Wednesday, May 15, 2013


            የመኖሪያ ቤት ፈላጊዎች የመመዝገቢያ ጊዜ ይፋ ተደረገ


     የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ለአራት ዓይነት የመኖርያ ቤቶች ግንባታ ፈላጊዎች የምዝገባ ጊዜ ይፋ አደረገ፡፡ አስተዳደሩ በተለይ በሦስት ፕሮግራሞች የመኖርያ ቤት ዋጋ ላይ ክለሳ አድርጓል፡፡

     የቤት ግንባታ ፕሮግራሞቹ 10/90፣ 20/80፣ 40/60 እና የመኖርያ ቤት የኅብረት ሥራ ማኅበራት ናቸው፡፡ 20/80 በመባል የሚጠራው የቤት ፕሮግራም ቀደም ሲል ሲካሄድ የቆየው የኮንዶሚኒየም ቤቶች ፕሮግራም ነው፡፡ በዚህ ፕሮግራም ተጠቃሚ ለመሆን በ1997 ዓ.ም. ከተመዘገቡት 453 ሺሕ ሰዎች መካከል መኖርያ ቤቱ ያልደረሳቸው ሰዎች በድጋሚ እንዲመዘገቡ ይደረጋል፡፡

      በዚህ የ20/80 ቤቶች ፕሮግራም ተጠቃሚ ለመሆን የሚፈልጉ ነዋሪዎች በየወረዳቸው ከሰኔ 3 ቀን 2005 ጀምሮ እስከ ሰኔ 21 ቀን 2005 ዓ.ም. ድረስ ምዝገባው ይካሄዳል፡፡ ይህንን መኖርያ ቤት ለማግኘትም ነባር ተመዝጋቢዎች በድጋሚ ሲመዘገቡ ለባለሦስት መኝታ ቤት 685 ብር፣ ለባለሁለት መኝታ ቤት 561 ብር፣ ለባለአንድ መኝታ ቤት 274 ብር እና ለስቱዲዮ 151 ብር መቆጠብ ይጠበቅባቸዋል፡፡  አዲስ ተመዝጋቢዎች የ20/80 ተመዝጋቢዎች ለባለሦስት መኝታ ቤት 489 ብር፣ ለባለ ሁለት መኝታ ቤት 401 ብር፣ ለባለ አንድ መኝታ ቤት 196 ብር መቆጠብ ይጠበቅባቸዋል፡፡

    በገንዘብ መጠን ላይ ለውጡ የተደረገው ነባሮቹ የሚቆጥቡት ለአምስት ዓመት በመሆኑና አዲስ ተመዝጋቢዎቹ የሚቆጥቡት ለሰባት ዓመታት በመሆኑ ነው ሲሉ፣ የአዲስ አበባ ከተማ ኮንስትራክሽንና ቤቶች ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ ጌታቸው ኃይለ ማርያም ገልጸዋል፡፡

    ለ10/90 ቤቶች ፕሮግራም እንዲሁ ምዝገባ የሚካሄደው ከሰኔ 3 እስከ ሰኔ 21 ቀን 2005 ዓ.ም. ነው፡፡ ይህ ፕሮግራም ዝቅተኛ ገቢ ላላቸው የኅብረተሰብ ክፍሎች የቀረበ ነው፡፡ በዚህ ፕሮግራም ተጠቃሚ ለመሆን አንድ ቤት ፈላጊ 187 ብር በወር መቆጠብ ይጠበቅበታል፡፡ እዚህ ፕሮግራም ውስጥ ለመታቀፍ ተመዝጋቢው ድህነቱን የሚገልጹ ማስረጃዎችን ከተገቢው አካል ማቅረብ እንደሚጠበቅበት ተገልጿል፡፡

      ከእነዚህ ሁለት ፕሮግራሞች ውጪ ያሉት የመኖርያ ቤት ፕሮግራሞች ዝቅተኛ ወይም መካከለኛ ገቢ ያለውን የኅብረተሰብ ክፍል የሚመለከቱ አይደሉም፡፡ ከንቲባ ኩማ ደመቅሳ ባለፈው ዓርብ ግንቦት 2 ቀን 2005 ዓ.ም. በአስተዳደሩ ካቢኔ አዳራሽ ጋዜጣዊ መግለጫ በሰጡበት ወቅት እንዳስረዱት፣ በ40/60 እና በመኖርያ ቤት ኅብረት ሥራ ማኅበራት በኩል የሚካሄዱት ፕሮግራሞች የተሻለ ገቢ ላለው የኅብረተሰብ ክፍል ነው፡፡

