እኚህ ሰው በኢትዮጵያ ስፖርት ውትድር ውስጥ ትልቅ ስም አላቸው ግን ተረስተዋል። አማን ሚካኤል አንዶም ይባላሉ። አማን አንዶም የተወለዱት ሱዳን ውስጥ ነው፡፡ አባታቸው በሱዳን የብሪትሽ ቅኝ ግዛት አስተዳደር ባለስልጣን ነበሩ፡፡ አማን የፅዮን ታላቅ ወንድም ናቸው፡፡ ከአማን በላይ ደግሞ መለስና ዮሐንስ የተባሉ ሁለት ወንዶች ነበሩ፡፡ አባታቸው አቶ ሚካኤል አፈንዲ አንዶም ለጃንሆይ የዘውድ በአል አዲስ አበባ መጥተው በነበረበት ሰዓት ልጆቻቸውም አብረው ነበሩ፡፡
ጃንሆይ የአፈንዲን ልጆች አዩና ‹እዚህ ሆነው ይማሩ አገልግሎትም ይስጡ ›አሉ፡፡ አፈንዲም ልጆቻቸውን በወቅቱ መስጠት ስላልፈለጉ ‹‹ ትምህርታቸውን እንደጨረሱ እልካቸዋልሁ፡፡ አሁን ግን እዚያው ሱዳን ውስጥ ከእኔ ጋር ይቆያሉ›› አሉ ፡፡ ጣሊያን ኢትዮጵያን ወርሮ ድል በተደረገ ጊዜ ጃንሆይ ከስደት በሱዳን በኩል መጡ ያን ጊዜ መለሰና ዮሐንስ ትምህርታቸውን አጠናቀው ነበር፡፡ጃንሆይም አፈንዲን ቃል በገባው መሰረት ልጆቹን እንዲሰጥ ጠየቁት አፈንዲ ተስማማ፡፡የአማን ታላቅ የሆኑት ዮሐንስና መለስ ፋሽሲቱ ጣሊያንን እያሳደደ ከነበረው ከብሪቲሽ አላይድ ጋር እንዲመደቡ ተደረጉ። ዮሐንስና መለስ ከአባታቸው ጋር ንጉሡ ጋር በቀረቡ ጊዜ አማን አብሯቸው ነበረ፡፡ አማን በወቅቱ በሱዳን የጅምናዚየም ሐላፊ ስለነበርና በስፖርት የዳበረ በመሆኑ ሰውነቱ ሰው አይን ውስጥ የሚገባ ነበር፡፡
ጃንሆይ አፈንዲን አዩና
- እሱ ከእኔ ጋር ይሁን
- እዚህ ነው?
- አይ ወደ ኢትዮጵያ እወሰደዋለሁ።
- አማንማ ከእኔ አይለይም።
- አማን በጣም ያስፈልገኛል።
- እሱ እኮ ገና ልጅ ነው፡፡
- ሰውነቱ የዳበረ ነው ስለ እሱም ሰምቻሁ
አፈንዲ ብዙ ተከራከሩ ጃንሆይም አማንን አጥብቀው ፈለጉት ከንጉሱም ጋር ወደ አዲስ አበባ መጣ። ብዙም ሳይቆይ ወታደሩን ክፍል ተቀላቀለ።
የአማን ሻምፒዮና
አማን ዘመናዊ ስፖርትን ለማስፋፋ ወታደሩን ማንቀሳቀስ ጀመረ፡፡ በግቢው ውስጥ ወታደሮችን መርጦ የእግር ኳስ ቡድን አቋቋመ ለንጉሡም ደብዳቤ አቀረበ፤ ውድድር እንዲያደርግ ተፈቀደለት፡፡በ1935 አዲስ የተቀጠሩ የአበሻ ወታደሮችን መልምሎ አራት ቦታ ከፍሎ ውድድር አዘጋጀ ፡፡ ስያሜውንም ‹የአማን ሻምፒዮና› አሉት እሱም ጎበዝ ተጫዋች ስለነበር የመድፈኛ ቡድንን ተቀላቀለ፤ በዋንጫ ውድድር የእሱ ቡድን ለፍፃሜ ቀረበ፡፡አሮጌው አውሮፕላን ሜዳ ንጉሡ ባሉበት ጨዋታው ተካሄደ፡፡ ንገሡም የስፖርት ውድድር በእንዲህ አይነት መልክ መካሄዱ ደስ አላቸው፡፡ ስፖርቱን እንዲያጠናክር ለአማን ሐላፊነቱን ሰጡት አማን የኢትዮጵያ ሻምፒዮና ውድድር ማዘጋጀት አለብኝ ብሎ ተነሳ፡፡
