Thursday, January 7, 2016

የአዲስ አበባ ስታዲየምን ለመገንባት ስምምነት ተካሄደ

 ዘመናዊ እና ግዙፉ የአዲስ አበባ ስታዲየም ለመገንባት በኢትዮጵያ ወጣቶች እና ስፖርት ሚኒስቴር እና በቻይናው ስቴት ኮንስትራክሽን ድርጅት መካከል  በሸራተን አዲስ ስምምነት ተካሄደ፡፡ ስታዲዮሙ የዓለም ዋንጫ እና ኦሎምፒክ ደረጃን ያሟላ ሆኖ ይገነባል ተብሏል፡፡


    በስምምነቱ መሰረት ግንባታው በሁለት ምዕራፍ የሚካሄድ ሲሆን 900 ቀናት ይፈጃል፡፡ የወጣቶች እና ስፖርት ሚኒስትር አቶ ሬድዋን ሁሴን እንዲሁም የቻይናው ስቴት ኮንስትራክሽን ድርጅት ጀኔራል ማናጀር ሚስተር ሶንግ የስምምነት ፊርማቸውን አስቀምጠዋል፡፡ ከስምምነቱ በኋላ አቶ ሬድዋን ሁሴን የሀገራችንን ዕድገት አመላካች የሆነው ይህ ስታዲዮም  ግንባታው እስከሚጠናቀቅ ድረስ መንግስት ሙሉ ድጋፍ ያደርጋል ብለዋል፡፡

  ስታዲዮሙ በመጀመሪያው ምዕራፍ ብቻ 2 ነጥብ 47 ቢሊዮን ብር እንደሚፈጅ ሚኒስትሩ አቶ  ሬድዋን ሁሴን  ገልፀዋል፡፡ በግንባታው ወቅት የአገር ውስጥ የግንባታ ድርጅቶች እና 2ሺህ የሚሆኑ ዜጎች የስራ ዕድል እንደሚያገኙበትም አቶ ሬድዋን አብራርተዋል፡፡ የቻይና ስቴት ኮንስትራክሽን ድርጅት ማናጀር ሚስተር ሶንግ በበኩላቸው በአዲስ አበባ ጥራት ያለው ስታዲዮም በመገንባት ስማችንን የበለጠ እንገነባለን ብለዋል፡፡


   ስታዲዮም ዓለም የደረሰበትን የቴክኖሎጅ ግብዓት እንደሚጠቀም በመግለጫው ታውቋል፡፡ የኮንስትራክሽን ድርጅቱ የአፍሪካ ህብረት አዲሱን ህንጻ ጨምሮ በዓለም ላይ ታላላቅ ግንባታዎችን በመስራት ስም ያተረፈ መሆኑ ተገልጿል፡፡ ስታዲዮሙ 60 ሺህ ተመልካች እንደሚይዝ ታስቦ ቢሰራም የመያዝ አቅሙ የማደግ እድል እንዳለው ተገልጿል፡፡ 2ሺህ የሚሆኑ የክብር እንግዶችን /ቪአይ / እንዲይዝ ሆኖም ተቀርጿል፡፡

   በስታዲዮሙ ዙሪያ 60ሺህ ሜትር ስኩየር ቦታም ለሱቆች ግልጋሎት ታስቦ እንደሚሰራ ተመልክቷል፡፡ ስታዲዮሙ 10ሺህ መኪናዎችንም በዙሪያው እንደሚያስጠልል የስታዲዮሙ የዲዛይንን ስራ የሰራው ኤም ኤች ኢንጅነሪግ አብራርቷል፡፡

                                                    ምንጭ፡- ኢ.ብ.ኮ