣ ስለሌላቸው የተወሰነውን አቃጥለው መውጣታቸውን ጠቁመዋል፡፡
Ethiopians illegally deported from Benshangul region to Amhara region Finote-Selam town [Photo - Addis Admass]
Ethiopians illegally deported from Benshangul region in a shelter in Finote-Selam town Amhara region [Photo - Addis Admass]
      የተፈጸመው ድርጊት ፈጽሞ መሆን ያልነበረበትና አግባብ አለመሆኑን የተናገሩት አዲሱ አስተዳዳሪ፣ ተፈናቃዮቹ እየተመለሱ እንደሆነና የማረጋጋት ሥራ እየተሠራ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ የዞኑና የወረዳው ኃላፊዎች በመሰባሰብ ተፈናቃዮቹ ያለምንም ችግር ወደየቤታቸው ተመልሰው፣ ቀድሞ በሚኖሩበት አኳኋን ከአካባቢው ነዋሪዎች ጋር የሚኖሩበት ሁኔታ ቀጣይነት እንዲኖረው ምክር እየተለገሳቸው መሆኑንም አስታውቀዋል፡፡

    እስከ አሥርና ከዚያም በላይ ከኖሩበት ቀዬ ተፈናቅለው ከ15 ቀናት በላይ በፍኖተ ሰላም ከተማ መጠለያ ከነበሩት ውስጥ የተወሰኑትን አነጋግረናቸው፣ ከሚያዝያ 2 ቀን 2005 ዓ.ም. ጀምሮ ወደ ቤኒሻንጉል ክልል እየተመለሱ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡ በመኖርያ ቤታቸው ገብተው ያላቸውንና ያጡትን ለመመልከት ባይችሉም፣ በያሶ ወረዳ ተሰባስበው በጐጥ በጐጥ (አንድ ጐጥ እስከ 50 ሰዎች ሊይዝ ይችላል) በመሆን በፖሊስ ጥበቃ እየተደረገላቸው መሆኑን፣ ከአማራ ክልልም ተከትለዋቸው የሄዱ ፖሊሶችና የጤና ባለሙያዎች መኖራቸውን አስረድተዋል፡፡ ሻቢዲ፣ ሊጐ፣ ሀሎ፣ ፋብሪኮ የሚባሉ ጐጦች መኖራቸውን የገለጹት ተፈናቃዮቹ፣ በአንድ ቀበሌ ከሦስት እስከ አምስት ጐጦች እንዳሉም ጠቁመዋል፡፡ በአጠቃላይ የተፈናቀሉት ከአምስት ሺሕ በላይ በመሆናቸው ጐጣቸውም እንደዚያው ብዙ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ 

      ከአካባቢው ተወላጆች ጋር ተግባብተው፣ ተመካክረው፣ ተረዳድተውና አንድ በሚያደርጋቸው የእምነት ተቋምም ሳይቀር ድምፃቸው ሳይሰማ መኖራቸውን የገለጹት ተፈናቃዮቹ፣ የወረዳና የዞኑ ካድሬዎች “ካገራቸው የመጡት የማዳበሪያ ክፍያ ሳይፈጽሙ፣ መሣሪያ ተነጥቀውና ግብር ሳይከፍሉ ነው፡፡ ሕገወጦች፤” በማለት ያለስማቸው ስም ሰጥተው ለዓመታት የኖሩበትን ቤት ሳይዘጉት፣ ገበያ እንደወጡና ውኃ ሊቀዱ እንደወረዱ በኃይል አስገድደው እንዳፈናቀሏቸው አስረድተዋል፡፡
ከ15 ቀናት በላይ በኖሩበት የምዕራብ ጎጃም ፍኖተ ሰላም ከተማ የከተማው ፖሊስ መምሪያው፣ ነዋሪዎችና የምግብ ዋስትና ጽሕፈት ቤት ላደረጉላቸው እንክብካቤ አመስግነው በክልሉ ባለሥልጣናት ግን ማዘናቸውን ገልጸዋል፡፡

    “ሕገወጦች ናቸው ተብለን ተከሰን ከኖርንበት አካባቢ ስንመጣ አንድም የክልሉ ባለሥልጣናት አልደረሱልንም ወይም በተጠለልንበት ቦታ መጥተው አልጠየቁንም፡፡ ወይም ትክክል ነው የወሰዱት መሣሪያ አለ፣ ግብርም አልከፈሉም፣ የማዳበርያ ክፍያም አለባቸው ብለው ቀርበው አልከሰሱንም፤” ያሉት ተፈናቃዮቹ፣ እነሱ ዝም ሲሏቸው “ለምን?” ብለው ራሳቸው ሲጠይቁ፣ “ድሮም እኛ ሂዱ አላልናችሁም፡፡ የሄዳችሁት በራሳችሁ ጊዜ ነው፡፡ አሁን ቀድሞ ወደምትኖሩበት ቀዬ ግቡ አሉን፤” ብለዋል፡፡

    እነሱ ወደ ክልሉ የሄዱት በሁለት ምክንያት መሆኑን የተናገሩት ተፈናቃዮቹ፣ ቀደም ሲል የነበራቸው መሬት በመጥበቡና ለኑሮ አመቺ ባለመሆኑ ሲሆን፣ በሌላ በኩል ደግሞ ሕገ መንግሥቱ በፈቀደላቸው በማንኛውም ቦታ ተዘዋውረው ሀብት የማፍራት መብታቸውን ለመጠቀም መሆኑን ገልጸዋል፡፡ የክልሉ ፕሬዚዳንት አቶ አህመድ ናስርና የተባበሩት ዓረብ ኤምሬት የኢትዮጵያ ቆንስላ የነበሩትንና አሁን የክልሉ ምክትል ፕሬዚዳንት የሆኑትን አምባሳደር ምሥጋኑ አረጋን፣ በተፈናቃዮቹም ላይ ዳግም ተመሳሳይ ችግር እንዳይፈጠር በቀጣይ ምን ለማድረግ እንደታሰበ ማብራርያ እንዲሰጡን ያደረግነው ጥረት፣ ስብሰባ ላይ መሆናቸውን ከማወቅ በዘለለ ምላሽ ማግኘት አልቻልንም፡፡ ከክልሉ በቅርቡ እንዲፈናቀሉ የተደረጉ ዜጎችን በተመለከተ ከአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ማብራሪያ ለመጠየቅ ብንሞክርም ሊሳካ አልቻለም፡፡

                                                                        Source: Ethiopian Reporter – April 14, 2013
                                                                           

No comments:

Post a Comment