Sunday, July 30, 2017

ሀምሌ ወር በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ ….. !!!


ሀምሌ 1 - 1927 ዓ.ም የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር ተቋቋመ
ሀምሌ 5 - 1829 ዓ.ም አፄ ዮሀንስ 4ኛ ተወለዱ
-   1942 ዓ.ም ባለቅኔ ደበበ ሰይፉ ተወለደ
-   1865 ዓ.ም አፄ ዮሀንስ 4ኛ- አፄ ተክለጊዮርጊስን ድል አድርገው ማረኳቸው
-  1984 ዓ.ም ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ ፓትርያርክ ሆነው ተሾሙ
-     1971 ዓ.ም የኢህአፓ አመራር የነበረው ብረሃነመስቀል ረዳ በደርግ ተረሸነ
ሀምሌ 7 - 1971 ዓ.ም ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ቴዎፍሎስ በደርግ እጅ ተገደሉ፤
              ሀምሌ 4, 1984 ዓ.ም አፅማቸው በክብር አርፏል
-     አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ 1357 ዓ.ም ተወለዱ
-     አርቲስት ቴዎድሮስ ካሳሁን በ1968ዓ.ም ተወለደ

ሀምሌ 9 - 1923 ዓ.ም ንጉሰ ነገሥት ቀዳማዊ አፄ ኃይለሥላሴ ኢትዮጵያ ታሪክ      የመጀመሪያ የሆነውን የተፃፈ ሕገ-መንግሥት አፀደቁ፤ ህገ-መንግስቱ መምጣቱም   ሀምሌ 16 1931 . በተካሄደ ታላቅ ድግስ ላይ ታወጀ…

ሀምሌ 11 - 1927 ዓ.ም የሀገር ፍቅር ማህበር /የአሁኑ ሀገር ፍቅር /ቴያትር ቤት ተመሰረተ
ሀምሌ 16 - 1884 ዓ.ም ንጉሰ ነገስት አፄ ኃይለስላሴ (ተፈሪ መኮንን) ተወለዱ


-   1937 ዓ.ም የቀድሞው ቀዳማዊ ኃይለስላሴ 2ኛ ደረጃ ት/ቤት የአሁኑ ኮተቤ መምህራን ማሰልጠኛ ኮሌጅ ተቋቋመ በቅርቡ ደግሞ ኮተቤ የኒቨርስቲ ኮሌጅ ተብሏል
-   1938 ዓ.ም አቡነ ጴጥሮስ የመታሰቢያ ሀውልት ቆመላቸው

ሀምሌ 18 - 1985 ዓ.ም ድምፃዊ ኬኔዲ መንገሻ ከዚህ አለም በሞት ተለየ፤ ሀምሌ 19 የቀብር ስነ- ስርዓቱ ተፈፀመ


ሀምሌ 20 - 1869 ዓ.ም ነጋድራስ ተሰማ እሸቴ ተወለዱ
ሀምሌ 22 - 1928 ዓ.ም ብፁዕ አቡነ ጴጥሮስ በፋሽስት ጣሊያን ተገደሉ



ሀምሌ 26 - 352 ዓ.ም አባ ሰላማ ከሳቴ ብርሃን (ቅዱስ ፍሬምናጦስ) አረፉ….፡፡ የጎደለውን ሞልታችሁ ፣ የዘመመውን አቃንታችሁ እና አስፋፈታችሁ መረጃ እንደምታጋሩኝ እምነቴ ነው፡፡ እኔ ይቺን ለቅምሻ ብያለሁ……!!!

Thursday, May 18, 2017

የልብ ጓደኝነት እንዴት ይገለፃል፤ እውነተኛ የልብ ጓደኛስ ይኖር ይሆን …..?


