Wednesday, December 23, 2020

አንጋፋው የስፖርት ጋዜጠኛ እና ሁለገቡ የጥበብ ሰው ኢብራሂም ሀጂ ዓሊ አረፉ፡፡

ጋዜጠኛና አርቲስት ኢብራሂም ሀጂ ዓሊ 2012 ዓ.ም ክረምት ጀምሮ ታመው የሕክምና እርዳታ ሲደረግላቸው ቆይቶ ከዚህ ዓለም በሞት ተለይተዋል፡፡


ጋዜጠኛና አርቲስት ኢብራሂም ሀጂ ዓሊ ለአፋን ኦሮሞ ቋንቋ እድገት ከፍተኛ አስተዋጽኦ አበርክተዋል፡፡ ተወልደው ባደጉበት በድሬዳዋ ሙዚቃን እንደጀመሩም ይወሳላቸዋል፡፡ 1967/68 የአፍረን ቀሎ ባንድ 2 ትውልድ በመባል በሚጠራው የአዱ ቢራ ባንድ መስራቾች ከሚባሉት የክብር ዶክተር አርቲስት አሊ ቢራ፣ ሂሜ የሱፍ፣ አብዱ ሸኩር፣ መሀመድ ጠዊል ጋር በመሆን የባንዱ መስራችም ነበሩ፡፡ በአፍረን ቀሎ ባንድ ውስጥ  ሲያቀርቧቸው በነበሩት የሙዚቃ ስራዎቻቸው የሚታወቁ ሲሆን፣ አራት የሙዚቃ መሳሪያዎችን መጫወት እንደሚችሉም ይነገርላቸዋል፡፡ የዘፈን ግጥም እና ዜማም ይደርሱ ነበር፡፡ የድሬዳዋ ጨርቃ ጨርቅ እግር ኳስ ተጫዋችም እንደነበሩ አንዳንድ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡

ጋዜጠኛ እና አርቲስት ኢብራሂም ሀጂ ዓሊ የበሪሳ ጋዜጣ ላይ በጋዜጠኝነት አገልግለዋል፡፡ ከዚያም 197ዐቹ ውስጥ በኢትዮጵያ ሬዲዮ የኦሮምኛ ክፍል የስፖርት ዝግጅትን በየሣምንቱ እየተመላለሱ ከተስፋዬ ቱጂ ጋር የነፃ አገልግሎትም ሰጥተዋል፡፡ 1987 ..ጀምሮ ሙሉ ለሙሉ ወደ ሬዲዮ ጋዜጠኝነት በመግባት በሬድዮ ፋና ውስጥ በፕሮግራም አዘጋጅነትና በኤዲተርነት ያገለገሉ ሲሆን፣ በተለይ በፋና አፋን ኦሮሞ ፕሮግራም አዘጋጅነት አድናቆትን ያተረፉ አንጋፋ ጋዜጠኛ ነበሩ፡፡


በአፋን ኦሮሞና በአማርኛ ቋንቋ የስፖርት ክፍል አስተባበሪና አዘጋጅ በመሆንም አገልግለዋል፡፡ ከመደበኛ ሥራቸው ውጭ ኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ ሻምፒዮናዎችን ስታዘጋጅ የሕዝብ ግንኙነት አባል በመሆን በየዝግጅቶቹ የመጽሔት አዘጋጅ በመሆን ሰርተዋል፡፡

በሀገር አቀፍ ሻምፒዮናዎች ላይም ጉልህ አስተዋጽኦ አበርክተዋል፡፡ በአትሌቲክስ ፌደሬሽን፣ በኢትዮጵያ እግር ኳስና በባድሜንተን ፌደሬሽንም የሕዝብ ግንኙነት አባል በመሆን ነፃ አገልግሎት ሰጥተዋል፡፡ በፋና ሬዲዮ የስፖርት የቀጥታ ሥርጭት ውይይትማካሄድ እና የዘፈን ግምገማም ከተባባሪዎቹ ጋር ሰርተዋል፡፡ በፊንፊኔ FM ሬዲዮ የእንግሊዝ ኘሪሚዬር ሊግን በቀጥታ ሥርጭት በኮሜንታተርነት አገልግሎት ሰጥተዋል፡፡


ባለፈው ዓመት የዓለም አቀፍ ሬዲዮ ቀንን ምክንያት በማድረግ የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን ከኢትዮጵያ ብሮድካስት ባለስልጣን፣ ከዩኔስኮና ከሌሎች የሚመለከታቸው አካላት ጋር በመተባበር በአገር አቀፍ ደረጃ ባከበረበት ወቅትም በጋዜጠኝነት ዘርፍ ላበረከቱት የረጅም ዘመን አገልግሎትም እድሜ ያልገደበው ጋዜጠኛ” በማለት የእውቅና የምስክር ወረቀትና የወርቅ ሃብል ሽልማት ተበርክቶላቸዋል፡፡

ለጋዜጠኛና አርቲስት ኢብራሂም ሀጂ ዓሊ እረፍተ ነፍስን ፤ ለቤተሰቦቻቸውለወዳጅ ዘመዶቻቸው እና ለአድናቂዎቻቸው ደግሞ መፅናናትን እንመኛለን።

No comments:

Post a Comment