Thursday, February 13, 2014

ተፅዕኖ ፈጣሪው ቀኝ ጌታ ዮፍታሄ ንጉሴ

  የአማርኛን ስነ ጽሁፍ ካሳደጉት ታላላቅ ኢትዮጵያዊያን መካከል ባለቅኔው ዮፍታሄ ንጉሴ ይጠቀሳሉ፡፡ ዮፍታሄ ንጉሴ የተወለዱት በጎጃም ክፍለ ሀገር በደብረ ኤልያስ በ1885 ዓ.ም ሲሆን በደብረ ኤልያስ ደብር የጥንቱን የኢትዮጵያ ቤተክርስትያን ትምህርት በሚገባ ተምረዋል፡፡

    ዮፍታሄ በልጅነታቸው የዜማ ትምህርት ያስተማሯቸው መሪጌታ አደላ ንጉሴ ሲሆኑ የቅኔን ትምህርት ያስተማሯቸው የኔታ ገብረስላሴ ነበሩ፡፡ የኔታ ገብረስላሴ በደብረ ኤልያስ ደብር ታዋቂ የቅኔ መምህር ሲሆኑ ሁለተኛው ኢትዮጵያዊ ፓትርያርክ አቡነ ቴዎፍሎስን ቅኔ እንዳስተማሯቸው በታሪክ ይታወቃል፡፡ ደብረ ኤልያስ ደብር የ”ፍቅር እስከ መቃብር” ደራሲ ሃዲስ አለማየው የተማሩበት ደብር ነው፡፡

      አቶ ሙሉጌታ ስዩም በ1964 ዓ.ም በቀዳማዊ ኃይለ ስላሴ ዩኒቨርስቲ በመመረቂያ ጽሁፉ ላይ እንደገለፀው፤ በደብረ ኤልያስ ደብር የነበሩ መምህራን “ማህበረ ኤልያስ” በሚል ስም እግረ ኤልያስ ብለው ደቀመዛሙርት ተማሪዎቻቸውን ይጠራሉ፡፡ በዮፍታሄ የዜማና የቅኔ ችሎታ መምህራኖቹ ከመደነቃቸው የተነሳ ለአምስት ተከታታይ ዓመታት እግረ ኤልያስ የሚለውን ምርጥ ስም ሰጥተውታል፡፡ ለዮፍታሔ ገና በልጅነቱ የአባቶችን ማእረግ ቀኝ ጌታ ሾመውታል፡፡

      ቀኝ ጌታ ዮፍታሄ በ1911 ዓ.ም አዲስ አበባ እንደመጡ፣ ወዲያውኑ በአቦ ደብር በአጋፋሪነት፤ በመቀጠልም በደብረ አለቅነት ተሹመዋል፡፡ ከቤተክርስቲያን አገልጋይነት ቀጥለው በሊጋባ ወዳጆ ጽ/ቤት የጽሕፈት ስራ እየሰሩ ለተወሰነ አመት ቆዩ፡፡ በኋላም ዶክተር አምሳሉ አክሊሉ ባልታተመ ጥናታቸው እንደገለፁት፤ ቀኝ ጌታ ዮፍታሄ በዳግማዊ ሚኒሊክ ትምህርት ቤት በአስተማሪነት ተቀጥረው ልዩ ልዩ መዝሙሮችን እየደረሱ ማስተማር ጀመሩ፡፡ በቀድሞ ጊዜ ዳግማዊ ምኒሊክ ትምህርት ቤት ያስተምሩ የነበሩ መምህራን በየጊዜው በትምህርት ቤቱ ቅጥር ጊቢ ልዩ ልዩ ትያትሮች እየደረሱ ለተማሪዎች ያሳዩ ነበር፡፡ ይህም ሁኔታ የመዝሙር መምህሩን ዮፍታሄን ከቲያትር ጋር አስተዋወቃቸው፡፡ ዮፍታሄም አዳዲስ ትያትሮችን በተለየ አቅጣጫ መድረስ ጀመሩ፡፡