   መልካም ጓደኝነትን በዕጣ ወይም በሒሳብ ቀመር ተጠቅመን የምናገኘው ነገር ባይሆንም የራሱ የሆኑ መመዘኛዎች ግን ይኖሩታል፡፡ እውነተኛ ጓደኞች ውድና ብቅር እንደሆነ አልማዝም ናቸው ፡፡ የችግር ተካፋይ፣ የሐዘን አጋሮች፣ ተስፋ የቆረጠውን ተስፋውን የሚያለመልሙ ፣ የወደቀውን የሚያነሡ ከጨለማ ወደ ብርሃን ፣ ከሞት ወደ ሕይወት የሚመልሱ በአጠቃላይ ከጎናችን ሆነው የሕይወት ስንክሣራችንን የሚጋሩ ጓደኞች ዋጋቸው ከወርቅም ከዕንቁም የበለጠ ነው፡፡ አብሮን የዋለ አብሮን ያደረ በተለያየ እንቅስቃሴአችን ውስጥ የምናገኘው ሰው ሁሉ የልብ ጓደኛችን ሊሆን አይችልም፤ ነገር ግን ከእነዚህ ሰዎች መሀል ሃሣቡ ከሃሣባችን፣ ዓላማው ከዓላማችን፣ ሕይወቱ ከሕይወታችን የሚገጣጠመው ብቻ ባልንጀራችን ይሆናል፡፡


  ብዙ ሰዎች በጓደኝነት ጉዳይ ብቻም ሳይሆን በሌሎች ነገሮች ላይም እነርሱ ያልሆኑትን ከሌላው የመመኘት ባሕርይ አለ፤ ነገር ግን ሰዎች እንዲታመኑልን ከፈለግን እኛ ታማኝ፣ ሰዎች እንዲያፈቅሩን ከፈለግን እኛ የፍቅር ሰዎች መሆን፣ ሰዎች ይቅር እንዲሉን ከፈለግን እኛ የይቅርታ ልብ ሊኖረን ይገባል፡፡  በአጠቃላይ መልካም ጓደኛ ለማግኘት ከፈለግን እኛም ለሌሎች ጥሩ ጓደኞች መሆን ይጠበቅብናል፡፡

 አንዳንድ ሰዎች ጓደኝነትን የሚመሠርቱት ጥቅም ለማግኘት ሆን ብለው አስበው፣ በሽንገላ ከንፈር አንደበታቸውን በማጣፈጥ፣ ንብረት ለመውረስ ፣ ገንዘብ ለመዝረፍ ይሞክራሉ ፤ ከተሳካላቸውም ያደርጉታል፡፡ ጓደኛዬ ባሉት ሰው ትከሻ ተረማምደው ከሀብት ርካብ፣ ከሥልጣን ኮርቻ ላይ ከተፈናጠጡ በኋላ ያንን ሰው ከነመፈጠሩ ይረሱታል፡፡

 የልብ ጓደኝነት በዘር፣በቋንቋ፣ በአንድ አካባቢ ተወላጅነት ወዘተ ላይ በመመስረት ሊመጣ የሚችል አይደለም፡፡ ጓደኝነት በፍፁም ፍቅር ላይ የተመሠረተ መሆን አለበት፡፡ መልካም ጓደኛ ለችግር ጊዜ ደራሽ ፣ በመከራ ፣ በሐዘን፣ በደስታ ተካፋይ፣ መልካም አማካሪና፣ ገመናን ሸፋኝ ነው፡፡ 

    እውነተኛ ጓደኝነት በሁለቱ ሰዎች ብቻ ተወስኖና ከቤት ውጪ የሚደረግ ሆኖ አይቀርም፡፡ አንዱ በሌላው ቤተሰብ ታውቆና ተወዳጅቶ ዝምድናን ይፈጥራል፡፡ በጓደኛው ቤተሰብ ውስጥ በሚፈጠር ሐዘንም ሆነ ደስታ ተካፋይ ይሆናል፡፡ ጓደኝነት ዘወትር ፍጹምነት ሊኖረው አይችልም አልፎ አልፎ አንዳንድ ልዩነቶች እና አንደኛውን ወገን የሚያሳዝኑ ነገሮች በማወቅም ባለማወቅም ሊከሠቱ ይችላሉ፡፡ እንዲህ አይነት ጥቃቅን ነገሮችን በመቻቻል ማሳለፍ ከእውነተኛ ጓደኝነት ባሕርያት አንዱ ነው፡፡ በመሆኑም በመልካም ጓደኝነት ውስጥ ይቅር ባይነትና መቻቻል አስፈላጊ እና ሊኖርም ይገባል፡፡


