Monday, February 3, 2014

ሊቢያ የ2014 የቻን አፍሪካ ዋንጫ ሻምፒዮና ሆነች

   በ2014 በደቡብ አፍሪካ አዘጋጅነት ሲካሄድ በነበረው የአፍሪካ ሀገራት የቻን ዋንጫ ጥር 24/2006  ምሽት በተካሄደ የደረጃ እና የዋንጫ ጨዋታ በሊቢያ የበላይነት ተጠናቀቀ፡፡
   ሊቢያ ከ32 ዓመታት በፊት ባዘጋጀችው ውድድር ላይ በጋና 7 ለ 6 በሆነ ውጤት የተሸነፈችበትን ጨዋታ በመቀየር ወደ አሸናፊነት በተመለሰችበት የምሽቱ ጨዋታ በመደበኛው እና በጭማሬው ሰዓት ምንም ጎል ሳይቆጠር 0 ለ 0 በሆነ ውጤት በማጠናቀቃቸው ወደ ፍጹም ቅጣት ምት አምርተዋል፡፡
   በመደበኛው እና ጭማሬው የጨዋታ ሰዓት ሁለቱም ቡድኖች ጎል ለማስቆጠር ያደረጉት ጥረት ከፍተኛ ቢሆንም ሳይሳካለቸው ቀርቶ ወደ ፍጹም ቅጣት ምት ያመሩት ቡድኖቹ ሊቢያ ጋናን 4 ለ 3 በሆነ ውጤት በማሸነፍ ለመጀመሪያ ጊዜ ሻምፒዮና መሆን ችላለች፡፡
    በሀገሪቱ ፖለቲካዊ ችግር ምክንያት የሐገር ውስጥ እግር ኳስ ውድድሩ የተቋረጠባት ሊቢያ በዚህ ውድድር ላይ እዚህ ደረጃ ላይ ትደርሳለች የሚል ግምት ባይሰጣትም፤ በትላንት ምሽቱ ጨዋታ ላይም የአብዘሃኛው ግምት ለጋና ቢሆንም ሊቢያ ግን ታሪካዊ ውጤት ማስመዝገብ ችላለች፡፡
   

    በቻን የአፍሪካ ዋንጫ ውድድር ሊቢያ ሻምፒዮና መሆኗን ተከትሎ በትሪፖሊ የሀገሪቱ ዜጎቹ ደስታቸውን እየገለጹ ሲሆን መንግስትም ተጫዋቾቹ ወደ ሐገራቸው ሲመለሱ የብሔራዊ ጀግና አቀባበል እንደሚደረግላቸው አስታውቋል፡፡ በደቡብ አፍሪካ ፍሪ ስቴት ስቴዲየም በተደረገው የምሽቱ ጨዋታ የካፍ ፕሬዝዳንት ኢሳ ሃያቱን ጨምሮ በክብር እንግድነት የተገኙት የፊፋው ፕሬዝዳንት ሴብ ብላተር ለተጫዋቾች ዋንጫ እና ሜዳሊያ አበርክተዋል፡፡
   ደቡብ አፍካ ባዘጋጀችው የቻን አፍሪካ ዋንጫ ሊቢያ የዋንጫ፣ የገንዘብ እና የወርቅ ሚዳሊያ ተሸላሚ ስትሆን ጋና በሁለተኛ ደረጃ የብር ሚዳሊያ እና የገንዘብ እንዲሁም ዝምባብዌን ያሸነፈችው ናይጄሪያ ደግሞ የነሐስ ሜዳሊያ እና የገንዘብ ሽልማት ተበርክቶላቸዋል፡፡
    በምሽቱ ጨዋታ ላይ ሁለት ጎሎችን ያዳነው የሊቢያው ግብ ጠባቂ ስቴቭን አዳምስ የጨዋታው ኮኮብ ተብሎ ሲመረጥ፤ የደቡብ አፍሪካው በርናርድ ፓርከር ሐገሩ ባደረገችው ሶስት የውድድሩ ጨዋታዎች አራት ጎሎችን በማስቆጠር የኮኮብ ጎል አግቢነት ሽልማትን አግኝቷል፡፡
   በ2014 የቻን አፍሪካ ዋንጫ ላይ ናይጄሪያዊው ሰባት ቁጥር ለባሽ ኢጂኬ ኦዞዲዜ የውድድሩ ምርጥ ተጫዋችነት ክብርን በማግኘት ተሸላሚ መሆን ችሏል፡፡
     የ2016 የቻን አፍሪካ ዋንጫ አዘጋጅ በመሆን የተመረጠችው ሩዋንዳ ከ2014 የቻን አፍሪካ ዋንጫ አዘጋጅ ደቡብ አፍሪካ የአዘጋጅነት አርማውን ተረክባለች፡፡

No comments:

Post a Comment