         ቀኝ ጌታ ዮፍታሄ ንጉሴ ከደረሷቸው በርከት ያሉ ትያትሮች መካከል “አፋጀሽኝ”፣ “የሆድ አምላኩ ቅጣት”፣ “የደንቆሮዎች ትያትር”፣ “እርበተ ፀሐይ” እና “ጎበዝ አየን” ይጠቀሳሉ፡፡
የትያትር መምህሩና ተዋናዩ ተስፋዬ ገሰሰ በጥናታዊ ጽሁፋቸው እንደገለፁት፤ ዮፍታሄ ንጉሴ በድርሰት ችሎታቸው ብዙ የተመሰገኑ እና ከግርማዊ ቀዳማዊ ኃይለ ስላሴ ብዙ ሽልማቶችን ያገኙ ነበር፡፡ ከጦርነቱ በፊት በመናገሻ ቅጥር ጊቢ ውስጥ የጊዮርጊስ ትምህርት ቤት ሲባል ከነበረው ቀበና ከሚገኘው ሊሴ ኃይለ ስላሴ ትምህርት ቤት፣ ከተፈሪ መኮንንና ከዳግማዊ ምኒሊክ ትምህርት ቤቶች ተማሪዎች ተመርጠው ልዩ ልዩ ትያትሮችን እያዘጋጁ ያበረክቱ ነበር፡፡ አቶ ሙሉጌታ ስዩም በጥናቱ እንደጠቆመው፣ አንድ ጊዜ ጃንሆይ ዮፍታሄን ትያትር በመመልከት ላይ እያሉ በጣም ከመደሰታቸው የተነሳ ከልዑል አልጋ ወራሽ አንገት ወርቅ አውልቀው፤ ለዮፍታሄ አድርገውላቸዋል፡፡


       ቀኝ ጌታ ዮፍታሄ በርካታ የመድረክ ድርሰቶች አዘጋጅተው አሳይተዋል፡፡ ነገር ግን ድርሰቶቹ ባለመታተማቸው የተገኙት በጣም ጥቂቶች ናቸው፡፡ “ጎበዝ አየን” የሚባለው ድርሰታቸው የህትመት ብርሀን አይቷል፡፡ ለመድረክ ከቀረቡት ውስጥ የተመልካችን አድናቆት ያተረፈው “አፋጀሽኝ” የተባለው ድርሰታቸው ነው፡፡ ይሄን ድርሰት ዮፍታሄ የጀመሩት ከጣሊያን ወረራ በፊት ሲሆን ድርሰቱን የፈፀሙት ከወረራው በኋላ ነው፡፡
“አፋጀሽኝ” ድርሰት ምሳሌያዊ ሲሆን በወቅቱ የነበረውን የአለም ፖለቲካዊ አዝማሚያ የሚጠቁም ከመሆኑም በላይ በድርሰቱ ውስጥ የተመሰለችው እናት ሀገር ኢትዮጵያ በሚከጅሏት ዘንድ የነበራትን የፖለቲካ ሁኔታ የሚያሳይ ነው፡፡ “አፋጀሽኝ” ዋና ጭብጡ በጣሊያንና በኢትዮጵያ የነበረውን ጦርነት የሚያመለክት ነው፡፡ ይሄም የጊዜው አንገብጋቢ ፖለቲካዊ መልእክት ነበር፡፡ ድርሰቱ የዮፍታሄን ኪናዊ ችሎታ በቅጡ የሚያንፀባርቅ እንደሆነ ይነገርለታል፡፡

     በኢትዮጵያ የድራማ ታሪክ የመድረክ ተውኔቶችን ካቀጣጠሉት ፈር ቀዳጆች መካከል በቅድሚያ የሚጠቀሱት በጅሮንድ ተክለሀዋርያትና እና ቀኝ ጌታ ዮፍታሄ ንጉሴ ናቸው፡፡ ዮፍታሄ የድራማ ሰው የነበሩትን ማቲዎስ በቀለን አስተምረዋል፡፡ “ሙናዬ ሙናዬ” የተሰኘው ዘፈን የዮፍታሄ ግጥም ሲሆን ዜማው በአገር ፍቅር ማህበር ይገኛል፡፡

        ቀኝ ጌታ ዮፍታሄ ከተውኔት ድርሰታቸው በተጨማሪ መዝሙሮችንና ግጥሞችን ደርሰዋል፡፡ የኢትዮጵያ አንድነትና የህብረት መዝሙር የሚገልጽልንን የኢትዮጵያ ህዝብ መዝሙር (ተፈሪ ማርሽ)፣ ወላድ ኢትዮጵያ፣ አጥንቱን ልልቀመው፣ ድንግል አገሬ ሆይ የሚባሉ መዝሙሮችን ደርሰዋል፡፡ አጥንቱን ልልቀመው የሚለው ግጥም አርበኞቹን የዶጋሊውን አሉላ አባ ነጋ እና ራስ ጎበናን በማነፃፀር የገጠሙት ግጥም ሲሆን ድንግል ሀገሬ ሆይ የተሰኘውን ድርሰት የፃፉት በስደት ኢሊባቡር ሆነው በ1929 ዓ.ም ነበር፡፡ ይህ መዝሙር ከመጀመሪያ ረድፍ ከሚጠቀሱት ስራዎቻቸው ቀዳሚው ነው፡፡

