Thursday, February 2, 2023
የመጀመሪያዋ ኢትዮጵያዊት ሴት ጋዜጠኛ ወይዘሮ ሮማነወርቅ ካሣሁን
የታላላቅ ስራዎች ባለቤት ከሆኑ ሴቶች መካከል አንዷ የሆኑት የመጀመሪያዋ ኢትዮጵያዊት ሴት ጋዜጠኛ ወይዘሮ ሮማነወርቅ ካሣሁን በጋዜጠኝነት፣ በደራሲነትና በጸሐፌ ተውኔትነት ልዩ ልዩ ተግባራትን አከናውነዋል፡፡ የመጀመሪያዋ ኢትዮጵያዊት ሴት ጋዜጠኛ ወይዘሮ ሮማነወርቅ ካሣሁን ከአባታቸው ከአቶ ካሣሁን እንግዳሸት እና ከእናታቸው ከወይዘሮ አለሙሽ ዓለም በ1914 ዓ.ም አዲስ አበባ ከተማ ውስጥ ተወለዱ፡፡ እድሜያቸው ለትምህርት ሲደርስም ቅድሥት ሥላሴ ቤተ-ክርስቲያን መንፈሳዊ ትምህርት ቤት ገብተው የቤተ-ክርስቲያን ትምህርት በመማር ዳዊት ደገሙ፡፡ ከዚያም ስዊድን ሚሲዮን ትምህርት ቤት በመግባት በጊዜው ይሰጥ የነበረውን ዘመናዊ ትምህርት ተማሩ፡፡ በትምህርት ቤት ቆይታቸውም የወቅቱን “ሴት ለትምህርት አልተፃፈችም” የሚለውን ልማድ በጥረታቸውና በትጋታቸው በመቋቋም በትምህርት ቤት ቆይታቸው የአንደኛነት ደረጃን በመያዝ በአውሮፓውያን አስተማሪዎቻቸው ይሸለሙ ነበር፡፡ በስዊድን ሚሲዮን ትምህርት ቤት ይማሩ በነበረበት ወቅትም ከአውሮፓውያን መምህራን ያገኙት ዘመናዊ ትምህርት ከተፈጥሮ ችሎታቸው ጋር ተደምሮ በጥናትና ንባብ ያዳበሩትን እውቀታቸውን ወደአደባባይ ማውጣት ስለፈለጉ በጥር ወር 1939 ዓ.ም በወቅቱ “የማስታወቂያና ፕሮፖጋንዳ ሚኒስቴር” ተብሎ ይጠራ በነበረው መስሪያ ቤት የመጀመሪያዋ ሴት ጋዜጠኛ በመሆን ተቀጠሩ፡፡
በማስታወቂያ ሚኒስቴር ውስጥ ባገለገሉባቸው ጊዜያት በሬዲዮ ዜና አጠናቃሪነት፣ በዜና አንባቢነት፣ በሴቶች ፕሮግራም አዘጋጅነት ሰርተዋል፡፡ በተለይ “ለወይዛዝርት” የተባለውና በሳምንት ሁለት ጊዜ በኢትዮጵያ ሬዲዮ የሚቀርበው ፕሮግራም አዘጋጅና አቅራቢ ነበሩ፡፡ በዚህ ፕሮግራም ላይ በትያትርና በውይይት መልክ የሚያቀርቧቸው ትምህርታዊ መሰናዶዎች ስለ ቤት ባልትና፣ ስለ ልጅ አስተዳደግና ስለ መልካም ቤተሰብ ኑሮ ያወሱ ነበርና በአድማጮች ዘንድ “እውነትም ሮማነወርቅ” አሰኝቷቸዋል፡፡ በዚሁ መስሪያ ቤት ውስጥ አንድም ቀን “ሰለቸኝ” ሳይሉ በየጊዜው ለአድማጭ አዲስ ነገር ይዞ በመቅረብ ለ25 ዓመታት ያህል ለሙያቸው በመታመን ያገለገሉት ጋዜጠኛ ሮማነወርቅ፣ ለሴቶች ብቻ ሳይሆን ለወንዶችም (በተለይ ደግሞ ለጋዜጠኞች) አርዓያ መሆን ችለዋል፡፡ ይህም ከፍተኛ የሆነ ተወዳጅነትንና አድናቆትን አስገኝቶላቸዋል፡፡