  መልካም ጓደኝነት በአፍ(በቃል) ሳይሆን በተግባር የሚገለጽ ነው፡፡ ሲለያዩ የሚረሣሡ፣ በአጋጣሚ ካልሆነ በምክንያት የማይገናኙ፣ የልባቸውን የማይተዋወቁ፣ የዓላማ አንድነት፣ የባሕርይ ተመሳሳይነት የሌላቸው ነገር ግን ጓደኛሞች ነን የሚሉ ካሉ ተሳስተዋል፣ ይህ ጓደኝነት ከዕለታዊ ወይም ከወቅታዊ ግንኙነት የተሻለ አይደለምና፡፡ እውነተኛ ጓደኝነት እስከመስዋዕትነት የሚያደርስ ገንዘብንና ቁሳቁስን ብቻ ሳይሆን ነፍስን እስከመስጠት ሊያደርስ የሚችል ነው፡፡ እንግዲህ ጥሩ ጓደኛ እንደምንፈልግ ሁሉ እኛም ለሌላው ጥሩ ጓደኛ ለመሆን መዘጋጀት ይኖርብናል ፡፡
       “ ብረት ብረትን ይስለዋል፥ ሰውም ባልንጀራውን ይስላል።

Tuesday, May 2, 2017

ደስታ፣ ሳቅ እና ጨዋታ የእሳቸው መለያ ናቸው ... ተዋናይት አስካለ አመነሸዋ


 “ለእኔ ራሱ ግርም ይለኛል ጭንቅላቴ ካሴት ማለት ነው አንዴ የተነገረኝን /የያዝኩትን/ ቶሎ አልረሳም በቃ ካሴት በሉኝእያሉ ጨዋታቸውን ሲያዥጎደጉዱት አፍ ያስከፍታሉ፡፡
   
  የብሄራዊ ቲያትሯ መሪ ተዋናይ አርቲስት አስካለ አመነሸዋ ከትወናው አለም እስከተገለሉበት ጊዜ ድረስሂሩት አባቷ ማን ነው ጨምሮ 40 በላይ ቲያትሮች ላይ ተሳትፈዋል፡፡ የድል አጥቢያ አርበኛ፣ ስነ-ስቅለት፣ አሸርቶስ ንጉስ፣ ቂመኛው ባህታዊ፣ ስራሽ ያውጣሽ፣ ታርቱፍ፣ ማንም ሰው፣ ደህና ሁኚ አራዳ፣ ደመ መራራ፣ ንግስት ሳባ፣ አንድ አመት ካንድ ቀን፣ በህይወት ዙሪያ፣ ቴዎድሮስ፣ ስስታሙ መንጠቆ፣ አስቴር፣ ጎንደሬው /ማሪያም፣ አወናባጅ ደብተራ፣ ምኞቴ፣ የሺ፣ እኝ ብዬ መጣሁ፣ ለሰው ሞት አነሰው፣ ኦቴሎ፣ የበጋ ሌሊት ራዕይ፣ የከተማው ባላገር፣ ጠያቂ እና የአዛውንቶች ክበብን ለአብነት መጥቀስ ይቻላል፡፡ በአንጋፋው ጋዜጠኛ እና ደራሲ ነጋሽ /ማሪያም የተደረሰው የአዛውንቶች ክበብ የመጨረሻ ስራቸው እንደሆነም ይናገራሉ፡፡
  

   በኢላላ ኢብሳ የተደረሰ በኢትዮጵያ የመጀመሪያው ነጭ እና ጥቁር ፊልም ነው፡፡ ፊልሙ በሃገር ፊልምና ማስታወቂያ ስራ አማካኝነት በሆሊዩድ ነው የተሰራው፡፡በ35 ሚሊ ሜትር የተሰራው ይህ ፊልም በህይወት ውጣ ውረድ ውስጥ ስለምትኳትን አንዲስ ሴት እና በልጇ ህይወት ላይ ትኩረቱን ያደረገ ነው፡፡ በዚህ ፊልም ላይ ከተወኑት አንዷ አርቲስት አስካለ አመንሸዋ ሲሆኑ በመሪ ተዋናይነት የፅዲቱን የቡና ቤት ገፀ ባህሪይ ተላብሰው ተውነዋል፡፡ ቀደም ባለው ጊዜ ከንጉሰ ነገስቱ የወርቅ የአንገት ሀብል፣  “የሂሩት አባቷ ማን ነው” 50 አመትን ምክንያት በማድረግ ዋንጫ እና የገንዘብ ሽልማት ተበርክቶላቸዋል፡፡ ባለፈው አመት ደግሞ “የጉማ ሽልማት” ዓመታዊ ክብረ በዓል በኢትዮጵያ የፊልም ጥበብ የ2008ዓ.ም ምርጥ የእድሜ ዘመን ተሸላሚ ሆነዋል፡፡


 
  የኋላው ከሌለ የለም የፊቱ ….. አይደል ያለው ቴዲ አፍሮ በዘፈኑ፡፡ እኛም ቀደምቶቻችንን እናስብ፤ እነሱንም እንጠይቅ፣ እንመርምር ብዙ ቁምነገሮችንም እናገኛለንና…….

