Thursday, March 10, 2022

ሁለገብ የጥበብ ሰው ካሳዬ ገበየሁ ኮረሪማ… !!!


አርቲስት ካሳዬ ገበየሁ ኮረሪማ የኪነ ጥበብ ጅማሮው በአርሲ ባህል ኪነት ቡድን ነው፡፡ አርቲስቱ ከታዳጊነቱ ጀምሮ በባህል ውዝዋዜ በድምፃዊነት ተዋናይነት መድረክ ዝግጅት እና በድርሰት ሙያ ተሳትፏል፡፡ በራስ ትያትር ህፃናት እና ወጣቶች ሀገር ፍቅር እና ትያትር እና ባህል አዳራሽ (ማዘጋጃ ቤት) ከባለሙያነት እስከ አመራርነት ባሉት ኃላፊነቶች ሰርቷል፡፡

ከትውልድ ቅዬው በ1980ዎቹ ወደ አዲስ አበባ በመምጣት በጊዜው በነበሩ ኪነቶች ውስጥም ይሰራ ነበር፡፡ ከዚያም በአዲስ አበባ ትያትር እና ባህል አዳራሽ በባህል ተወዛዋዥነት ተቀጥሮ ስራን አሀዱ ብሎ ጀመረ፡፡ ከዚያ በኋላ በራስ ትያትር - በድምፃዊነት እና በትወና፤ በራስ ትያትር - በድምፃዊነት እና ትወና ፤ በህፃናት እና ወጣቶች - በስቴጅ ማኔጀርነት እንዲሁም  በሀገር ፍቅር - ለ3 አመት ያህል በስራ አስኪያጅነት አገልግሏል፡፡ 

አርቲስት ካሳዬ ገበየሁ በተለያዩ የሬዲዮ እና የቴሌቭዥን ድራማዎች ላይ ተሳትፏል፡፡ በብዙዎች ዘንድ “የቀን ቅኝት” በተሰኘው የሬዲዮ ድራማ ላይ በሚጫወተው የ “ደምለው” ገፀ ባህሪ ተወዳጅነትን አትርፏል፡፡ ከገፀ ባህሪ ባለቤቱ “አንጓች” - አስቴር በዳኔ ጋር የነበራቸው መናበብ እና ብቃትም በአድማጭ ዘንድ እውቅናን እንዲያገኙ አድርጓቸዋል፡፡ ከሬዲዮ ድራማ በሻገርም “ማረፊያ ያጣች ወፍ”፣ “ኖላዊ”“መስኮት” እና ሌሎች የቴሌቭዥን ድራማዎች ላይ ሰርቷል፡፡  “ከዘራው” የተሰኘ ፊልም በመድረስም ለተመልካች አቅርቧል፡፡

በትያትር ረገድም “ጤና ያጣ ፍቅር”“የምሽት ፍቅረኞች”“ሮሚዮ እና ጁሌት”“ደመና” እና የተለያዩ  ሙዚቃዊ ተውኔቶች ላይ በማዘጋጀት እና በመተወን ተሳትፏል፡፡ አሁን ደግሞ ስራን አሀዱ ወደአለበት ትያትር ቤት ተመልሶ  የአዲስ አበባ ትያትር እና ባህል አዳራሽ(ማዘጋጃ ቤት)ን በስራ አስኪያጅነት እያገለገለ ይገኛል፡፡ ስለ አርቲስት ካሳዬ ገበየሁ እኔ ከብዙ በጥቂቱ ይህንን አጋርቻችኋለሁ፤ በተረፈ እናንተ ጨምሩበት፡፡ 

Tuesday, March 1, 2022

ብእረ ሃይለኛው ፣ ድምፀ ጎርናናው እና ስለ ስመ ገናናው ጋዜጠኛ አለምነህ ዋሴ!!!

በአሜሪካ ኋይት ሃውስ ከትልቁ እስከትንሹ ቡሽ አብሮ ምሳ የበላ፣በታላቋ ሞስኮቭ ተገኝቶ ቦሪስ የልሲንን የዘየረ፣ ከቭላድሚር ፑቲን ጋር በአንድ ማእድ የቀረበ፣በባህረሰላጤው ሰፈር የገነነ፣ የሳዳም ሁሴን ባልነጀራ፣ የኩየት አሚሮች ምስጢረኛ የእስራኤል ፕሬዝዳንቶች አማካሪ ነው የሚመስለው፡፡እሱ ከምድሪቱ ማእዘናት ከብዙ ማይልስ ርቀት የተከናወነውን በየደጃፋችን ያደረሰ፤ በአስገምጋሚ ድምፁ በማራኪ ቃላቱ በአጫጭር ሃሳቦቹ ሰፊዋን ዓለም በርብሮ፣አጥብቦና አቅርቦ ዝና ገመናዋን እየዘረገፈ ለኢትዮጵያውያን ሲመግብ የኖረ ነው፡፡ ይህ ሰው ብእረ ሃይለኛው ድምፀ ጎርናናው ስለ ስመ ገናናው ቁመተ ለግላጋው አመለ ሸጋው የሬዴዮ ወዳጅ እና አገልጋይ ዝነኛው ጋዜጠኛ አለምነህ ዋሴ፡፡

