Sunday, August 3, 2014

አልዩ አምባ እና አብዱል ረሱል ምን ያውቃሉ …?

አልዩ አምባ በቀደምትነት ከምትታወቅባቸው መካከል፡-
 F የመጀመሪያዋ የጉምሩክ ከተማ በመሆን
 F በቀዳሚነት የስልክ መስመር የተዘረጋባት እና
 F የመጀመሪያው የቀረጥ ዉል የተፈረመባት ጥንታዊ ከተማ ናት፡፡ 

  አልዩ አምባ ከአንኮበር ከተማ አሥራ ሁለት ኪሎ ሜትር ያህል ቁልቁል ሲወረድ ትገኛለች። የወደብ ከተማ በመሆኗ 4 በሮች ነበሯት፡፡ የአካባቢው አዛውንቶች እንደሚያስረዱት ከሆነ አዋሽ እና ጨኖ መግቢያ ሲሆኑ አንኮበር እና ምንጃር በር ደግሞ መውጫ በሮች ናቸው፡፡ በወቅቱ የጦር መሳሪዎች እና የተለያዩ ሸቀጣ ሸቀጦች ወደ ሀገር ውስጥ ሲገቡ የዝሆን ጥርስ ፣ ቡና ፣ ወርቅ ፣ እና የመሳሰሉት ደግሞ ወደ ውጪ ይላኩ ነበር ፡፡
  ከመካከለኛው ዘመን ጀምሮ እስከ 20ኛው ክፍለ ዘመን መጀመሪያ ድረስ በኢትዮጵያ ታሪክ ጥንታዊ ከሚባሉት የቀረጥ ኬላዎችና የንግድ ማዕከሎች አንደኛዋም ነበረች። የፈረንሳይ ዲፕሎማት ሮቺ ሄሪኮርት እንደፃፈው 1500 እስከ 1700 የሚጠጉ ግመሎች የአገር ውስጥ ምርት ወደውጭ ያጓጉዙባት ነበር። 

  በ1834 . እና 1835 . በአገራችንመጀመሪያ የሆነው የቀረጥ ውል የተፈረመውም በአልዩ አምባ ገበያ መሠረት ነው። በከተማዋ  ከፐርሽያ ( ኢራን) ከህንድና ከአረብ አገሮች የሚመጡ በርካታ የውጭ አገር ዜጎች ይኖሩባት እንደነበርም የተለያዩ ደራሲያን ጽፈውላታል።


  ስልክም ወደ ኢትዮጵያ እንደገባ  ከአጤ ምኒልክ ቤተ መንግሰት / አንኮበር / እስከ እቃ ግምጃ ቤታቸው መስመር ተዘርገቶ ንጉሱ ነበሩ ለመጀመሪያ ጊዜ የተነጋገሩበት ፡፡ ከዚም አልዩ አምባ ውስጥ ስልክ አምባ የምትባል አካባቢ የመጀመሪያው መስመር ተዘረጋ ቀጥሎም ወደ ጨኖ እና ሌሎች አካባቢዎች ተስፋፋ በማለት የአካባቢው አዛውንቶች ይናገራሉ። እነዚሁ አባቶች አልዩ አምባ የተዳከመችው የባቡር ሐዲድ በከተማዋ ማለፍ ባለመቻሉና ወደ ድሬደዋ በመዛወሩ መሆኑን ያስረዳሉ ዛሬ የአልዩ አምባ ገበያ አብዛኛዎቹን አርጎባዎች ይዞ የአፋርንና አማራ ብሔረሰቦችን ያገናኛል።

     አብዱል ረሱል ከ1285 እስከ 1415 ዓ.ም እንደተመሰረተች ይነገራል፡፡አካባቢው የወላስማ ስረወ መንግስት ግዛቱን ካስፋፋባቸው ስፍራዎች በቀዳሚነት ይጠቀሳል፡፡ ይህን ስያሜ ያገኘው አብዱል ናስር ከሚባሉ ሰው እንደሆነም የአካባቢው ነዋሪዎች ይገልፃሉ፡፡

  አብዱል ረሱል ቀደም ባለው ጊዜ የባሪያ ንግድ የሚፈፀምበት ሲሆን ይህ ባሪያ የሚገበያዩበት እና የሚያጉሩበት /የሚያሳርፉበት/ ቦታ በአካባቢው ነዋሪዎች ተለይቶ ይታወቃል፡፡  
  
  ከአካባቢው ባገኘሁት መረጃ መሰረት አንድ ባሪያ ከ 60 እስከ 120 ብር ድረስ ይሸጣል፡፡ የተኮላሸው ባሪያ 120 ብር ያወጣ ነበር ምክንያቱም ስለተኮላሸ  ልቡ ሴትን አያስብም ተብሎ ስለሚታመን እና ስራውን በአግባቡ ይፈፅማል ተብሎ ስለሚገመት ነው፡፡ 

  ስለዚህ ከፍተኛ ዋጋ ያለው የተኮላሸው ሲሆን ያልተኮላሸው ደግሞ ከ 60 ብር ጀምሮ ይሸጥ እንደነበር አንዳንድ የፅሁፍ እና የቃል ማስረጃዎች ይጠቁማሉ ፡፡ ከዚሁ ጋር በተያያዘም ኢትዮጵያ የሌግ ኦፍ ኔሽን/ league of Nation/ አባል እሰከ ሆነችበት ጊዜ ድረስ ያሉ የቀረጥ ደረሰኞችም አካባቢው ባሉ ግለሰቦች እጅ ይገኛል፡፡

No comments:

Post a Comment