በከተማ ውስጥ ያሉትን ቡድኖች መዝገበ፡፡ ከወታደሩ አራት ከኮሚኒቲ ስምንት ቡድን በድምሩ 12 ክለቦች ያዘና እሱ ውድድሩን በሐላፊነት እየመራ በተጨዋችነትም እየተሳተፈ ሻምፒዮናውን ለማዘጋጀት ሁሉን ነገር አጠናቀቀ፡፡ ድልድልም አወጣ፡፡ አንድ ሳምንት ሲቀረው ማስታወቂያ ሚኒስቴር ሻምፒዮናውን የማዘጋጀው እኔ ነኝ ብሎ ከአማን ቀማው፡፡ከነርሱ ጋር ብዙ ተከራከረ ግን አልሆነለትም፤አማን የወታደሩን ምርጥ አቋቋመና ማስታወቂያ ሚኒስቴር ባዘጋጀው ውድድር ውስጥ ገባ ነገር ግን እንግሊዞች ወታደርን የሚወክለው አንድ ቡድን በመሆኑ እኛ ስለገባን እናንተ መጫወት አትችሉም ተባሉ በወቅቱ ቢ .ኤም.ኤም (ብሪትሽ ሚሊተሪ ሚሽን ) የተባለው የእንግሊዝ ወታደሮች ቡድን ሰራዊቱን የሚወክለው ‹ነጩ እንጂ ጥቁሩ› አይደለም ብለው የአማንን ቡድን እንዳይገባ አገዱት፡፡
አማን ከአራቱ ልዩ ልዩ ክፍሎች የመረጣቸውን ወታደሮች ‹‹ ጠቅል›› በሚል መጠሪያ ሰይሟቸው የኢትዮጵያ ወታደሮችን ወክሎ ነበር ሊገባ የፈለገው ነገርግን በእንግሊዞች እገዳ የኢትዮጵያ ወታደሮች ራሳቸውን ወክለው ሊገቡ አልቻሉም፡፡ አማንና ይድነቃቸው በስፖርት ይቀራረቡ ነበር፤ ጊዮርጊስ በውድድሩ ተመዝግቦ ነበር ግን የእንግሊዝና ግሪኮችን ቡድን ለመቋቋም የሚያስችል ብቃት ላይ አልነበረም ፤ጎበዝ ተጫዋቾች ያሉት ደግሞ ወታደር ቤት ውስጥ ነበር፡፡
አማንና ይድነቃቸው ተመካከሩና መጠሪያው የጊዮርጊስ ሆኖ ጠቅል የተባለው ቡድን ጊዮርጊስን ወክሎ ገባ ቡድኑም የጊዮርጊስ ሆነ ጊዮርጊስም ተጠናከረ በዚያን ጊዜ በእግር ኳስ ታዋቂ የነበሩት አመለወርቅ ተክለዜና፤ አፈወርቅ ተክለዜና ፤አማን አምዶም ፣ ወንድሙ ፈይሳ፣ እንዲሁም ፈለቀ፤ ገ/እግዚአብሔር እና ተስፋሚካኤል የተባሉት በጥቅሉ ዘጠኝ ወታደሮች ለጊዮርጊስ ቡድን ተሰልፈው ተጫወቱ ክለቡም ጠንካራ ሆነ እንግሊዞች ወታደሮቹን ከጊዮርጊስ ለማስወጣት ፈለጉ፡፡ ግን አልቻሉም፤በመቅጣትና ፍቃድ በመከልከል ጊዮርጊስን ለማዳከም ሞክረው ነበር፤በሂደት ደግሞ አማን በጎን በኩል የራሱን ቡድ ይዞ መግባት ፈልጓል፤ አማን ለንጉሡ በተለያየ ጊዜ ጥያቄ አቀረቡ የኢትዮጵያ ወታደር ቡድን እራሱን ወክሎ ውድድሩ ላይ መሳተፍ አለበት አሉ በመጨረሻም የእሺታን መልስ አገኙ ጉዳዩን የሚያውቁት እሳቸው ብቻ ነበሩ፡፡