ድንግል ሀገሩ ሆይ ጥንተ ተደንግሎ
ጥንተ ተደንግሎ ጥንተ ተደንግሎ
ህፃናቱ ታርደው ያንቺም ልብ ቆስሎ
ልጅሽ ተሰደደ አንቺን ተከትሎ
የህፃናቱ ደም አዘክሪ ኩሎ፡፡
አዝማች፤ አስጨነቀኝ ስደትሽ
እመቤቴ ተመለሺ እመቤቴ ተመለሺ

ይሄ ግጥም ዮፍታሄ ንጉሴ ህዝቡ በፋሺስት ወረራ የደረሰበትን ስደት የገለፁበት ስንኝ ነው፡፡ ቅድስት ድንግል ማርያም ከእስራኤል ወደ ግብጽ ያደረገችውን ስደት እና በኤሮድስ ህፃናት መቀላታቸውን ከኢትዮጵያ ስደት ጋር ያነፃፀሩበት ግጥምም ነው፡፡ የቀኝ ጌታ ዮፍታሄ ግጥሞች ትንቢታዊ ሲሆኑ በአንድ ስንኝ የሚጽፉት ግጥም ተሰጦአቸው የላቀ መሆኑን ያሳየናል፡
የሰማይ አሞራ ልጠይቅሽ ወሬ፣
ተቃጥሏል መሰለኝ ሸተተኝ አገሬ፡፡
በጣሊያን ወረራ ወቅት ለፋሺስት ያገለገሉ ባንዳዎችን በማስመልከት የገጠሙት ምፀታዊ ግጥም እንዲህ ይላል፡-
ለጌሾ ወቀጣ ማንም ሰው አልመጣ
ለመጠጡ ጊዜ ከየጐሬው ወጣ፡፡
ቀኝ ጌታ ዮፍታሄ በተለይ የግእዙን ቅኔ መንገድ ለአማርኛ ለማውረስና የግእዙን ኪነታዊ ጠባይ አማርኛ እንዲኖረው ለማድረግ ታላቅ አስተዋጽኦ እንዳደረጉ ከግጥሞቻቸው እንረዳለን፡፡ ዶክተር አምሳሉ አክሊሉ በጥናታቸው እንደፃፉት፤ ይህም በግእዝ ቋንቋ ያላቸውን እውቀትና ብስለት የሚያረጋግጥ ነው፡፡ ከሳቸው በፊት እንዲህ ያለ ሙከራ ያደረገ ሰው መኖሩም ያጠራጥራል፡፡ የተፃፈም ነገር አላጋጠመንም፡፡ ግን ኋላ ላይ ይህን መንገድ ብዙዎቹ ባለቅኔዎች ተከትለው ሰርተውበታል፡፡

ቆሞ የስኳር ጠጅ
ውስተ ደብረ ማሕው ልብነ ሀገሩ ስቃይ ወተድላ፤
ወደይነ በበተራሆሙ አረቄ ወጠላ፤
በውስተ በርሜል ልብነ ምስትግቡአ በቀለ አተላ፤
እሳተ አራዳ ኮኛክ እሷው ተቃጥላ፤
አወያይታ ለባቢሎን ገላ፡፡
ግማሽ አማርኛ ግማሽ ግእዝ አድርገው የሚያዘጋጇቸው ማህሌተ ገንቦ የተባሉት መዝሙሮቻቸው አድማጭ የሚስቡ ነበሩ፡፡ በተጨማሪም በቀኝ ጌታ ዮፍታሄ ንጉሴ ድርሰት ላይ ጐልቶ እንደታየው የዮፍታሄ አፃፃፍ ከቀበሌኛ ወይም ከአገራቸው ከጐጃም አማርኛ የነፃ ነው፡፡ ለማንም አማርኛ ተናጋሪ ሳይቸግር ይገባል፡፡ የግእዝ ብስለታቸው ለዚህ አፃፃፍ ከፍተኛ አስተዋጽኦ አድርጓል፡፡
ማሽላና ስንዴ በአንድ አብረን ስንቆላ፤
እያረረ ሳቀ የባህር ማሽላ፡፡
ከሰል የሚሆኑ ብዙ እንጨቶች ሳሉ፤
ዝግባ ለምን ይሆን ይቆረጥ የሚሉ፡፡
የቀኝ ጌታ ዮፍታሄ አፃፃፍ ለተከታዮቹ ደራሲያን ምሳሌ ስለነበር አንጋፋነታቸው ታላቅ ዋጋ የሚሰጠው ነው፡፡ ዮፍታሄ በግእዝ ቅኔ የበሰሉ ስለነበሩ አማርኛ የስነ ጽሑፍ ቋንቋ እንዲሆንና እንዲያድግ የላቀ አስተዋፅኦ አበርክተዋል፡፡

