Saturday, October 1, 2022

እንኳን ለኢሬቻ በዓል በሰላም አደረሳችሁ … !!!


የዓመቱ መስከረም ወር ላይ የኢሬቻ በዓል በደመቀ ስነ ስርዓት ይከበራል፡፡ ይህ ክብረ በዓል በኦሮሚያ ክልላዊ አስተዳደር ትኩረት ከተሰጣቸው ህዝባዊ በዓላት አንዱ ሲሆን በዓሉ የምስጋና፣ የሰላም፣ ፍቅርና አንድነት መገለጫ ነው። የኢሬቻ በዓል አንዱ የገዳ ስርዓት መገለጫ ሆኖም በተባበሩት መንግስታት የትምህርት፣ የሳይንስና የባህል ድርጅት (ዩኔስኮ) በማይዳደስ ቅርስነት ተመዝግቧል፡፡

ኢሬቻ የኦሮሞ ህዝብ በህብረት ወደ ተራራ እና መልካ ወይም በወንዝ ዳር ወርዶ ፈጣሪውን የሚያመሰግንበት ስርዓት/በዓል ነው፡፡ ይህ በዓል በተለያዩ ቦታዎች ቢካሄዱም ዋና ዋናዎ በሁለት ይከፈላሉ፡፡ እነርሱም “ኢሬቻ ቱሉ” እና “ኢሬቻ መልካ” በመባል ይታወቃሉ፡፡ 

የበጋ ወቅት አልፎ በበልግ ወቅት ላይ የሚከበረው የኢሬቻ በዓል “ኢሬቻ ቱሉ” ይባላል፡፡ ይህም በበጋ ወቅት ሰው እና እንሰሳት በድርቅ ሲጠቁ ወይም ሲጎዱ ወደ ተራራ በመውጣት የበልግ ዝናብ እንዲዘንብላቸው ፈጣሪን የሚለማመኑበት ስርዓት ነው፡፡

ክረምት አልፎ በፀደይ መግቢያ ወቅት ላይ በቢሾፍቱ ከተማ በድምቀት የሚከበረው ደግሞ “ኢሬቻ መልካ” በዓል ይባላል፡፡ ይህ በዓል ከክረምት ወደ በጋ በሰላም ስላሸጋገራቸው እርጥብ ሳር እና አደይ አበባ በመያዝ ወንዝ ዳር ወጥተው ፈጣሪን የሚያመሰግኑበት ስርዓት ነው፡፡ በዚህ በዓል ላይም ከሀገር ውስጥ እና ከውጭ በርካታ ሰዎች ይታደማሉ፡፡

No comments:

Post a Comment