የሁለቱ ጭቅጭቅ
አንድ ቀን ወታደሮች በግቢው ውስጥ ብቻ ልምምድ እንዲሰሩ ሌላ ቦታ እንዳይሄዱ ትዛዝ ተሰጠ ፤ይሄንን እዲያስፈጽም ተቆጣጣሪ ተመደበ ፤ተቆጣጣሪው ወደሜዳው ሄደ፡፡
- አመለወርቅ
- ፈለቀ
- አፈወርቅ
- ወንድሙ
- አማን እያለ ስም ጠራ ግን ከአንድ ሰው በስተቀረ ሁሉም አልነበሩም፡፡ ተቆጣጣሪው ‹‹አማን የት ሄደ›› ብሎ ጠየቀ፡፡ ጊዮርጊስ ክለብ ልምምድ ሊሰራ አንደሄደ ተነገራቸው፡፡ ተቆጣጣሪው በነገሩ ተገረሙ፡፡ ይሄን ትዕዛዝ ያስተላላፈው አማን ሆኖ እሱ እንዴት እንደቀረ ተገረመ፡፡ ትዕዛዝ ነውና የሄዱት በሙሉ ተቀጡ፡፡ አማንን ጨምሮ፡፡ በዚያን ወቅት ጊዮርጊስ ልምምዱን ከጨረሰ በኋላ አማንና ይድነቃቸው ተነጋገሩ አመለወርቅ ተክለዜና እንዲህ ይላሉ ‹‹ አማንና ይድነቃቸው ከልምምዱ በኋላ ጎሉ ጋር ሆነው ብዙ ተጨቃጨቁ አማን እጁን እያወራጨ ነበር የሚናገረው፡፡ ክርክሩ ሐይለኛ ነበር፡፡ሁለቱ ውይይታቸውን ከጨረሱ በኋላ ይድነቃቸው እኛን ሰብስበው ለጃንሆይ ደብዳቤ እንደሚፅፉና በስፖርቱ ጉዳይ እንደሚወያዩ ነገሩን፡፡
አንድ ቀን አማን ማንም ወታደር ጊዮርጊስ ጋር ሄዶ ልምምድ እንዳይሰራ ብሎ ተናገረ፡፡ ነገር ግን ማን እንደፈቀደልን ሳናውቅ ከበላይ በመጣ ትዕዛዝ ጊዮርጊስ ውስጥ ብቻ ነው የምትጫወቱት ተባለ። ከአማን በስተቀር ሁላችንም ሄደን መጫወት ጀመርን፡፡ በ1938 የኢትዮጵያ ጥሎ ማለፍ ዋንጫ ድልድል ሲወጣ ከማን ጋር እንደደረሰን ለማወቅ ይድነቃቸውን መጠበቅ ነበረብን፡፡ያን ጊዜ ጊዮርጊስ ክለብ ልምምድ እየሰራን ነበር።እኛ ያለንበት ቦታ ይድነቃቸው መጣ፡፡ ፊቱን ስናየው ደስተኛ አይደለም፡፡ "አማን እኮ አስቸጋሪ ሰው ሆነ" አለን፡፡ ወታደር ወደሆንነው እያየ "እናንተ ከእንግዲህ ለአማን ነው የምትጫወቱት የእኛ አይደላችሁም"አለን፡፡
ይድነቃቸው ይሄን ሲናገር ተከፍቶ ነበር፤ ማንም ሳያውቅ አማን "ጠቅል" በሚል ስያሜ መመዝገቡን ሰማን፤ በነጋታው ይድነቃቸውን ጠየቅኩት እሱ በጣም ቅር የተሰኘው "ዘጠኝ ቋሚ ተሰላፊ ከአንድ ቡድን ሲወጣ ጊዮርጊስ ይደክማል እነዚህን ተጨዋቾች የሚተኩልንን ሰው እስካገኝ ጊዜ ስጠኝ ስለው እምቢ አለኝ አማን ጥሩ አልሰራም" በሚል ይድነቃቸው አጫወተኝ፡፡ ይድነቃቸው ሸምጋዮች ባሉበት ከአማን ጋር ብዙ ተከራክረዋል። ግን ሊሰማሙ አልቻሉም፡፡ ይድነቃቸው ለእኔ ከልጅነት ጀምሮ ጓደኛዬ ነው፡፡ ከእሱ መለየት አልፈልግም ግን ተቀጣሪ ወታደር ስለሆንኩኝ አማን ባቋቋመው የመቻል ቡድን ውስጥ መጫወት ግዴታዬ ሆነ ይላሉ፡፡ በቆይታ "ጠቅል" ክርክር ሊያስነሳ ስለሚችል አማን ‹መቻል› የሚለውንም ስም በተለዋጭነት አስመዘገቡ።