     የአማርኛ ስነ ጽሑፍን ለማሳደግ በተውኔት፣ በግጥም፣ በዘፈን እና በመዝሙር ባደረጉት ጥረት በኢትዮጵያ ስነ ጽሑፍ ታሪክ ውስጥ ከፍተኛ የክብር ቦታ አላቸው፡፡ ባለ ቅኔው ዮፍታሄ ከጣሊያን ወረራ በኋላ እስከ 1941 ዓ.ም የህግ መወሰኛ ምክር ቤት ምክትል ፕሬዝዳንት ሆነው ሲሰሩ ቆይተው በ1942 ዓ.ም አርፈዋል፡፡ የባለ ቅኔው ዮፍታሄ ስራዎች ግን ተጽእኖ ፈጥረው ከትውልድ ወደ ትውልድ ይሸጋገራሉ፡፡

የደራሲው ሥራዎች
1. እኔ አይኔን ሰው አማረው(ግጥምና ቅኔ)
2. ዐጥንቱን ልልቀመው፥ መቃብር ቆፍሬ(ግጥምና ቅኔ)
3. ወላድ ኢትዮጵያ ለልጆቿ ብላ(ግጥምና ቅኔ)
4. ጎበዛዝቴ ሆይ ወይ ቆነጃጅቴ(ግጥምና ቅኔ)
5. ሰውን ሰው ቢወደው አይኾንም እንደራስ(ግጥምና ቅኔ)
6. አወይ ጥርሴ ሞኙ ዘወትር ይሥቃል(ግጥምና ቅኔ)
7. ሙናዬ(ግጥምና ቅኔ)
8. የኛማ ሙሽራ(ግጥምና ቅኔ)
9. አንተ ባለጐዛ(ግጥምና ቅኔ)
10. ድንግል አገሬ ሆይ ጥንተ ተደንግሎ(ግጥምና ቅኔ)
11. የእኛማ ሀገር(ግጥምና ቅኔ)
12. ሰለኢትዮጵያ(ግጥምና ቅኔ)
13. ትንሽ ዐማርኛ(ግጥምና ቅኔ)
14. የሥነ- በዓል መዝሙር...እንደመፋቂያ(ግጥምና ቅኔ)
15. ጉሰማዬ(ግጥምና ቅኔ)
16. ተነሱ ታጠቁ(ግጥምና ቅኔ)
17. አብሪ ብርሃንሽን(ግጥምና ቅኔ)
18. የባሕር ዳር ጨፌ(ግጥምና ቅኔ)
19. ባገር ገዳይ፥ቋጥኝ ድንጋይ...(ግጥምና ቅኔ)
20. በለስ ለመለመች(ግጥምና ቅኔ)
21. እስክትመጣ ድረስ...(ግጥምና ቅኔ)
22. ጎሐ ጽባሕ(ግጥምና ቅኔ)
23. አገሬ ኢትዮጵያ...ሞኝ ነሽ ተላላ...(ግጥምና ቅኔ)
24. የኢትዮጵያ ሕዝብ መዝሙር(ግጥምና ቅኔ)
25. የሰንደቅ ዓላማ መዝሙር ደሙን:ያፈሰሰ፥ተጣማጅ: አርበኛ(ግጥምና ቅኔ)
26. አፋጀሽኝ(ተውኔት)
27. እያዩ ማዘን(ተውኔት)
28. ስለአያ ከምሱና ስለአያ እነባንት ይቀጡ(ተውኔት)
29. እለቄጥሩ /ጎበዝ አየን / (ተውኔት)
30. ጥቅም ያለበት ጨዋታ(ተውኔት)
31. የሕዝብ ፀፀት፥የእመት በልዩ ጉዳት(ተውኔት)
32. የሆድ አምላኩ ቅጣት(ተውኔት)
33. ዕርበተ ፀሐይ(ተውኔት)
34. ምስክር(ተውኔት)
35. ያማረ ምላሽ(ተውኔት)
36. ዳዲቱራ(ተውኔት)
37. ሞሽሪት ሙሽራ(ተውኔት)
38. መሸ በከንቱ፥ ሥራ ለፈቱ(ተውኔት)
39. ጠረፍ ይጠበቅ(ተውኔት)
40. ዓለም አታላይ(ተውኔት)
41. የደንቆሮዎች ትያትር(ተውኔት)
42. ንጉሡና ዘውድ(ተውኔት)