Thursday, April 27, 2017

ሰዎች ትዳር ለምን ይፈራሉ….. ?

  
   “... ትዳር ማለት ችግርን ወይም ተግዳሮትን ለሁለት የሚያካፍል፣ ደስታ እና ስኬታችንን ደግሞ በሁለት የሚያበዛ ወዳጅ ማግኘት ማለት ነው፡፡...” ምንም እንኳን በጋብቻ መልካምነት ላይ ብዙዎች ቢስማሙም ጥቂት የማይባሉ ሰዎች በግል ህይወታቸው ከተለማመዱት፣ በአካባቢያቸው ካዩት እና ከሰሙት ነገሮች በመነሳት ስለ ጋብቻ አሉታዊ የሆነ አስተሳሰብን ሊያራምዱ ይችላሉ የሚሉት ባለሙያው የሰዎች ድርጊት በአብዛኛው የሚወሰነው በአእምሮአቸው ውስጥ ባለው አስተሳሰብ በመሆኑ ሰዎች የጋብቻን መልካምነት እንዳይረዱ ብሎም የተሳሳተ አመለካከት እንዲኖራቸው ምክንያት የሚሆኑ አስተሳሰቦች ወይም ልምምዶች በርካታ እንደሆኑም ጨምረው ይጠቅሳሉ፡፡
 


   ሁሉም ሰው ጋብቻን አይፈራም፡፡ ነገር ግን ጋብቻን የማይፈልጉ እና ሀላፊነት ወዳለበት ህብረት ለመግባት የሚፈሩ ሰዎች ይኖራሉ፡፡ እንግዲህ ይህ ፍርሀት ወይም አሉታዊ የሆነ አመለካከት የእራሱ የሆነ መነሻ ምክንያት ይኖረዋል፡፡ የሁሉም ምክንያት ግን ተመሳሳይ ላይሆን ይችላል፡፡  እነዚህ ምክንያቶች እጅግ በርካታ እና የተለያዩ ቢሆኑም የቤተሰብ የኋላ ታሪክ አንዱ እና ግንባር ቀደም ከሚባሉት ውስጥ ሊጠቀስ የሚችል ነው፡፡ ሰዎች በቤተሰቦቻቸው የትዳር ህይወት ውስጥ ከሚያዩት ነገር በመነሳት ስለጋብቻ መልካም ወይም መጥፎ አመለካከት ሊኖራቸው ይችላል፡፡


   ጋብቻ የተጋቢዎች የመጨረሻ ግብ ሳይሆን የጥምረት ጉዞ መጀመሪያ ነው፡፡ ይህ ጉዞ ተጋቢዎች የብቻቸው የሚያደርጉት ሳይሆን በጥምረት የሚያደርጉት የሕይወት ዘመን ጉዞ ነው፡፡ በዚህ ጉዞ ውስጥ ሁለቱም እያደጉና እየጎለመሱ ይሄዳሉ፡፡ ከስህተታቸው እየተማሩና አንዱ ለሌላው ያለው ፍቅር እየጎለበተ የሚሄድበት ጉዞ ነው፡፡ ይህ ጉዞ ረዥም መንገድ ስለሆነ ብዙ አስደሳች እንዲሁም አሳዛኝ ነገሮች ያጋጥማሉ፡፡ በዚህ ጉዞ ፈቃደኝነታቸው ካለ በውጣ ውረዶች ውስጥ አንድነታቸውን ጠብቀው ደስታውንና ሐዘኑን እየተካፈሉ መሄድ ይችላሉ፡፡

    ላገባችሁም ሆነ በቅርቡ ወደ ትዳሩ አለም ለምትገቡ መልካም ትዳር ተመኝተናል!!!