የመቻል መቋቋም
ከብዙ ሙግት በኋላ የኢትዮጵያን ወታደር የሚወክለው የመቻል ቡድን በአማን አማካኝነት ተቋቋመ፡፡ አማን የቡድኑ ተጨዋችም አሰልጣኝም ሆኖ ተመዘገበ። በዚሁ አመት በጥሎ ማለፍ ጊዮርጊስና መቻል ለዋንጫ ደረሱ፡፡ አመለወርቅ ውሎው ከይድነቃቸው ጋር ነው፤ አማን አመለወርቅን መከሩት፡፡ ለበላይ አለቆችም ሪፖርት አደረጉበት፡፡ ከይድነቃቸው ጋር እንዳይውል ደጋግመው አስጠነቀቁት፡፡ አመለወርቅ ግን ከይድነቃቸው መለየት አልቻለም፡፡ በድብቅ ይገናኙ ጀመር፡፡ ይድነቃቸው የሚሰራበት መስሪያ ቤት ሞተር ሳይክል ነበረው፡፡ ስራውን ስለለቀቀ ሞተሩን ማስረከብ ስለነበረበት ውስጡ ያለውን ቤንዚን መጨረስ ፈለገ፡፡ አመለወርቅን አፈናጠው ከተማውን መዞር ጀመሩ፡፡ አራት ኪሎ ደረሱ፤ በፍጥነት ላይ የነበረችው ሞተር ሳይክል ሰው ገጨች፡፡ ሁለቱም ወደቁ፡፡ አመለወርቅም ተጎዳ አማን ሁኔታውን ደረሱበት፡፡ አመለ ትእዛዝ ጥሶ ከይድነቃቸው ጋር በመታየቱ ወደ ክፍለ ሐገር መዘዋወር አለበት አሉ፡፡ ግን ደግሞ እሁድ የዋንጫው ቀን መሰለፍ አለበት ብለው ወሰኑ፡፡ አመለወርቅ እንደታመመ ገባ መቻል 2ለ1 ጊዮርስን አሸነፈው፡፡
ሁለቱን ጎል አመለወርቅ አስገባ፤ መቻል በታሪክ የመጀመሪያው ዋንጫ ያገኘ የአበሻ ክለብ ሆነ፡፡ አማን በመቻል ውስጥ እየታወቁ ሄዱ በወቅቱ አትዮጵያን የሚወክል ብሄራዊ ብድን ስላልነበረ አማን ብሄራዊ ቡድን አቋቁሚያለሁ ብሎ አወጀ፡፤ ተጨዋቾች ከየቦታው መረጡና የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ብለው ሰየሙ፡፡ቡድኑንምም እራሱ ማሰልጠን ጀመረ፡፡ከሀገር ውስጥ ቡድኖች ጋር መጫወት ጀመረ፡፡አመለ እንዲህ ይላል "ብሄራዊ ቡድን አቋቁሞ አሰለጠነን ከነግብጽና ሱዳን ጋር ለመጫወት እየተነጋገረ ነበር በምን እደሆነ ባላውቅም ባለስጣኖች ከለከሉት"ይላሉ:: አማን መቻልን ወክለው ስራ አስኪያጅ ኮሚቴ ውስጥ ገቡ፡፡ በ1939 በፕረዘዳንትነት ተመረጡ፡፡ ይድነቃቸው በጊዮርጊስ ውስጥ ተጠናክረው ከፍ ብለው ሲውጡ አማንም በመቻል ጀርባ ተንጠልጥሎ በእግር ኳስ ውስጥ ቁንጮ ሆነ፡፡
ጥቁርና ነጭ
