Tuesday, December 24, 2013

ድምፃዊ ሚካያ በሀይሉ አረፈች


   ሸማመተውበሚለው የሙዚቃ አልበሟ የምትታወቀው ድምፃዊት ሚካያ በሀይሉ ከዚህ ዓለም በሞት ተለይታለች።
 ከባለፈው መስከረም ጀምሮ  በገጠማት የደም ስር መቆጣት የህክምና ክትትል ስታደርግ የቆየችው አርቲስት ሚካያ በሀይሉ ታህሳስ 15 ቀን  ምሽት 4 ሰአት አካባቢ በተወለደች በ36 አመቷ በጥቁር አንበሳ ሆስፒታል በድንገት ህይወቷ አልፏል፡፡

 ከእናቷ ከወይዘሮ ሙሉ እመቤት ፀጋዬ እና ከአባቷ አቶ በሀይሉ ገለታ ግንቦት 22 ቀን 1969 ዓ.ም አዲስ አበባ ቄራ አካባቢ ተወልዳ ያደገችው ሚካያ፣ የመጀመሪያ ደረጃ  ትምህርቷን በቤተልሄም 1ኛ ደረጃ የህዝብ ት/ቤት የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቷን ደግሞ በአብዮት ቅርስ ት/ቤት ተከታትላለች፡፡ 

 በ1994 መጀመሪያ አካባቢ ድንገት በኢቲቪ የአለቤ ሾው ቀርባ ስታዜም የተመለከቷት የሙዚቃ አቀናባሪ አልያስ መልካ እና ድምፃዊ ሚካኤል በላይነህ ወዲያው የአብረን እንስራ ጥያቄ አቀረቡላት፡፡

ከዚያም በኤልያስ መልካ  ፕሮዲውሰርነት "ሸማመተው" አልበሟን በ1999 አሳተሙት፡፡ በዚህ አልበም ውስጥ በሚገኘው "ደለለኝ" የሙዚቃ ስራዋም በ2000 በናይጀሪያ በተካሄደው የኮራ የሙዚቃ ውድድር በመሳተፍ ከምርጥ አስሮች ውስጥ መግባት ችላ ነበር፡፡ ሸማመተውከሚለው አልበሟ በተጨማሪም ሌሎች  ነጠላ ዜማዎች ያሏት ሲሆን፥ ግጥምና  ዜማም  ትደርሳለች።


ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲም በኢትዮጵያ ቋንቋዎችና ስነ ፅሁፍ የመጀመሪያ ድግሪዋን አግኝታለች፡፡ ሚካያ ከሙዚቃ ስራዋ ውጭ በመምህርነት በተለያዩ ትምህርት ቤቶች የሰራች ሲሆን በአሁኑ ሰአትም ሁለተኛ ድግሪዋን በመከታተል ላይ እያለች ነው ህይወቷ ያለፈው ፡፡    

 አርቲስቷ በአሁኑ ሰአትም  "ሚካያ አርት ወርክስ" የተሰኘ ድርጅት አቋቁማ ለሀገሪቱ ኪነ ጥበብ  መጎልበት የድርሻዋን እያበረከተች ነበር፡፡ አርቲስት ሚካያ በሀይሉ  የአንዲት ሴት ልጅ እናትም ነበረች፡፡ በ36 አመቷ ህይወቷ ያለፈው ድምፃዊት ሚካያ በሀይሉ  ወዳጅ ዘመዶቿና አድናቂዎቿ በተገኙበት በለቡ ገብርኤል ቤተክርስቲያን ታህሳስ 16 ፣2006 የቀብር ስነ ስርዓቷ ተፈፅሟ፡፡

  ለወዳጅ ዘመዶቿ ፣ ለቤተሰቦቿ ለሙዚቃ  አፍቃሪዎቿ  መፅናናትን ተመኝተናል።


No comments:

Post a Comment