ወ/ሮ ሮማነወርቅ ካሣሁን በህይወት ዘመናቸው ከሚወዱት የጋዜጠኝነት ሙያ በተጨማሪ ደራሲም ናቸው፡፡ ወይዘሮ ሮማንወርቅ ካሣሁን የመጀመሪያ መጽሐፋቸውን “ትዳር በዘዴ” በ1942 ዓ.ም ለእትመት አብቅተዋል። መጽሐፉ የገጠሩንና የከተማውን ትዳርና ኑሮ የሚያነፃፅር ሲሆን በውስጡም በገጠር ያለውን የሕይወት ውጣ ውረድ ዘርዝሮ ያቀረበ ነው፡፡ ከአንድ ዓመት በኋላ በ1943 ዓ.ም ሁለተኛ መጽሐፋቸውን “ማህቶተ ጥበብ” መፅሐፍ በትያትር መልክ በማዘጋጀት ለህትመት አበቁ፡፡ መፅሃፉ በወቅቱ ሕይወታቸው ስላለፈው ስለ ልዕልት ፀሐይ ኃይለሥላሴ ሕይወት የሚያወሳ ነው፡፡ በ1948 ዓ.ም ሦስተኛ መጽሐፋቸውንም ለህትመት አብቅተዋል፡፡
ከዚህ በተጨማሪም ወይዘሮ ሮማንወርቅ ጽሁፎቻቸውን በተለያዩ ጋዜጦችና መጽሔቶች ላይ በማሳተም በሕትመት መገናኛ ብዙኃን ላይም የፋና ወጊነት ሚናን ተጫውተዋል፡፡ የ“መነን” መጽሔት አዘጋጅ ከመሆናቸውም በተጨማሪ የሴቶችን ሕይወት የሚመለከቱ ልዩ ልዩ ትምህርታዊ (የምክር) ጽሑፎችን በጋዜጦችና በመጽሔቶች ላይ በመፃፍም የታወቁና የተደነቁ ነበሩ፡፡
ወይዘሮ ሮማንወርቅ በሙያቸው ላበረከቱት አስተዋፅኦና ላሳዩት ከፍተኛ ስራ ብርታትና ትጋት የተለያዩ ሽልማቶችን አግኝተዋል፡፡ ከሽልማቶቹ መካከልም ከኢትዮጵያ ንጉሰ ነገሥት መንግሥት የወርቅ ሜዳልያ እና በ1956 ዓ.ም የኢትዮጵያ ደራሲያን መታሰቢያ ሽልማት - የብር ሜዳሊያ ይጠቀሳሉ፡፡ ወይዘሮ ሮማነወርቅ የጤና እክል አጋጥሟቸው በሕክምና ሲረዱ ቆይተው ጥር 23 ቀን 1964 ዓ.ም አረፉ፡፡ ስርዓተ ቀብራቸውም በማግስቱ የማስታወቂያ ሚኒስቴር ሹማምንትና ሰራተኞች እንዲሁም እጅግ በርካታ ሕዝብ በተገኘበት አዲስ አበባ ከተማ ውስጥ በቀጨኔ መድኃኔዓለም ቤተ-ክርስቲያን ተፈጽሟል፡፡ ሞት ቀደማቸው እንጂ “ሔዋን” ፣ “መልካም እመቤት” ፣ “የቤተሰብ አቋም” ፣ “የባልትና ትምህርት” ፣ “የሕፃናት ይዞታ” ፣ “ዘመናዊ ኑሮ” ፣ “የኑሮ መስታዎት” ፣ “ጋብቻና ወጣቶች” ፣ እንዲሁም “የባልና የሚስት ጠብ” በሚሉ ርዕሶች መጻሕፍትን አዘጋጅተው ለሕትመት ለማብቃት እየሰሩ እንደነበረም ይነገራል፡፡ ክብር ለሚገባው ክብር እንስጥ….
Subscribe to:
Post Comments (Atom)
No comments:
Post a Comment