በፊደሎቻችን ላይ ሦስት ሀ - ሐ - ኀ፣ ሁለት አ - ዐ -፣ ሁለት ሠ - ሰ ሁለት፣ ጸ - ፀ አሉ፡፡ እነዚህ ፊደሎች የራሳቸው የሆነ የስም አጠራርም አላቸው፤ ሀሌታው ሀ፣ ሐመሩ ሐ፣ ብዙኃን ኀ፣ ንጉሡ ሠ፣ እሳቱ ሰ፣ ጸሎት ጸ፣ ፀሐዩ ፀ ይባላሉ፡፡ በጽሑፍ የሚገቡበትን ተገቢ (ተስማሚ) ቦታም አላቸው፡፡ ለምሳሌ በሁለት ፊደሎች መጠቀም ይቻላል፡፡ ሀገር አገር ይህ ትክክለኛ አጻጻፍ ሲሆን፤ ነገር ግን ከዚህ ውጪ ሐገር፣ ኀገር ብሎ መጻፍ ግን ስሕተት ይሆናል፤ የሚከተሉትን ደግሞ እንመልከት፤
ሕገ መንግሥት፣ ሕገ ወጥ፣ ሕዝብ፣ ሕብረት፣ ዓቃቤ ሕግ፣ ወዘተ. የመሳሰሉት አጻጻፋቸው ትክክል ነው፡፡ ከዚህ ልማዳዊ አሠራር ውጪ ህገ መንግሥት፤ ህገወጥ፤ ህዝብ፤ ህብረት፤ አቃቤ ህግ ስሕተታዊ አጻጻፍ ይሆናል፤ ሌላ ማስረጃ ቢፈለግ፤ ኃይለሥላሴ የሚለው ስም ሦስት የተለያዩ ፊደሎች ይዟል፡፡ የመጀመርያው ፊደል ብዙኀን - ኃ - ሲሆን፣ ከንጉሡ -ሥ- ሳድስ፣ ከእሳቱ -ስ- ሃምስን በመጻፍ እንዲካተት ተደርጓል፡፡ ሀይለ ስላሴ ብሎ ቢጻፍ ግን የፊደሎቻችን የአጻጻፍ ሥርዓት ማፋለስ ይሆናል፤ በአቦ ሰጡኝ ፊደሎቻችን አለቦታቸው መግባትም፣ መጻፍም የለባቸውም፡፡
በዓፄ ኃይለ ሥላሴ ዘመነ መንግሥት በማስታወቂያ ሚኒስቴር ረዳት ሚኒስትር የነበሩት የተከበሩ ብላታ ወልደ ጊዮርጊስ ወልደ ዮሐንስ የቅድሚያ ዓይነተኛ ሥራቸው የፊደሎች ዘሮች አለቦታቸው እንዳይጻፉ መጠበቅ ነበር፤ በዚያን ወቅት ተማሪ ሁኜ አልፎ አልፎ በጋዜጣ እንዲወጣልኝ አንድ አንድ ሐሳብ በማመንጨት እጽፍ ስለነበር ብዙ ጊዜ አርመውኛል፡፡
ከእሳቸው በተማርኩት ትምህርትና ባገኘሁት ልምድ አእምሮዬን አሻሽያለሁ፡፡ በቀድሞው የንጉሠ ነገሥቱ ዘመነ ሥርዓት የክፍል ሹም የመጀመርያ ሹመት ሆኖ ወደ ላይ እንደሚከተለው ይዘልቃል፡፡ ዲሬክተር ዋና ዲሬክተር፤ ረዳት ሚኒስትር ምክትል ሚኒስትር፣ ሚኒስትር ዲ-ኤታ፤ ሚኒስትር፡፡ ከምክትል ሚኒስትር ወደ ላይ ያሉት እስከ ሚኒስትር ማዕረግ የደረሱት ክቡር ይባላሉ፡፡ ከዚህ በታች ያሉትን ግን ክቡር አይባሉም፡፡ በተመሳሳይ ያሉትን ማለት ኮሚሽነሮች፤ ሌ/ጀኔራሎች፣ አምባሳደሮች ክቡር ይባላሉ፡፡ ሚኒስትሮች የነበሩ በዳሬክተርና በሥራ አስኪያጅነት ሥራ ቢመደቡ እንኳን የቀድሞውን የሚኒስትር ማዕረጋቸውና ክብራቸው አይቀነስባቸውም፡፡ ክቡር መባል አለባቸው፡፡ ሥርዓት ነውና፡፡ ይህንኑ መለመድ ይገባዋል፤ በወታደሩ ሹመት አሰጣጥ ግን ያለው ሥርዓት የተጠበቀ ስለሆነ መልካም ነው እላለሁ፡፡ ከዚሁ ሌላ የምለው አለኝ፡፡ ባሁኑ በኢሕአዴግ መንግሥት ዘመን አምባሳደር ነዋሪ የማዕረግ መጠሪያ ስም ሆኖአል፡፡ አንድ አምባሳደር የዲፕሎማሲውን ሥራ አቁሞ ሲዛወር ልክ በሥራው እንዳለ ተቆጥሮ “አምባሳደር” እየተባለ መጠራት የለበትም፡፡