ሁለቱ ሰዎች በክለቦቻቸው አማካኝነት ተቃራኒ ሆነው ቢሄዱም ብዙ ልዩነት ቢኖራቸውም በኢትዮጵያ እግር ኳስ ውስጥ ግን ትልቅ መነቃቃትን ፈጠሩ፡፡ የአፍሪካ እግርኳስ ፌዴሬሽን በ1949 ሲቋቋም ከመሰራቾቹ አንዷ ኢትዮጵያ ነች፡፡ ጉባኤውን ለመካፈል ኢትዮያጵያን ወክለው የሄዱት አማን፤ ይድነቃቸውና ገበየሁ ነበሩ፡፡ ኢትዮጵያ ዋና አላማ አድርጋ የሄደችው ዘረኛውን ደቡብ አፍሪካ ከውድድር ለማስወጣት ነበር፡፡ ይኸውም ቡድኑ ነጭና ጥቁርን መቀላቀል ስላልፈለገ ነው፤ስብሰባው ላይ ሲከራከረ ከቆየ በኋላ ደበቡ አፍሪካ ተባረረች፡፡ በወቅቱ የኢትዮጵያን ብሄራዊ ቡድን በአምበልነት የመራው ከበደ መታፊሪያ ነው፡፡ ከበደ ከመቻል የተመረጠ ተጨዋች ነው ስለሁኔታው እንዲህ ይላል "አማን አለቃዬ ነው ፡፡ ከስብሰባ እንደወጡ ማታ ሆቴል ውስጥ እራት ከበላን በኃላ ስለስብሰባው ነገረኝ ግብፅና ሱዳን የእንግሊዝ ቅኞች ስለነበሩ ደቡብ አፍሪካም በእንግሊዞች ስለምትታገዝ ግብፅና ሱዳን ላላ ብለው ነበር፡፡
ለሱዳንና ለግብፅ ተወካዮች በአረብኛ የምፈልገውን ነገርኳቸው ይሄን ያደረግኩት የእነዚያ ተወካዮች እንዳይሰሙ ነው፡፡ ከዚያ በኋላ ነገሩ አለቀ ብሎ ነገረኝ፡፡ ጉዳዩ ማታውኑ ለጃንሆይ ተላለፈ፡፡ ደቡብ አፍሪካ በመታገዷ እሳቸውም ደስ አላቸው" በማለት ይናገራሉ፡፡ አማን መቻልን ተክለው ዝነኛ ካደረጉ በኋላ ከኢትዮጵያ እግር ኳስ ውስጥ ቀስ እያሉ እየተገለሉ ሄዱ፡፡በውትድርናውም ገፉበት፡፡ በወታደርነታቸውም ታዋቂ እየሆኑ ሄዱ፡፡ በተለይ በ1953 የኢትዮ ሱማሌ ግጭት እንዲሁም በ1954 የዳኖት ግጭት ጊዜም ጥሩ አመራር አሳይተዋል፡፡
የ3ተኛ ክፍለጦርን ሀይለኛ አደረጉት ለጦሩ ሙዚቃ እንዲወጣ አዘዙ፡፡ "-- ሳንጃን 3ተኛ ክፍለጦሪ ነመኛታ ኦፈን!"የሚል ተሰራ፡፡ ትርጉሙ ‹የ3ተኛ ክፍለ ጦር ሳንጃ ይበላሃል› ማለት ነው፡፡ የ3ተኛ ከፍለጦር የሙዚቃ ባንድ ተጫዋች አበበ በመድረክ ላይ በደምብ ተጫውቶታል፡፤የዘፈኑ መጠሪያ ‹‹ነመኛታ›› ነው፡፡ይሄንን ዘፈን ከብዙ ጊዜ በኋላ በአ/አ ስታዲየም የመቻል ደጋፊዎች ይጠቀሙበት ነበር ፡፡በ3ተኛ ከ/ጦር አማን ዝነኛ በነበሩ ጊዜ ሻለቃ መንግስቱ ኃ/ማሪያም የመሳሪያ ግምጃ ቤት ሀላፊ ሲሆኑ የአማን አድናቂ ነበሩ፡፡ አማን በወታደርነታቸው ዝነኛ ሆኑ አማን ሳይሆን ”A” (ኤ.ማን) በሚል እስከመጠራት ደረሱ፡፡ንጉሡም በወታደሩ ዘንድ አማን ተደማጭ በመሆኑ አንድ ቀን ሊገለብጠኝ ይችላል በሚል ራቅ ያለ ቦታ አደረጓቸው፡፡ ስማቸውም ከማስሚዲያ እየራቀ ሄደ ፡፡ አማን በዝምታ ተቀመጡ፡፡ ደርግ ስልጣን ላይ ወጣ ብዙ ጄነራሎች ሲታሰሩ አማን ብቻ ሳይታሰሩ ደርግን ተቀላቀሉ፡፡
