Friday, December 30, 2022
የብራዚሉ የእግር ኳስ ኮኮብ ፔሌ ከዚህ አለም በሞት ተለየ፡፡
“የእግር ኳሱ ንጉስ” ተብሎ የሚጠራው ብራዚላዊው ኳስ ተጫዋች ፔሌ በ82 ዓመቱ ከዚህ ዓለም በሞት መለየቱን ብሉን በርግ ዘግቧል፡፡
በእግር ኳሱ ዓለም ትልቅ ስም ያለው ብራዚላዊው የእግር ኳስ ተጫዋች ፔሌ ባጋጠመው የካንሰር ህመም ሆስፒታል ገብቶ ህክምና ሲከታተል የቆየ ቢሆንም ህይወቱን ማዳን አልተቻለም።
በሙሉ ስሙ ኤድሰን አራንቴስ ዶ ናሲሜንቶ በመባል የሚታወቀው ፔሌ በአለም ዋንጫ ታሪክ ሶስት የዓለም ዋንጫዎችን፣ በ1958፣ 1962 እና በ1970 ከሀገሩ ጋር የውድድሩ አሸናፊ በመሆን ብቸኛ ባለታሪክ ነው፡፡
አለም በእግር ኳሱ ካየቻቸው የምንጊዜም ምርጦች መካከል ስሙ የሚጠቀሰው ኤድሰን አራንቴስ ዶ ናስሜንቶ ወይም በቅፅል ስሙ ፔሌ እ.አ.አ በ1940 በብራዚል ትሬስ ኮራኮስ መወለዱን ታሪኩ ያስረዳል። በልጅነቱ ግብ ጠባቂ ሆኖ ሲጫወት የሠፈሩ ልጆች በአካባቢው በሚታወቅ አንድ ተጫዋች ስም ‘ቢሌ’ ብለው እንደጠሩትና በግዜ ሂደት ስሙ ወደ ‘ፔሌ’ እንደተቀየረ ፔሌ ከዚህ በፊት በሰጣቸው ቃለ ምልልሶች ተናግሮ ነበር፡፡
በታችኛው የብራዚል ሊግ ሲጫወት ቆይቶ እ.አ.አ በ1956 በዋናው ሊግ የሚጫወተውን ሳንቶስ እግርኳስ ክለብን ተቀላቅሎ በአጥቂነት ተጫውቷል። ከሁለት አመት በኋላ ምትሀተኛው አጥቂ ፔሌ በ17 አመቱ ሃገሩ በአለም ዋንጫ እንድትደምቅ አደረጋት፤ በፍፃሜው ጨዋታም ተጋጣሚያቸው ስዊድን ላይ 2 ግቦችን አስቆጥሮ ዋንጫውን ከፍ እንዲያረጉ ምክንያት ሆኗል። ፔሌ በፍጥነት፣በሚዛን አጠበበቅ፣በኳስ ቁጥጥር፣በጥንካሬ እና ተጋጣሚን በሚያሸብሩ እንቅስቃሴዎቹ አለምን ያስደነቀ ነበር። ክለቡ ሳንቶስንም 3 ጊዜ ለሻምፒዎንነት አብቅቷል።
እ.አ.አ ኖቬምበር 19፣1969 18ሺህ ደጋፊዎች በተገኙበት የማራካኛ ስቴድየም ፔሌ 1000ኛ ጎሉን በፍፁም ቅጣት ምት ቫስኮ ደጋማ ላይ አስቆጠሮ ታሪኩን ጽፏል። ፔሌ በ1974 እግር ኳስ በቃኝ ብሎ ጫማውን ቢሰቅልም በ1975 በ7 ሚሊዮን ዶላር የአሜሪካውን ኒውዮርክ ኮስሞስን ተቀላቅሏል። ኮስሞስን ሻምፒዮን ያረገው ፔሌ እግር ኳስ በአሜሪካ እንዲለመድ ጥረት አድርጓል። በ1977 ጥቅምት 1 ፔሌ የመጨረሻውን ፕሮፌሽናል የእግርኳስ ጨዋታውን በጂያንትስ ስቴድየም ከቀድሞ ክለቡ ሳንቶስ ጋር አድርጎ ጫማውን ሰቅሏል።
ፔሌ ረጅም አመታትን በተሻገረው ደማቅ የእግርኳስ ህይወቱ ከ1280 በላይ ግቦችን አስቆጥሯል። በ2000 ላይ ፊፋ የሚሊኒዬሙ መርጥ ተጫዋች ሲልም ሰይሞታል። ፔሌ ጫማውን ከሰቀለ በኋላ የስፖርት አምባሳደር ሆኖ ከተባበሩት መንግስታት ድርጅት እና ከዩኒሴፍ ጋር በወዳጅነት ስፖርታዊ ውድድሮች በዓለም ላይ ሰላም እና እርቅ እንዲሰፍን ጥረቶችን አድርጓል። በተለየ ብቃቱና፣ በተወዳጅ ፈገግታው የሚታወቀው ፔሌ እግር ኳስ በዓለም ተወዳጅ እንዲሆን አድርጎ በ82 ዓመቱ ከዚህ ዓለም በሞት ተለይቷል፡፡
Subscribe to:
Post Comments (Atom)
No comments:
Post a Comment