    " ኮከብ እምኮከብ ይኄይስ ክብሩ" የሚል የኖረ የግእዝ አባባል አለ:: አንዱ ኮከብ በብርሀኑ፤ በግዘፉ፤ መጠቅላላ ተፈጥሮው ከሌላው ኮከብ ይበልጣል:: እኔን የሚያስገርመኝ ይኽ አይደለም:: እንዳንድ ከዋክብት አሉ--በተለየ አጠራር ተወርዋሪ የምንላቸው:: በሌሊቱ ኅዋ ውስት ከአንዱ መአዘን ሰማይ ወደ ሌላው ተወርውረው ብልጭ ብለው ይጠፋሉ:: ይህ ሁሉ የሚሆነው በቀፅበት ነው::ያንን በጨለማው ግርማ የተዋጠውን ኅዋ በብርሃን ጎርፍ ሰንትቀው አጥለቅልቀውት ይጠፋሉ:: ተመልካችም ከመገረም በሚመነጭ ዝምታ ይዋጣል:: በኢትዮዽያም የሥነ ጽሑፍ ኅዋ ውስጥ ዮፍታሔ ንጉሤ አንድ ተወርዋሪ ኮከብ ነበር።

ብሩህ ነጸብራቁ፤
ውበቱና ድምጹ አንድነት ተሰማ
ተው አንድነት ቢበርቁ፤ የመያው
ቅለት ጠፍቶ፤ ምስጢሩን አካቶ፤
ተወርዋሪ ኮከብ በራሱ ነበልባል
በራሱ ነዲድ ተቃጥሎ የጠፋ፤
ተወርዋሪ ኮከብ በምናየው ሰማይ
ነበረ በይፋ።

አዎን፤ ነበረ። በዚያን ቅጽበት በሆነው የጽሁፍ ዘመን ዮፍታሔ፤ የኢትዮዽያን የስነጽሁፍ ኅዋ በቅኔ ፤ በግጥም ፤በመዝሙርና በተውኔት የብርሃን ጎርፍ ሰንጥቆ አጥለቅልቆት ጠፍቷል። ዛሬ የሚያሳዝነው የዚህ ተወርዋሪ ኮከብ ተጽእኖ በዘመናችን መጥፋቱ ነው።

   ስለ ዮፍታሔ ንጉሴ በሕፃንነቴ እናት አባቴ ሲያወጉ፤ ሲወያዩ፤ አንዳንዴም ሲከራከሩ እሰማ ነበርበተለይ አባቴ ከዮፍታሔ ንጉሴ ተውኔቶችና መዝሙሮች በቃሉ የሚያስታውሳቸውን ስንኞች ሲያንጎራጉር እየሰማሁ የዮፍታሔ ፍቅር በሕፃን ልቦናዬና ስሜቴ ተሳለብኝ ። ያኔ ከሰማኋቸው ትዝ የሚሉኝ "አንተ ባ...ጎራዴ ግዛ" እና "ወላድ ኢትዮዽያ ለልጆቻ ብላ እጅግ ሳይትሩባት ሳይዘሯት አብቅላ" የተባሉት መዝሙሮች ናቸው። ሁለተኛው በጣም ጠሊቅ መዝሙር ነው። ጠሊቅነቱ የተገነዘብሁት ካደግሁ በኋላ ነው። ያኔ መዝሙሩ ይመስጠኝ የነበረው በቃላቱ ጣእመ ዝማሬ ነበረ። የፊተኛውን መዝሙር ግጥሙን በሙሉ ላገኘው አልቻልሁም። የኋለኛው ግን "ብርሃንና ሰላም" ይባል በነበረው ጋዜታ በሙሉ ተጽፎ ስላገኘሁት ከዚህ ቀጥሎ ጽፌዋለሁ፤

