Friday, June 14, 2013

     የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ዛሬ ሰኔ 6/2005 የናይል ተፋሰስ የትብብር ማዕቀፍ ስምምነትን በሙሉ ድምፅ አፀደቀ፡፡
 ማዕቀፉ ኢትዮጵያ ያላትን የተፈጥሮ ሀብት ፍትሃዊ በሆነ መንገድ እንድትጠቀም ያስችላል ተብሏል፡፡ ከ10 አመት በላይ ድርድርና ውይይት የተካሄደበትና በ 6 የተፋሰስ ሀገራት ስመምነት የተፈረመበት የናይል ተፋሰስ የትብብር ማዕቀፍ በአለም አቀፍ ደረጃ ተቀባይነት ያለውን የድንበር ተሻጋሪ ወንዞች ህግ መሰረት ያደረገ ነው፡፡
    ማዕቀፉ እ.ኤ.አ በ1929 እና 1959 ዓ/ም የተካሄደውን የግብፅና ሱዳን በአባይ ውሃ ለብቻ የመጠቀም ስመምነትን የሚሽርም ነው፡፡ ፍትሃዊ የውሃ አጠቃቀምን በማረጋገጥ በጋራ መልማት የሚያስችለውን ይህን መርህ ኢትዮጵያ፣ ኬንያ፣ ሩዋንዳ፣ ታንዛንያ፣ ኡጋንዳና ቡሩንዲ ከፈረሙ ቆየተዋል፡፡
   ሀገራቱ የማዕቀፍ ስመምነቱን ከፈረሙ በኋላ ወደ ተግባር ለመግባት በሀገራቸው ፓርላማ ማፅደቅ ቀጣይ እርምጃ ነበር፡፡ይሁንና በግብፅ በተቀሰቀሰው አብዮት ምክንያት በፓርላማ የማፅደቅ ሂደቱ እንዲራዘም መደረጉን በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግስት ተጠሪ ሚኒስትር አቶ ወንድሙ ገዛሀኝ ገልፀዋል፡፡
     የምክር ቤቱ አባላትም ኢትዮጵያ በተፈጥሮ ሀብቷ ተጠቅማ ድህነት ማስወገድ የሚያስችላት ስመምነት በመሆኑ ማዕቀፉ መፅደቅ እንደሚገባው አስተያየታቸውን  ሰጥተዋል፡፡ከምክር ቤቱ አባላት አዋጁ ለምን አሁ  መፅደቅ አስፈለገ የሚል ጥያቄም ተነስቷል፡፡
   የውሃ እና ኢነርጂ ሚኒስትሩ አቶ አለማየሁ ተገኑ ኢትዮጵያ ከወሰደቻቸው ትልልቅ ቅን እርምጃዎች አንዱ አዋጁን የማፅደቅያ ጊዜ ማራዘምዋ ነው ብለዋል፡፡ የምክር ቤቱ አባላትም በማዕቀፉ ላይ ሰፊ ውይይት ካደረጉ በኋላ በሙሉ ድምፅ አፅድቀውታል፡፡

No comments:

Post a Comment