መልካም ጓደኝነትን በዕጣ ወይም በሒሳብ ቀመር ተጠቅመን የምናገኘው ነገር ባይሆንም የራሱ የሆኑ መመዘኛዎች ግን ይኖሩታል፡፡ እውነተኛ ጓደኞች ውድና ብቅር እንደሆነ አልማዝም ናቸው ፡፡ የችግር ተካፋይ፣ የሐዘን አጋሮች፣ ተስፋ የቆረጠውን ተስፋውን የሚያለመልሙ ፣ የወደቀውን የሚያነሡ ከጨለማ ወደ ብርሃን ፣ ከሞት ወደ ሕይወት የሚመልሱ በአጠቃላይ ከጎናችን ሆነው የሕይወት ስንክሣራችንን የሚጋሩ ጓደኞች ዋጋቸው ከወርቅም ከዕንቁም የበለጠ ነው፡፡ አብሮን የዋለ አብሮን ያደረ በተለያየ እንቅስቃሴአችን ውስጥ የምናገኘው ሰው ሁሉ የልብ ጓደኛችን ሊሆን አይችልም፤ ነገር ግን ከእነዚህ ሰዎች መሀል ሃሣቡ ከሃሣባችን፣ ዓላማው ከዓላማችን፣ ሕይወቱ ከሕይወታችን የሚገጣጠመው ብቻ ባልንጀራችን ይሆናል፡፡
ብዙ ሰዎች በጓደኝነት ጉዳይ ብቻም ሳይሆን በሌሎች ነገሮች ላይም እነርሱ
ያልሆኑትን ከሌላው የመመኘት ባሕርይ አለ፤ ነገር ግን ሰዎች እንዲታመኑልን ከፈለግን እኛ ታማኝ፣ ሰዎች እንዲያፈቅሩን ከፈለግን
እኛ የፍቅር ሰዎች መሆን፣ ሰዎች ይቅር እንዲሉን ከፈለግን እኛ የይቅርታ ልብ ሊኖረን ይገባል፡፡ በአጠቃላይ መልካም ጓደኛ ለማግኘት ከፈለግን እኛም ለሌሎች ጥሩ ጓደኞች
መሆን ይጠበቅብናል፡፡
አንዳንድ ሰዎች ጓደኝነትን የሚመሠርቱት ጥቅም ለማግኘት ሆን ብለው አስበው፣
በሽንገላ ከንፈር አንደበታቸውን በማጣፈጥ፣ ንብረት ለመውረስ ፣ ገንዘብ ለመዝረፍ ይሞክራሉ ፤ ከተሳካላቸውም ያደርጉታል፡፡
ጓደኛዬ ባሉት ሰው ትከሻ ተረማምደው ከሀብት ርካብ፣ ከሥልጣን ኮርቻ ላይ ከተፈናጠጡ በኋላ ያንን ሰው ከነመፈጠሩ ይረሱታል፡፡
የልብ ጓደኝነት
በዘር፣በቋንቋ፣ በአንድ አካባቢ ተወላጅነት ወዘተ ላይ በመመስረት ሊመጣ የሚችል አይደለም፡፡ ጓደኝነት በፍፁም ፍቅር ላይ
የተመሠረተ መሆን አለበት፡፡ መልካም ጓደኛ ለችግር ጊዜ ደራሽ ፣ በመከራ ፣ በሐዘን፣ በደስታ ተካፋይ፣ መልካም አማካሪና፣
ገመናን ሸፋኝ ነው፡፡
እውነተኛ ጓደኝነት በሁለቱ ሰዎች ብቻ ተወስኖና ከቤት ውጪ የሚደረግ ሆኖ
አይቀርም፡፡ አንዱ በሌላው ቤተሰብ ታውቆና ተወዳጅቶ ዝምድናን ይፈጥራል፡፡ በጓደኛው ቤተሰብ ውስጥ በሚፈጠር ሐዘንም ሆነ ደስታ
ተካፋይ ይሆናል፡፡ ጓደኝነት ዘወትር ፍጹምነት ሊኖረው አይችልም አልፎ አልፎ አንዳንድ ልዩነቶች እና አንደኛውን ወገን
የሚያሳዝኑ ነገሮች በማወቅም ባለማወቅም ሊከሠቱ ይችላሉ፡፡ እንዲህ አይነት ጥቃቅን ነገሮችን በመቻቻል ማሳለፍ ከእውነተኛ
ጓደኝነት ባሕርያት አንዱ ነው፡፡ በመሆኑም በመልካም ጓደኝነት ውስጥ ይቅር ባይነትና መቻቻል አስፈላጊ እና ሊኖርም ይገባል፡፡
መልካም ጓደኝነት በአፍ(በቃል) ሳይሆን በተግባር የሚገለጽ ነው፡፡ ሲለያዩ የሚረሣሡ፣ በአጋጣሚ ካልሆነ በምክንያት የማይገናኙ፣ የልባቸውን የማይተዋወቁ፣ የዓላማ አንድነት፣ የባሕርይ ተመሳሳይነት የሌላቸው ነገር ግን ጓደኛሞች ነን የሚሉ ካሉ ተሳስተዋል፣ ይህ ጓደኝነት ከዕለታዊ ወይም ከወቅታዊ ግንኙነት የተሻለ አይደለምና፡፡ እውነተኛ ጓደኝነት እስከመስዋዕትነት የሚያደርስ ገንዘብንና ቁሳቁስን ብቻ ሳይሆን ነፍስን እስከመስጠት ሊያደርስ የሚችል ነው፡፡ እንግዲህ ጥሩ ጓደኛ እንደምንፈልግ ሁሉ እኛም ለሌላው ጥሩ ጓደኛ ለመሆን መዘጋጀት ይኖርብናል ፡፡
“ ብረት ብረትን ይስለዋል፥ ሰውም ባልንጀራውን ይስላል።”
No comments:
Post a Comment