ወላድ ኢትዮዽያ ለልጆቿብላ፤
እጅግ ሳይጥሩባት ሳይዘሯት አብቅላ፤
ስንዴውን ጠብቃ እንክርዳዱን ነቅላ፤
ስትመግበን አየን በፀሐይ አብስላ።

ምሳሌ ዘርእ አገራችን፤
ንጹሕ ዝናብ መንግሥታችን።
በመልካሙ ዘርእ ላይ እንክርዳቸ ሲዘራ፤
ታሳድገውና ከእንክርዳዱ ጋራ፤
ገለባ ሲቃጠል ገበሬ ሲያመራ፤
ታቃጥለዋልች እንክርዳዱን አብራ።
ምሳሌ ዘርእ አገራችን፤
ንጹሕ ዝናም መንግስታችን ።
አይዞህ የኛ ጌታ ነገርህን አትርሳ፤
አለስልሰህ ዝራ የስንዴውን ማሳ፤
የተዘራችው ዘርእ ፈርሳና በስብሳ ፤
ታፈራልቸ ፍሬ ሙታ ስትነሣ።
ምሳሌ ዘርእ አገራችን፤
ንጹሕ ዝናም መንግስታችን ።
በጊዜው የዘራ መልካም ዘር አትርፎ፤
ከበሮቹ ጋራ ማታ ከትላ አርፎ፤
ብርነት ታትቆ በቅን ተሰልፎ፤
በቸርነት ታጥቆ በቅን ተሰልፎ፤
ደግሞ ዘሩን ዘራ መክር አሳልፎ።
ምሳሌ ዘርእ አገራችን፤
ንጹሕ ዝናም መንግስታችን ።

   ኋላም ትምህርት ቤት ከገባው በኋላ፣ በተለይም መሁለተኛ ደረጃ በነበርሁበት ጊዜ ፣ በብላታ መርስዔ ሐዘን ስዋስው ውስጥ የዮፍታሔ ቅኔዎች፣ ግጥሞችና መዝሙሮች አልፎ አልፎ ተጠቅሰው በማግኘቴ በቃሌ አትንቼ እንደ ዳዊት እደግማቸው ነበረ። መጀመሪያ ምናቤን የመታው ፤ ስሜቴን የነካው የዮፍታሔ የቋን ቋው ኀይልና ውበት ነበር።ኋላም ስለ ቅኔም ሆነ ስለግጥም አንዳንድ ነገር ከገረጫጨፍሁ በኋላ ያን መጀመሪያ ምናቤን የመታውን፣ ስሜቴን የነካውን የቋንቋ ኀይልና ውበት መመርመር ጀመርሁ።

   የዮፍታሄ ስንኞች መቀነባበር፤ የዘይቤው ወይንም የስለምኑ መተባበርና መዋሐድ ፤ በስተቅኔውም በኩል የሰምና ወርቁነ፤ የውስተ ወይራው፤ የሰም ለበሱ ፤ የኅብሩና የምርምሩ አካሄድ እስከ ዛሬ ከተነሱት ገጣሚዎች ሁሉ ዮፍታሔን የተለየ ያደርጉታል። የዮፍታሔ ርቀቱ ፤በኪነት ሥራው ሁሉ ከሀብተ ትንቢት ጋር የተሳላው የዘይቤው ወይንም የስለምን ስልቱ ልዝብ በመሆኑ አይኮሰልም፤ ወይንም ሌላ ሊቀዳው አይችልም። ወጥነቱ የተመሠረተው በዚህ ላይ ነው። ---ንጹሕ የኪነት ወጥነት ነው።

ማስታወሻ፡-

   የቀኝ ጌታ ዮፍታሄ ንጉሤን የተወለዱበትን እና ህይወታቸው ያለፈበትን ትክክለኛ ቀን ለማወቅ አዳጋች ነው ምክንያቱም የተለያዩ የመረጃ ምንጮ የተለያየ ቀን ያስቀምጣሉና ስለዚህ የሚቀራረበውን መምረጥ ተገቢ ይሆናል፡፡

                                          ምንጭ:-            - http://www.addisadmassnews.com
                                                               - http://www.ethiosalon.com
                                                               - http://ethioliteraturepaltalk.blogspot.com
                                                              - http://www.ethioreaders.com

No comments:

Post a Comment