ኮዳ ትራሱ
ደርግ የሐገሪቱን ሥልጣን ከተቆጣጠረ በኋላ በየቦታው ያለው ወታደር ጥያቄ ነበረው፡፡ እነዚህ ነገሮች ደርግን አስጨነቁት፡፡ አንዱ ክፍል ተነስቶ "ጥያቄዬን ካልመለሳችሁልኝ እንደተሰበሰባችሁ መድፍ ልተኩስ ነው" እያለ ሲያስፈራራ ሌላኛው ተነስቶ ጥያቄውን ያቀርብና ሳይመለስለት ሲቀር "አንዳችሁን አፍኜ ልወስድ ነው"ብሎ ሲዝት ደርግ ተጨናነቀ፡፡ደርጉን የሚመሩ ሰዎች በወታደሩ ብዙም እውቅና የሌላቸው በመሆኑ ወታደሩን የሚያረጋጋ ታማኝ ሰው ፈለጉ፡፡ ለዚህ የተመረጡት ደግሞ ጄነራል አማን አምዶም ናችው፡፡መንግስቱና አማን ሀረር 3ተኛ ክፍለጦር ስለሚተዋወቁ መንግስቱ የራሱን ሰው አመጣ ተብሎ ተወቀሰ፡፡ አማን በወታደሩ ‹‹ ኮዳ ትራሱ›› በሚል ስያሜ ይታወቃሉ፡፡ በዋነኛነት ሠራዊቱ የሚተማመንባቸው በመሆናቸው አመራራቸውን ይቀበላል፡፡ እንዲሁም የከፍተኛ መኮንንኖችን ስጋት ለማርገብ ይጠቅማሉ በሚል የደርግ ሊቀመንበር ሆኑ፡፡
ከዚህም ሌላ የሀገሪቱ ርዕሰ ብሄር ሆነው ተሸሙ፤ የሐማሴን ተወላጆችም "ዘር ወጣልን ….. ቀን ወጣልን" በማለት ፈነደቁ፡፡ ሹመታቸውን ያገኙ ቀን ጉዳዩ ባልታወቀ ምክንያት አየር ሐይል "ጄነራሉን ከስልጣን ላይ አውርዷቸው እምቢ ካላችሁ አማንን አፍኜ እወስዳለሁ ጥያቄዬ ካልተፈጸመ በትዕዛዛችሁም ሥር አይደለሁም" አለ፡፡ ነገሩ ተረጋግቶ አማን ስልጠናቸው ላይ ቆዩ ጄነራሉ የሐገሪቱ መሪ ይሁኑ እንጂ የጦር ሐይሎች ጠቅላይ አዛዥ አልነበሩም፡፡ ነሐሴ መጨረሻ ላይ ቢ.ቢ.ሲ "አማን አንድ ደረጃ ወረዱ" ብሎ አወራ፡፡ ነገሩ አማን የሐገሪቱ መሪ ከሆኑ የጦር ሐይሎች አዛዥም መሆን ነበረባቸው አሁን ግን ከደረጃቸው ዝቅ እንዳሉ በመቁጠር ዘገበ፡፡አማን በነገሩ ቅር ተሰኝተዋል፤ መስከረም 5 ቀን 1967 ዓ.ም የደርግ ስብሰባ ላይ አባላቱ በሌላ ጉዳይ እየተወያየአማን ድንገት ስብሰባውን አቋርጠው "በእኔ ላይ ያለችሁ እምነት እስከምን ድረስ ነው" በማለት ተናገሩ፡፡
የደርጉ ጠቅላላ ጉባኤ የሚናገረው ጠፍቶት ብዙ ቆየ፡፡ ከዚያም "እኛ እኮ ሊቀመንበራችን ያደረግንዎት ስላመንዎት ነው" በማለት ተናገሩ፡፡ አማንም መተማመኛ ድምፁን ካገኙ በኋላ ወሳኙን ጥያቄ አስከተሉ "የጦር ሐይሎች አዛዥነቱ ክፍት መሆኑን ታውቃላችሁ፡፡ ይሄ ቦታ ሰው ከሌለው ደግሞ ችግር መፈጠሩ አይቀርም ፡፡ ደርግ እንደ ርዕሰ ብሔር እኔን ካስቀመጠኝ የጦር ሐይል አዛዥነቱን መያዝ አለብኝ ፡፡ ይሄን ልትፈቅዱልኝ ይገባል፡፡ ውሳኔያችሁን