      የ40/60 ቤቶችን ተጠቃሚ ለመሆን ለባለአንድ ክፍል 857 ብር፣ ለባለሁለት መኝታ ቤት 1,337 ብር፣ ለባለሦስት መኝታ ቤት 2,133 ብር መቆጠብ የግድ ነው፡፡ በከተማው ውስጥ በመንግሥትና በግል ድርጅቶች ወይም በአነስተኛ ንግድ የተሰማራ ሰው፣ ከኑሮው ተርፎት ይህን ገንዘብ መቆጠብ እንደማይችል የብዙዎች እምነት ነው፡፡ ለመኖርያ ቤት ኅብረት ሥራ ማኅበርም እንዲሁ በአዲሱ ደንብ መሠረት የሚጠየቀው ክፍያ መቶ በመቶ በመሆኑ ዝቅተኛና መካከለኛ ገቢ ያላቸው የኅብረተሰብ ክፍሎች ከጨዋታ ውጪ መሆናቸው ተረጋግጧል እየተባለ ይነገራል፡፡

    በ40/60 ቤቶች ተጠቃሚ ለመሆን ከነሐሴ 5 ቀን እስከ ነሐሴ 17 ቀን 2005 ዓ.ም. ድረስ እንዲሁም የመኖርያ ቤት ኅብረት ሥራ ማኅበራት ከሐምሌ 15 እስከ ሐምሌ 30 ቀን 2005 ዓ.ም. ድረስ ምዝገባ ይካሄዳል፡፡

    ለመኖርያ ቤት ኅብረት ሥራ የሚደራጁ ሰዎች በኅብረት ሆነው አቅማቸውን አቀናጅተው የቤት ባለቤት የመሆን ፍላጎት ኖሮአቸው ነው፡፡ ነገር ግን መቶ በመቶ ክፍያ መጠየቁ ቤት የመሥራት ህልም የነበራቸውን ሰዎች እንዲደናቀፉ አያደርግም ወይ? የሚል ጥያቄ ከሪፖርተር የቀረበላቸው ከንቲባ ኩማ ሲመልሱ መሬት በሊዝ በጨረታ ወስደው፣ ከሪል ስቴት አልሚዎች ቤት በመግዛት ተጠቃሚ መሆን የሚችሉት የተሻለ ገቢ ያላቸው ነዋሪዎች ናቸው፡፡ በተጨማሪም 40/60 እና ማኅበራት አሁንም የተሻለ ገቢ ላላቸው የቀረቡ ናቸው ብለዋል፡፡

‹‹መጠየቅ ካለበት መጠየቅ ያለበት ጥያቄ ለሁሉም የኅብረተሰብ ክፍል እንደ አቅሙ አማራጭ ተሰጥቶታል ወይስ አልተሰጠም የሚለው ነው፡፡ በእኔ እምነት ዝቅተኛም ሆነ መካከለኛ ገቢ ላለው አማራጭ ተሰጥቶታል፡፡ ዝቅተኛና መካከለኛ ገቢ ላላቸው ነዋሪዎች የተያዙትን 10/90 እና 20/80 ቤት ልማት ፕሮግራሞች መንግሥት ይደጉማል፡፡ 40/60 እና ማኅበራትን ግን አቅሙ አለን እንችላለን የሚሉ ክፍሎች የሚገቡበት ነው፤›› ሲሉ ከንቲባ ኩማ ገልጸዋል፡፡

    ከንቲባ ኩማ በመግለጫቸው እንዳስረዱት፣ ሕገወጦችን ለመከታተል ቴክኖሎጂ ጥቅም ላይ ይውላል፡፡ ኅብረተሰቡም ቤት እያላቸው በድጋሚ ለመመዝገብ የሚጥሩትን በንቃት እንዲከታተል ጠይቀው፣ ሆን ብሎ አቅዶ የማይገባውን ጥቅም ለማግኘት በሚመክር ማንኛውም ሰው ላይ ጠንከር ያለ ዕርምጃ እንደሚወሰድበት ከንቲባው አስጠንቅቀዋል፡፡

No comments:

Post a Comment