Tuesday, June 18, 2013

የኢትዮጵያ የአረንጓዴ ኢኮኖሚ ፖሊሲ ለአፍሪካ ሀገራት አርአያ ይሆናል

የኢትዮጵያ የአረንጓዴ ኢኮኖሚ ፖሊሲ  ለአፍሪካ ሀገራት አርአያ ይሆናል
     በኢትዮጵያ እየተተገበረ ያለው የአረንጓዴ ኢኮኖሚ ለሌሎች የአፍሪካ ሀገራት በአርአያነት የሚጠቀስ መሆኑን የአፍሪካ ሃይል አቅርቦት ጉዳዮች ማህበር ገለፀ፡፡

     በአለም አቀፍ የሃይል ካውንስል፣ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ሀይል ኮሚቴ፣ የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን እና የአፍሪካ ሀይል አቅርቦት ማህበር ቀጣይነት ያለው የሀይል አቅርቦት ለአፍሪካ“ በሚል መሪ ሀሳብ ያዘጋጁት አውደ ጥናት በአዲስ አበባ ተጀምሯል፡፡ በአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን የመሰረተ ልማት እና ሀይል ዳይሬክተር ዶክተር አቡበከር ባባ ሙሳ አፍሪካ አሁን ያለችበትን ፈጣን የዕድገት ጉዞ ቀጣይነት እንዲኖረው የሀይል ልማት ዘርፍ ላይ ትኩረት ተሰጠቶ ሊሰራ ይገባል ብለዋል፡፡
 
   “የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን በተለይ በመሰረተ ልማት ዕድገት ለአፍሪካ  መርሀ ግብር 40 በመቶውን ለሀይል ልማት ዘርፍ ትኩረቱን ሰጥቶ ይሰራል፡፡በተለይም በንፋስ ፣ የውሃ  እና የፀሃይ ሃይል ማመንጫዎች ላይ በሰፊው ለመስራት ተዘጋጅቷል፡፡“

     የአፍሪካ ታዳሽ ሀይል አጠቃቀም ከሌሎች አሀጉሮች ጋር ሲነፃፀር ዝቅተኛ መሆኑን እና በታዳሽ የሃይል ልማት ዘርፍ ላይ የተጠናከረ ስራ ሊሰራ እንደሚገባም የአለም አቀፍ የሀይል ካውንስል የፕሮግራሞች ዳይሬክተር ኤሌና ኒኬሽ ገልፀዋል፡፡ የውሃ እና ኢነርጂ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ከበደ ገርባ በአለም ላይ በተከሰተው የአየር ንብረት ለውጥ ችግር ኢትዮጵያም ተጎጂ በመሆንዋ በተለይም ለታዳሽ ሀይል ልማት ትኩረት እንደተሰጠው ገልፀዋል፡፡የአፍሪካ ሀይል አቅርቦት ማህበር ዋና ሃላፊ በበኩላቸው የኢትዮጵያ የአረንጓዴ ኢኮኖሚ ፖሊሲ ለሌሎች የአፍሪካ ሀገራት በአርአያነት ይጠቀሳል ብለዋል፡፡

   “በእርግጥ በአፍሪካ በታዳሽ ሃይል አቅርቦት በኩል የተሰራው ስራ ዝቅተኛ ቢሆንም የኢትዮጵያ የአረንጓዴ ኢኮኖሚ ፖሊሲ ለታዳሽ ሀይል አቅርቦት ላይ ትኩረት ማድረጉ ለሌሎች የአፍሪካ ሀገራት ኢትዮጵያ እንደማሳያ ማድረግ እንችላለን፡፡ ”

     በአለም ላይ ባሉ ዘጠና ሀገራት እስከ 3 ሺ አባል ድርጅቶች ያሉት የአለም አቀፍ የሀይል  ካውንስል ፍትሀዊነት ያለው፣ ተደራሽ የሆነና ከአከባቢ ብክለት ነፃ የሆነ የሀይል አቅርቦትን ሁሉንም ተጠቀሚ ለማድረግ የተቋቋመ ድርጅት ነው፡፡

No comments:

Post a Comment