ዛሬውኑ እፈልጋለሁ" አሉ፡፡ የደርግ ጉባኤ ተናደደ፡፡ ሻለቃ መንግሥቱም ተቆጡ ቦታውን ለአማን መስጠት ወታደሩን ያነቃነቅባቸውና ደርግን እራሱ በትነው ሙሉ ስልጣኑን እንደሚይዙ ገመቱ፡፡ ይቺ ሰዓት ወሳኝ ነች ሻለቃ መንግሥቱ እንዲህ አሉ፡፡ "ጌታዬ ! በአሁኑ ወቅት የጦር ሐይሎች አዛዥነትን አንድ ሰው ሊይዘው አይገባም አዛዥነቱ የጠቅላላ ጉባኤው ነው፡፡ ለእርሶ አንሰጥም" አሉ፡፡ አማንም በዚህ ቅር ተሰኙ፡፡ይሄንን ሁሉ ገትሮ የያዘው መንግሥቱ እንደሆነ አውቁ፡፡
ጄኔራል አማንና ሻለቃ መንግሥቱ ሐረር ሶስተኛ ክፍለ ጦር ይተዋወቃሉ፡፡ አማን ምን እንዳሰበ መንግሥቱ ገብቶታል፡፡ መንግሥቱ ምን አይነት ሰው እንደሆነ አማን ያወቃሉ ፤አማን እንደምንም ብለው መንግሥቱን ከዚያ ቦታ ካስነሱት ወታደሩን መቆጣጠር ይችላሉ፡፡ መንግሥቱን ከቦታው ለማስነሳ ደግሞ አማን የጦር ሐይሎችን ስልጣን መያዝ አለባቸው፡፡በዚህ ጉዳይ ሁለቱ ክፉኛ ተቃቃሩ ፤ለመገዳደልም ይፈላለጉ ጀመር፡፡ አማን ስልጣኑን ስላላገኙ አኩርፈው ስብሰባ ላይ ብዙ ሳይመጡ ቀሩ፡፡ አንድ ቀን ጄነራል ግዛው በላይነህ ለአማን ስልክ ደውለው "እርሶ ለምን ስብሰባ አይመጡም" ብለው ጠየቋቸው፡፡ አማንም "እኔ ከማንም ዱቄት ሰፋሪ ጋር አልሰራም" ብለው የተናገሩትን በስልክ ተጠልፎ ለደርጉ ጉባኤ ቀረበ፡፡ አንድ ቀን ሻለቃ መንግሥቱ እና ሌሎች የደርግ ባለስልጣኖች ወደቤታቸወ ሄዱ፡፡ አማንንም አነጋገሯቸው አማን ግን ጥያቄያቸው ተቀባይነት ካላገኘ እንደማይመለሱ አሳወቁ፡፡
ወደስብሰባው የሄዱት የደርግ አባላት ተካ ቱሉ፤ አጥናፉ አባተ፤ ደበላ ዲንሳና ፍሰሃ ደስታ ነበሩ፡፡ ከስብሰባው እንደተመለሱ አማን ስልክ ደውለው ሰዎቹን ስላልፈለጓቸው በእነሱ ፊት መናገር ያልፈለጓቸው ነገሮች እንዳሉና መንግሥቱ ብቻ መጥቶ ያነጋግረኝ ብለው መልእክት አስቀመጡ፡፡ መንግሥቱ ግን ብቻዬን አልሄድም አለ፡፡ አማን መንግሥቱን ሊያናግሩት ሳይሆን ሊጠልፉት እንደፈለጉ አንዳንዶቹ ይገምታሉ፡፡ አማን መንግሥቱ ባለመምጣቱ ሌላ ዘዴ ፈጠሩ፡፡አማን ለምክትላቸው አንድ ሻለቃ ጦር እንዲልክለት አዘዙት ጉዳዩን ደርግ ደረሰበትና አገደው፡፡በሌላ ቀን ማንም ሳያውቅ አማን ከቦረና የመጣ ጦር አንቀሳቅሰዋል ተባለ፡፡ ደርግ ሥጋት ውስጥ ገባ በአማን ላይ አስቸኳይ ስብስባ ተጠርቶ ውሳኔ ይተላለፍ ተባለ፡፡ ህዳር 14 ቀን ጥዋት ጠቅላላ ደርግ ባለበት ስብሰባ ተቀመጡ፡፡ "እኚህ ሰውዬ ምን ይወሰንባቸው" ተባለ ቀኑን ሙሉ ሲነጋገሩ ዋሉ፡፡ብዙ ክርክር ተነሳ በመጨረሻም ተይዘው ይምጡ ተባለ፡፡ ሻለቃ መንግሥቱም ነገሩ እንዳይበላሽ አንድ ነገር አሰበ፡፡ ማን መሄድ እንዳለበትም ወሰነ፡፡ ቀኝ እጅ የሆነውን ሰው መረጡ፡፡
