Saturday, September 3, 2022

መንዝ - እመጓ ኡራኤል ….


ይህ ቦታ ከመንዝ ማማ ምድር ወረዳ - ሞላሌ ከተማ በስተ ምእራብ አቅጣጫ 2 ሰአት 30 ደቂቃ የእግር ጉዞ ከተጓዙ በኋላ የሚገኝ ሲሆን ቤተ ክርስትያኑን ያሰሩት አጼ ናኦድ እንደሆኑ በድርሳኑ ላይ ተጽፎ ይገኛል፡፡ በዚህ ቦታ በአመት አንድ ጊዜ የእርገት በዓል በድምቀት ተከብሮ ይውላል፡፡ ቦታው ቅዱስ ዑራኤል የጌታችንን ቅዱስ ደም የረጨበት ሲሆን በአሁኑ ሰአት በየአመቱ የእርገት በዓል ሲከበር ከተለያዩ አካባቢዎች ምእመናን በመምጣት እየጎበኙ እና በረከትን እያገኙ ይገኛል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም በዚሁ አካባቢ የቅዱስ ጊወርጊስ ፈረሶች ከተራራ ተራራ እየዘለሉ ለብዙ ዘመናት የአካባቢውን ማህበረሰብ ያሰቃይ የነበረውን ሰይጣን ድል ለመንሳት ሲዋጉ ፈረሶቹ የረገጡት የእግራቸው ኮቴ ቅርፅ ድንጋይ ላይ ቀርቶ የሚታይበት ተአምረኛ ቦታ ነው፡፡

በተጨማሪም ከዚህ ቦታ በስተ ደቡብ ምእራብ በኩል በገደሉ ስር በአፄ ናኦድ ዘመነ መንግስት የተመሰረተች ቀጭን አምባ ማርያም የምትባል ቤተክርስትያን ስትገኝ በዚች ቅድስት ቦታ ብዙ ተአምራት የተደረጉ ሲሆን ከነዚህም መካከል በጌታችን የስቅለት እለት አጋንንት ወደ ሲኦል የወረዱበት አስደናቂ ቦታ ይገኛል፡፡ መንዝ ውስጥ የሚገኘው /እመጓል - ቆጵሮስ ኢየሱስ ቅዱስ ኡራኤል /ገዳም በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ታሪክ ከመጀመሪያዎቹ አራት ቀደምት ደብሮች አንዱ ሲሆን ድንግል ማርያም ከልጅዋ ጋር በተሰደደች ግዜ የተቀመጠችበት እና ቅዱስ ፅዋው የሚገኝበት ቅዱስ ቦታ ነው።

በቦታው 2 ተራራ አሉ:-

1-  ገሊላ(ክሊና)ተራራ:- ይህ ተራራ እመቤታችን የተቀመጠችበት ጌታችን እየሱስ ክርስቶስ ኢትዮጵያን አስራት ሀገርሽ ትሁንሽ ብሎ ያረገበት ቦታ ነው፡፡በተራራው ላይ በአየር ላይ የቆመ ድንጋይ ይታያል፡፡ በድንጋው ላይ ተወጥቶ 3 ግዜ ይዞራል፡፡

2-  ቆጵሮስ ተራራ:- ይህ ተራራ ቅዱስ ኡራኤል የጌታን ደም የረጨበት ጽዋ(መነሳነስ) የሰወረበት ተራራ ነው የሰወረበት ቦታ ይታያል።

ደብረ ቆጵሮስ - በእውቅ አክርማ ስፌት የተሰራ የመሶብ ክዳን የመሰለ ተራራ በእመጓ ቤተክርስቲያን በስተ ሰሜን ሲገኝ ከጌታችን ልደት በፊት በቦታው ላይ ዘንዶ ይመለከበት እንደ ነበር ይነገራል፡፡ ሌላው ተራራ ላይ ያለው አስደናቂ ተኣምር ተራራው ጫፍ መሀል ላይ አንድ የተሰነጠቀ ቦታ አለ ታዲያ ምእመናኑ ያንን ስንጥቅ ቦታ የተራመደ ከሀጢያት የጸዳ ነው ፡፡ መራመድ ያቃተው ደግሞ ሀጢያተኛ ነው የሚል እምነት ስላላቸው ቦታውን የረገጡ ሁሉ ይህንን ተኣምራዊ ቦታ ተራምዶ እራሱን ሀጢያተኛ ወይም ነጻ መሆኑን አረጋግጦ ይመለሳል ፡፡


ቅዱስ ኡራኤልም አምላኩንይህችን ቦታ በችሮታህ ቀድሳትበበረከትህም ባርክልኝ ሲል ለምኖ አስባርኳታል” መላኩ ቅዱስ ኡራኤል ጌታችን እስካረገበት 40ኛው ቀን ድረስ 40ቀን በቦታው ተቀምጦበታል በማለት አባቶች ይናገራሉ፡፡ አምላክም ለመልአኩ ቦታውን ‹‹ርስት ጉልት ትሁንህና ገንዘብ አድርጋት››ሲል ባርኮ መስጠቱን ድርሳኑ ይተርካል ፡፡ በዚህ መሰረት እመጓ ደብረ ቆጵሮስ ገዳም የቅዱስ ኡራኤል አስራት ስለሆነ ቅዱስ ኡራኤል ገዳም በመባል ሲጠራ የንግስ በአሉን ጌታችን በአረገ 40ኛው ቀን ሲውል በእለቱ ከአዲስ አበባን ከተለያዩ ቦታዎች ብዙ ምዕመናን በቦታው በመገኘት ከበረከቱ ተቋድሰው ወደየመጡበት ይመለሳሉ፡፡ እርሶዎም ይህንኑ አስደናቂ እና ታሪካዊ ቦታ ለማየት ይፍጠኑ!!!

       አዘጋጅ፡-  የመ///////ቤት የቅ////የስራ ሂደት

No comments:

Post a Comment