 የከያኒያን አምባ ከተሰኘችው ፈረንሳይ ለጋሲዮን መንደር ነው የተገኘው፡፡እዚሁ አዲስ አበባ፡፡የአንደኛ ደረጃ ትምህርቱን በህዝባዊ ሰራዊት እና ሚያዚያ 23 ከፍተኛ 2 ደረጃ ትምህርቱን ደግሞ በኮከበ ጽባህ እና እንጦጦ አጠቃላይ አጠናቋል፡፡ በሂሳብ ሙያ አያያዝ (አካውንቲንግ) ዲፕሎማ አግኝቷል። በጥር 1 ቀን 1979 . ገና 20 አመት ወጣት እያለ ነው ኢትዮጵያ ሬዴዮንን የተቀላቀለው። ከከዋክብቱ አንጋፋ ጋዜጠኞች ጋር አበረ፡፡ የኢትዮጵያ የዜና አባት ከሚለው ጌታቸው /ማርያም እግር ስር ሙያ ቀሰመ፡፡ የመዝናኛው መሃንዲስ እያለ የሚያሞካሸውን ታደሰ ሙሉነህ በቅርበት የማወቅ እድል አገኘ፡፡ ከገናናዎቹ ዳሪዮስ ሞዲ ነጋሽ መሃመድ ዘንድ አብሮ የመስራት እድል ፈጠረ፡፡በቃ ከዛ ግዜ ጀምሮ ላለፉት 35 ዓመታት ለዓለምነህ ሬዴዮ የክብር ሰገነቱ የንፅህና ምኩራቡ ሆነ፡፡

በእርግጥ አንዳንዶች ባህረሰላጤው ጦርነት የሳዳም እና ጆርጅ ቡሽ ዛቻና ስድድብ ለአለማችን ህዝብ አስጨናቂ ቢሆንም ለዓለምነህ ግን እንጀራ ሆኖታል እያሉ ይቀልዳሉ፡፡ የታዋቂነትና የተወዳጅነትን በር ሰተት አድርጎ የከፈተለት ይሄው ጦርነት ነበርና፡፡ እሱም ቢሆን ሳዳም ሁሴን ባለውለታዬ ነው እያለ ደጋግሞ ተናግሯል፡፡አድናቆት እና ዝናው ከጋዜጠኝነት ለለጠቀው የማስታወቀያ ስራ ስኬት ብዙ ደንበኛ አፍርቶለታልና፡፡

በኢትዮጵያ ሬዴዮ፣ በሬዴዮ ፋና አሁን ደግሞ በብስራት ሬዴዮ ሪፖርት ሰራ፡፡ ዜና መራ፡፡ ውጭና የአገር ውስጥ ትንታኔ አዘጋጀ፡፡ ትረካ ፃፈ፤ በውይይት ተሳተፈ በስፖርት ዝግጅቶቹ አንፀባረቀ፡፡ ከአገሩ ርቆ በእስራኤል በነበረበት የስደት ዘመን እንኳን ከሬዴዮ ጋር ብቻ እንደቆረበ ሰነበተ፡፡ አዋዜ ሬዴዮ ብሎ በኢንተርኔት ሬዴዮ ወደህዝብ መምጣቱን አላቋረጠም፡፡ በመጽሄቶች ላይ በርካታ መጣጥፎቹን አስነብቧል፡፡ የፌዶር ዶስቶቭስኪን መጽሃፍ ተርጉሞ ለንባብ አቅርቧል።

ሬዴዮ በኢትዮጵያ ተወዳጅ እንደሆነ እንዲዘልቅና በርካቶች ወደሙያው እንዲቀላቀሉ በማድረግ ለተወጣው ሃላፊነት 3ኛው ዓለም አቀፍ የሬዴዮ ቀን በተከበረበት እለት የህይወት ዘመን የሬዴዮ ባለውለታ ተሸላሚ ሆኖ ተመርጧል፡፡ (ተፃፈ ፀሀፈ በዮናስ ወልደየስ)

በድምፅ ከፈለጉ ሊንኩን ክሊክ አድርገው ያድምጡ https://www.youtube.com/watch?v=x6qReQKmu_k