የደርግ የዘመቻ መምሪያ ሐላፊ የሆነውን ኮለኔል ዳንኤል አስፋውን አስጠሩት፡፡ ለእሱ ሁኔታውን አስረዱት፤ ፓርቶሎችን የሚያንቀሳቅሰው ዳንኤል ነበር፡፡ ዳንኤል ወታደሮቹን ይዞ ወደሰውዬው ቤት ሄዱ ፤እዚያ ሲደርሱ ጄነራል አማን መሳሪያ አጥምደው ተቀምጠዋል፡፡ ቤታቸው ጦር ሀይሎች ከግቢው ጋር ተያይዞ ነው፡፡ የሄዱት ወታደሮች ሁኔታውን አይተው በተኩስም እንደማይችሏቸው ተገንዝበው መጡና "አማን እምቢ ብለውናል እጅም ሊሰጡ አልፈለጉም ምን እናድርግ" አሉ፡፡ ጉዳዩ ለሻለቃ መንግሥቱ ነው የተላለፈው፤ ሻለቃ መንግስቱም እዚያው ሰብስባ ላይ እንዳሉ ዳኤልን አስጠርተው ነገሩት እንዲህም አሉት "በድምፅ ማጉያ አማን እጅ እንዲሰጥ ንገራቸው እምቢ ካሉ የሐይል እርምጃ ውሰዱ" ብለው ነገሩት፤፤ ዳንኤልም የተነገረውን ለማድረግ ትእዛዙን ተቀብሎ ሄደ፡፡
ጄነራል አማን ብቸኛ ሰው ነበሩ፡፡ ቤታቸውን የሚጠብቁትና አትክልት የሚኮተኩቱት አንድ ሰው ብቻ ነበሩ፡፡ ምግብም ከእህታቸው ቤት ነው የሚመጣው፡፡ በጥቅሉ ቤተሰብ የላቸውም ፡፡ እነ ዳንኤል ሲመጡ እጅ እንዲሰጡ ተጠየቁ፡፡ አማን እምቢ አሉ፡፡ ወታደሮቹ በዋናው መግቢያ በኩል ተጠጉ፡፡ ተኮሱ፡፡ አማን መትረየሳቸውን አንጣጡ፡፡ አካባቢው ተተረማመሰ በጩኸት ተናጋ ወታደሮችንም አላስጠጋ አሉ፡፡ጉዳዩ አስቸጋሪ ስለሆነ ደርግ ስብሰባ ላይ በሬድዮ መልእክት ለሻለቃ መንግሥቱ ተነገረው፡፡ መንግስቱም ተስፋዬ ወልደኪዳንን ወደቦታው ላከው፡፡ ተስፋዬ ደርግን የተቀላቀለው ታንከኛን ወክሎ ነው፡፡ ጄነራል አማን ወደ አሉበት ሲሄድ ሰውዬው ለነዳንኤል ስላስቸገሩ በታንክ ለመደምሰስ ነበር፡፡ እንደተገመተውም ታንከኛ ተጠራ፡፡ አማን እጁ አንዲሰጡ ተጠየቁ ፍቃደኛ አልሆኑም ታንኩ አፈሙዙን ወደአማን ቤት አስተካክለ ሄደ- ደረሰ ቤታቸውን ደርምሶ ገባ አማን ታንኩን መቋቋም አልቻሉም እናም በላያቸው ላይ ሄደ፡፡ የቀድሞ የመቻል ተጨዋች እና የብሔራዊ ቡድን አሰልጣኝ ከኳስ ተጨዋችነት እስከ ሐገር መሪነት የደረሱ ብቸኛ ሰው ቢሆኑም በመጨረሻ ታንክ ሄዶባቸው፤ አሟሟታቸውም አሳዛኝ ሆነ፡፡ አማን የሐገሪቱ መሪ የሆኑት ለአምስት ወር ብቻ ነበር፡፡
ምንጭ:- ገነነ መኩሪያ (ሊብሮ)
No comments:
Post a Comment