ለምሳሌ በዓፄ ኃይለ ሥላሴ ዘመነ መንግሥት አምባሳደርነት ተሹመው የነበሩት ክቡር አቶ ጋሻው ዘለቀ፣ ክቡር አቶ ዘነበ ኃይለ፣ ክቡር ልጅ መንበረ ያየህ ይራድ፤ ክቡር ፊታውራሪ መሐመድ ሲራጅ ብዙ ዘመን በአምባሳደርነት ሲሠሩ ቆይተው ተልእኮዋቸውን ፈጽመው ወደ አገራቸው ሲመለሱ አምባሳደር የሚል ቀርቶ በቀድሞ ስማቸው አቶ ተብለው ነበር የሚጠሩት፤ ይህንኑ ጠይቆ ለማረጋገጥ ይቻላል፡፡ ፊታውራሪ የነበሩትም፤ ፊታውራሪ ተብለው ይጠራሉ፡፡ ዘላቂ ሆኖ ከሰው ጋር ቅጽል የማዕረግ ስም ሆኖ የሚያገለግል ነው፡፡ በራሴ ምሳሌ ልውሰድ፤ ከግርማዊ ጃንሆይ በአዋጅ የተሰጠኝ የማዕረግ ስም ፊታውራሪ ነው፤ በዚህ ምድራዊው ዓለም እስካለሁ ድረስ የምጠራበት ሲሆን፣ ከሞትኩም በኋላ እጠራበታለሁ፡፡ እንዲሁም በንጉሠ ነገሥቱ መልካም ፈቃድ የሚሰጠው የሥልጣንና ማዕረግ ተዋረድ ባላምባራስ፣ ግራዝማች፣ ቀኛዝማች ፊታውራሪ፣ ደጀዝማች፣ ቢትወደድ፣ ራስ ቢትወደድ፣ ልዑል ራስ፣ አልጋ ወራሽ፣ ንጉሥ ንጉሠ ነገሥት ሲሆን፣ በሌላ በኩል ደግሞ ብላታ፣ ብላቴን ጌታ፣ ፀሐፊ ትዕዛዝ፣ ሊቀ መኳስ በሕይወት ሳሉ ይጠሩበታል፡፡ ከሞቱም በኋላ ስማቸውና ታሪካቸው በተነሣ ቁጥር ከመቃብር በላይ ሆኖ በማዕረጉ ስም ይጠሩበታል፡፡
አምባሳደር ግን የማዕረግ ስም መጠሪያ ስላልሆነ የዲፕሎማሲ ሥራቸውን ሲያቋርጡ አምባሳደር ተብለው ሊጠሩበት አይገባም፡፡ በሌላ መንግሥት የማይሠራበት ሲሆን የኢትዮጵያ መንግሥት ለብቻው በዚህ ስም አጠራር ሕጋዊ ማድረጉ ተገቢ አይመስለኝም፡፡ እንደ ማዕረግ በዘላቂነት ይጠሩበት ከተባለ እኔ ከማሳሰብ በቀር እምጎዳበት የለም፡፡ ከዚህ ጋር የማያይዘው ሌላም አለ፤ ከላይ በዝርዝር እንደገለጽኩት ባሁኑ ሰዓት ዲሬክተር ጄኔራል እየተባሉ አንዳንድ ሹማምንት ይጠሩበታል፡፡ በእኔ አስተያየት ዲሬክተር ጄኔራል ከማለት ይልቅ ዋና ዲሬክተር ቢባሉ ወይም ለስም አጠራሩ የሚቀል ስለሆነ ረዳት ሚኒስትር እየተባሉ ቢጠሩ መልካም ነው፡፡ በዚህ ቢታረም ያማረ ይሆናል፡፡
በማጠቃለያ የማቀርበው ሐሳብ በየዕለቱ እና በየሳምንቱ በሚታተሙ ጋዜጦች መጽሔቶች፣ መጻሕፍት የፊደሎቻችን ዘሮችና ልማዳዊ የአጻጻፍ ሥርዓቶች ይጠብቁ (ይከበሩ) በማለት ሐሳቤን እቋጫለሁ፡፡ እንዲሁም የኮምፒውተር ፀሐፊዎች ይህንኑ የአጻጻፍ ስልት (ፈለግ) ተከትለው ይጠቀሙበት በማለት መልእክቴን አስተላልፋለሁ፡፡ በተጨማሪም ደራስያን፣ አስተማሪዎች፣ ማተሚያ ቤቶች፣ ከያኒያን ይህንኑ እንዲተገብሩ ማድረግ የግል ኃላፊነት ስላለባቸው ትኩረት ይስጡበት እላለሁ፡፡
ሌላው መታረም የሚገባው፣ “ስፖርት” እየተባለ የሚጻፈው ነው፡፡ ምክንያቱም የአውሮፓ ፊደል ኤስ (S) የእ ፊደል ድምፅ ስላለው፣ Sport ቢጻፍ ትክክል ነው፤ የእኛው ፊደል (ስ) ግን ድምፁ የተዋጠ ስለሆነ እ ፊደል ተጨምሮበት “እስፖርት” ቢባል የተሻለ ነው፤ እንዲሁም ለርምጃ እርምጃ ቢባል፣ በኔ በኩል ጥሩ ስለሆነ ታስቦበት ቢታረም መልካም ይመስለኛል፡፡
ምንጭ:- ሪፖርተር ጋዜጣ (በፊታውራሪ አበበ ሥዩም ደስታ)
No comments:
Post a Comment