Monday, June 17, 2013

    ፊፋ ኢትዮጵያን ጨምሮ በቶጎ እና ኢኳቶሪያል ጊኒ ላይ ተመሳሳይ ምርመራ ከፈተ
 
   
    የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ከዚህ ውጤት በኋላ ምድቡን አንድን በ13 ነጥብ በመምራት አንድ የምድብ ጨዋታ እየቀረ በጥሎማለፍ መልክ ወደሚካሄደው የቀጣዪ ዙር የአለም ዋንጫ ማጣሪያ ማለፏን ቢያረጋግጥም የአለም አቀፉ እግርኳስ ፌዴሬሽን ፊፋ እሁድ ማምሻውን ባወጣው ዜና “የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን በአለፈው ሳምንት ቦትስዋናን 2 ለ 1 በረታበት ጨዋታ ላይ ተሰልፎ መጫወት ያልነበረበት ተጨዋች አሰልፎ አጫውቷል” በሚል ምርመራ እንደሚደረግበት ማስታወቁ በኢትዮጵያዊያን ላይ የተፈጠረውን ታላቅ የደስታ ስሜት አደብዝዞታል።
 
    ፊፋ ኢትዮጵያን ጨምሮ በቶጎ እና ኢኳቶሪያል ጊኒ ላይ ተመሳሳይ ምርመራ የከፈተው የፊፋ የውድድር እና ስነ-ስርአት መተዳደሪያ ደንብ አንቀጽ 55 እና የብራዚሉ አለም ዋንጫ ማጣሪያ መተዳደሪያ ደንብ ላይ አንቀጽ ስምንትን በመጥቀስ ነው። የፊፋ የጨዋታ መዝገቦች እንደሚያሳዩት ከሆነ ምን አልባት መጫወት ሳይኖርበት የተጫወተው ምንያህል ተሾመ ሲሆን፣ ኢትዮጵያ ከደቡብ አፍሪካ ጋር 1 ለ 1 በተለያየችበት እና አዲስ አበባ ላይ ቦትስዋናን 1 ለ 0 በረታችበት ጨዋታዎች ላይ የቢጫ ማስጠንቀቂያ ካርዶች ያየ በመሆኑ በአለፈው ሳምንት ኢትዮጵያ ወደ ሎባትሴ አቅንታ ቦትስዋናን 2 ለ 1 በረታችበት ጨዋታ መሰለፍ አልነበረበትም። http://ethiopianobserver.wordpress.com/
 
    ኢትዮጵያ ጥፋተኛ ሆና ከተገኘች የአለፈው ሳምንቷ ድል ይሰረዝ እና ለቦትስዋና የ 3 ለ 0 አሸናፊነት እና ሙሉ ሶስት ነጥብ የሚሰጥ ሲሆን፣ የምድብ አንድ የደረጃ ሰንጠረዥን ኢትዮጵያ በ10 ነጥብ ስትመራ፣ ደቡብ አፍሪካ በስምንት ነጥብ ሁለተኛ፣ ቦትስዋና በሰባት ነጥብ ሶስተኛ፣ መሀከለኛው አፍሪካ ሪፐብሊክ በሶስት ነጥብ አራተኛ ደረጃን ይዘው የሚከተሉ ይሆናል። ስለዚህ ወደ ቀጣዩ ዙር የአለም ዋንጫ ማጣሪያ የሚያልፈውን የምድቡ አሸናፊ ለመለየት መሀከለኛው አፍሪካ ሪፐብሊክ ከ ኢትዮጵያ፤ ደቡብ አፍሪካ ከ ቦትስዋና የሚያደርጉት የምድቡ የመጨረሻ ጨዋታዎች ወሳኝ ይሆናሉ ማለት ነው።

No comments:

Post a Comment